1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቴዲ አፍሮ እና አወዛጋቢው ሠነድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2009

የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን «ኢትዮጵያ» የተሰኘው አዲስ የሙዚቃ አልበም መውጣት በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችን የተቆጣጠረ አቢይ ርእሰ-ጉዳይ ሆኗል፤ ቃኝተነዋል። የአዲስ አበባ ከተማን እና ኦሮሚያን በተመለከተ ተዘጋጀ የተባለዉ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ሰነድ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችንም አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/2cOwH
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ገነው በመውጣት ቁንጮው ላይ ከተቀመጡ የዘመኑ የጥበብ ሰዎች ዋነኛው መሆኑ ይነገርለታል። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን፥ ቴዲ አፍሮ። «ኢትዮጵያ» የሚል ስያሜ የሰጠው አልበሙ ይፋ መኾን አድናቂዎቹን ሲያስፈነጥዝ ነቃፊዎቹን አበሳጭቷል። አዲስ አበባ በቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ስትቦርቅ የብዙዎችን ቀልብ ሰንቆ የያዘ ሰነድም ሲዘዋወርባት ሰንብቷል። ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ሕገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም እንዳለው የሚተነትነው ባለ 46 ገጽ የጥናት ሰነድ እና ባለ 14 ገጽ አዋጅ። ሰነዱን በኦሮሚያ «የክልሉ መንግሥት የማያዉቀዉ መሆኑን» እስከገለጠበት ጊዜ ድረስ የተለያየ ትርጓሜ ሲሰጠው ቆይቷል።  

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ዘንድሮ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ለአድናቂዎቹ ጆሮ ያደረሰው «ኢትዮጵያ» የተሰኘው አልበሙ አድናቂ እና ነቃፊዎቹን ለሁለት ጎራ ከፍሎ በማኅበራዊ መገናኛዎች ማጨቃጨቅ ይዟል። አድናቂዎቹ፦ የቴዲ አፍሮ የዘፈን ግጥሞችን እና የዜማ አመራረጡን በመተንተን አወድሰዉታል። ቴዲ የሚያቀነቅነው ኢትዮጵያዊነትን እና ሰው መኾንን ነው ያሉት አድናቂዎቹ ምንም ይዞ ይምጣ ምን የጥበብ ትሩፋቶቹን  ሁሌም በፍቅር እናደምጣለን ሲሉ ተደምጠዋል። 
ለአብነት ያኽል ኢዮብ መሣፍንት በትዊተር ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «ለቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) እየተሰጠ ያለው አክብሮት እና ጥበቃ ለድምፃዊው ችሎታ የተሰጠ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጲያ አንድነት የተሰጠ ነው ብዬ ስለማስብ ደስተኛ ነኝ» ብሏል።

ነቃፊዎቹ በበኩላቸው ቴዲ አፍሮ በጥበባዊ ሥራው ሊያድግ አልቻለም፤ ዘንድሮም ይዞ የቀረበው ቀድሞ ያሰማንን በመቀባባት እና ከሌሎች አርቲስቶች በመውሰድ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። 

በነገራችን ላይ ክርክሩ በትችት እና አድናቆት ብቻ አልተገታም። የጥበብ ሥራውን ሕገ-ወጥ በኾነ መልኩ ዩቲውብ ላይ እስከመጫን የደረሱም አልታጡም። ቴዲ ወጥ ሥራ አልሠራም ከሌላ ወስዶ ነው የሚል አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል  ግርማ ጉተማ ይገኝበታል። 

Symbolbild Mikrofon
ምስል Fotolia/Serg Nvns

ግርማ ጉተማ በትዊተር ገጹ፦«ቴዲ አፍሮ አዲሱ ሲዲ ውስጥ የተካተቱት ዘፈኖች ዜማቸው ከሌሎች የተሰረቀ ነው።» ሲል ጽፏል።  ለማጣቀሻ ብሎም ከቴዲ አፍሮ አዲስ ዘፈኖች መካከል አንዱን ከዩቲውብ ላይ በመስወድ አቅርቦታል። «እማ ዘንድ ይደር አምሳሌ» የሚል ርእስ ያለው ዜማ ግን ግርማ ትዊተር ላይ ከተያያዘው ዩቲውብ ተደምስሷል።  

«የትውልዴ የሙዚቃ ንጉሥ ነው!» ሲል አድናቆቱን የቸረው ደግሞ ኪሩቤል ተሾመ ነው። ኪሩቤል በትዊተር ገጹ፦ «በፍፁም ቅንነትና በንፁህ አድናቆት ነው ይህን የምመሰክረው» ይላል። ቀጠል አድርጎም «ይኽ የኔ የግሌ የውስጤ እውነት ነው። ሰውን ላለማስከፋት ብዬ እውነቴን ከመተንፈስ ብቆጠብ ሕሊናዬ ይወጋኛል! ቴዲ አፍሮ» ሲል መልእክቱን አስተላልፏል። 

