1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ቱርክ፤ የመፈቅለ መንግስት ሙከራ አንደኛ ዓመት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 6 2009

የኢስታንቡል ሕዝብ የሰማዉን ለማረጋገጥ ከያለበት ሲወጣ ትላልቅ አዉራ ጎዳናዎች፤ ድልድዮች፤ የአታቱርክ አዉሮፕላን ማረፊያ በጦር ሠራዊት ተከበዋል። በከባድ የጭነት መኪኖች ተዘግተዋል። አንካራ። ሰማዩን እየሰነጠቁ የሚከንፉት ጄቶች የታቀፉትን ቦምብ-ሚሳዬል ከሐገሪቱ ምክር ቤት አዳራሽ እና ቤተ-መንግሥቱ ላይ ዘረገፉት። መፈንቅለ መንግስት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2gQAx
Deutschland Köln Pro-Erdogan-Demonstration
ምስል Reuters/T. Schmuelgen

Türkei-Ein Jahr nach dem putschversuch - MP3-Stereo

የቱርኩን ፕሬዝደንት የረሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንን መንግሥት በኃይል ለማስወገድ አምና የተደረገዉ ሙከራ የከሸፈዉ በሰዓት ዕድሜ ነዉ። ግን በአጭር ጊዜ ሦወስት መቶ ያክል ሕይወት ጠፍቶበታል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ ተካፍለዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ተባርረዋል ወይም ታግደዋል። 50 ሺሕ ያክል ታሥረዋል። የፕሬዝደንት ኤርዶኻን ሥልጣን ተጠናክሯል። የዶቼ ቬለዉ ክሪስቲያን ቡትኬራይት ያቺን ቀን የዘከረበትን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተዉ አጠናቅሮታል።

ሐምሌ 15 2016 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ቱርክ። መሽቷል። ግን በጋ ነዉ። በዚያ ላይ የሸዋል ኢድ ማግስት በመሆኑ-ኢስታንቡል-አካራ፤ ኢስሚር-ቡርሳ ገና እንደሞቁ፤ እንደደመቁ፤ ነዋሪዎቻቸዉ እንደነቁ ነዉ። በየቤቱ የገባዉ አንድም እርስበርሱ ያወጋል፤ አለያም ከየቴሌቪዥኑ ፊት ተገጭሯል። ሌላዉ በየካፌ፤ ምግብ ቤቱ ያዉካካል፤ አለያም ለስለስ ያለዉን የበጋ ምሽት አየር እየኮመኮመ በየአዉራ ጎዳናዉ ያዘግማል።
አራት ሰዓት። የኢስታንቡል ሰማይ ያንኮራኩር ያዘ። የአንካራም። ዝናብ አይደለም። ሔሊኮብተር ነዉ።
                                  
ለካ ያቺ ምሽት የወትሮዋ አልበረችም። ግን ለማሰቢያ ጊዜ የለም። ወትሮም የተረበሸዉን ሰማይ ሌላ ከባድ ድምፅ አደበላለቀዉ። ተዋጊ ጄት።
                                
የኢስታንቡል ሕዝብ የሰማዉን ለማረጋገጥ ከያለበት ሲወጣ ትላልቅ አዉራ ጎዳናዎች፤ ድልድዮች፤ የአታቱርክ አዉሮፕላን ማረፊያ በጦር ሠራዊት ተከበዋል። በከባድ የጭነት መኪኖች ተዘግተዋል። አንካራ። ሰማዩን እየሰነጠቁ የሚከንፉት ጄቶች የታቀፉትን ቦምብ-ሚሳዬል ከሐገሪቱ ምክር ቤት አዳራሽ እና ቤተ-መንግሥቱ ላይ ዘረገፉት። መፈንቅለ መንግስት ነዉ። ኢስታንቡል፤ የከተማይቱ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ መንገድ፤ ድልድይ፤ አዉሮፕላን ማረፊዎችን ከከበቡት ወታደሮች ጋር ይተናነቅ ገባ። የጦሩ አፀፋ-ጥይት።
                                    
አገር አማን ብለዉ እረፍት ላይ የነበሩት ፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኻን በርግጥ ድፍረት፤ ቁርጠኝነት፤ በሕዝባቸዉ ላይ የመተማመን መንፈሳቸዉ ጨርሶ አልተለያቸዉም። በጃቸዉ ላይ የነበራቸዉ መሣሪያ ግን አንድ ናት። ተንቀሳቃሽ ሥልክ። መዘዟት። ከሐገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር አገናኝተዉ የቪዲዮ መልዕክቱን ያንቆረቁሩት ገቡ።
                           
«የሐገሬ ሕዝብ ሆይ! ወደ አደባባይ እና አዉሮፕላን ማረፊያ ወጥተሕ የጥቂት ቡድናትን መፍንቅለ መንግሥት እንድትቃወም እጠይቃለሁ።»
ቱርክ የመሪዉን መልዕክት ሲሰማ የሱሌይማንያሕ፤ የኦስማን፤የአታቱርክ ጅግንነት እየሰበቀዉ ከታጠቁ ወታደሮች ጋር ሊጋፈጥ ግልብጥ ብሎ ተመመ። ወታደሩ በሕዝብ ላይ ይተኩሳል።
                                      
ጥይቱ አልበቃ ሲለዉ በተደረደሩ መኪኖች ዉስጥ የነበሩ ሰዎችን በታንክ ይደፈጥጣል። ሰዉ ይረግፋል። ሕዝቡ ግን አስከሬን እየተዘናገረ የወታደሩን ማንቁርት ያንቃል። ጎሕ ሲቀድ ፍልሚያዉ በሕዝብ ድል አድራጊነት ተደመደመ።የፕሬዝደንት ሬሴብ ጠይብ ኤርዲኻን መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራዉ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት መንፈሳዊ መሪ ፌቱላሕ ጉለንን ለመወንጀል ጀምበር እስክትበርቅ አልጠበቀም። ሰዉዬዉ እና የሚመሩት ንቅናቄ አሸባሪ ተብሎ ተወነጀለ። ንቅናቄዉ ኤርዶኻን የሚመሩት የAKP የተባለዉ ፓርቲ ጥብቅ ተባባሪ ነበር።
                              
«ጠንካራ ትብብር መሥርተዉ ነበር። ሁለቱም ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸዉ። አሁን ግን (የጉለን ሰዎች) አታለሉን ይላሉ። የመንግሥት ሥልጣን ይዘዉ ስንቴ ነዉ የሚታለሉት?»
ይጠይቃሉ የፖለቲካ ተንታኝ ሴዚጊን ታንሪኩሉ። ሙከራዉ በሰዓትት ልዩነት ከሽፏል። የ249 ሰላማዊ ሰዉ ሕይወት ቀጥፏል። መዘዙ ለዛሬም ተርፏል። ቅዳሜ አመቱ።

Türkei Ausnahmezustand: Folgen des Putsches
ምስል Getty Images/AFP/A. Messinis
Türkei Fethullah Gülen
ምስል picture-alliance/dpa/fgulen.com

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