በባሕላዊ ውዝዋዜ እና ቅንብር ታዋቂ የኾነው አብዮት ካሣነሽ ለቴዲ ያለውን ፍቅር ለማሳየት መኪና እያሽከረከረ፤ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃን ከፍቶ በተቀመጠበት እስክስታ እየወረደ የሚታይበትን ቪዲዮ በፌስቡክ በቀጥታ አስተላልፏል። «ከያኔነት ነጠላ ችሎታ አለመሆኑን በአንተ አየሁ። ጥበብ ፍቅርና እውነት ከሌለው ከንቱ መሆኑንም ተረዳሁ» በሚል ጽሑፍ የሚንደረደረው አብዮት አርቲስት ቴዎድሮስ ለጥበብ እራሱን አሳልፎ የሰጠ ትዕግስተኛ እና በጽናት የሚጓዝ ጠቢብ ብሎታል። «ወጀብ የማይንጥህ ሁካታና ጫጫታ የማያስደነብርህ እውነተኛ ጠቢብ አንተን አየሁ» ሲልም ለቴዎድሮስ ካሣሁን ያለውን ፍቅር ገልጧል። 

እሸቱ ሆማ ቄኖ ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «የጥቁር ሰው ዜማ አፄ ቴድሮስ ላይ የሆነ ቦታ ተወሽቃለች ልበል? ወይስ ጆሮዬ ነው?» ብሏል።

አርቲስት መስፍን ጌታቸው «ቴዲ አፍሮ ለኔ ንጉሤ ነው» ሲል በፌስቡክ ጽፏል፡፡ «በደም ከዘር ማንዘሮቹ ወርሶ ወይም ደግሞ በጦር በጎራዴ ተዋግቶና ድል ነስቶ ሳይሆን በፍቅር በብርታትና በጥበብ ሚሊዮኖችን በማንበርከክ በፀጋ ተቀብቶና አክሊል ደፍቶ ብዙዎች በአንድ ሰአት የአየር ግዜ አንዲት ቁም ነገር ማስጨበጥ አቅቶን ስንዳክር አራት መቶ እና አምስት መቶ ገፅ መጽሐፍትን በአምስት ደቂቃ ዘፈን ከነ ሙሉ ለዛው በዜማ በመተረክ ደግሞ ደጋግሞ ብቃቱን ያሳየና ከነሙሉ ግርማው ዙፋን ላይ የዋለ እውነተኛ ንጉሥ ነው» ሲል ገልጦታል።

ዘርይሁን በትዊተር ባስተላለፈው መልእክቱ፦ «ቴዲ አፍሮ የሚያስባትና የሚሰብካት ኢትዮጵያ እኛን አትውክልም የሚሉ ኃይሎች ትችታቸው ተገቢ የሚሆነው እነርሱ እራሳቸው ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ በምናባቸውና በሚያራምዱት ፖለቲካቸው አካተው ሲያልሙና ሲሰብኩ ብቻነው» ብሏል።

አዲስ አበባ የቴዲ አፍሮ «ኢትዮጵያ» የተሰኘውን አዲስ አልበምን ዋነኛ መነጋገሪያዋ ከማድረጓ ጥቂት ቀደም ብሎ አንድ በኢንተርኔት የተሰራጨ ሰነድ ይዘት በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ አጭሮባት ነበር። የኦሮሚያ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ስለሚኖረው ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም በሚል የሚያትተው ሰነድ ማን እንዳሰራጨው በይፋ አይታወቅም። 46 ገጽ ያለው ይህ ሰነድ እና ባለ 14 ገጹ «አዋጅ» በሚል ቃል የወጣው ጽሑፍ አዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነቷ ነባር ነዋሪዎች ያላቸው ኦሮሞዎች እንደሆነ ይገልጣል። 

Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

ጽሑፉ ስለከተማዋ ስያሜ፤ የሥራ ቋንቋ፤ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መብት እና ልዩ ጥቅም ይዘረዝራል። የከተማዋ ስም እና በከተማ ውስጥ የሚገኙ የመንደር ስሞችንም ነባር ወዳላቸው የኦሮምኛ ቃላት ለመለወጥ እንደሚሠራ ያትታል። 

«አዋጁ» ካካተታቸው ነጥቦች መካከል፦ በከተማዋ መስተዳደር ለኦሮሞ ተወላጆች ብቻ የተለየ ድምፅ እንደሚኖር፤ በኢኮኖሚው ዘርፍም ከሊዝ ነጻ መነገድ እንደሚችሉ፤ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ድምጽ የሚሰጡበት በእየ 5ዓመቱ የሚቀየር የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባኤ እንደሚቋቋም መገለጡ ጥቂቶቹ ናቸው።

በተጨማሪም በከተማዋ የሚኖሩ ኦሮሞዎች መሰብሰቢያ ስፍራዎችን ሲጠይቁ ቅድሚያ እንደሚያገኙ፤ አደባባዮች እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን ጨምሮ አንዳንድ ሥፍራዎች በኦሮሚኛ ስያሜ እንደሚቀየሩ፤ ቀደም ሲል የነበሩ የከተማ ቻርተር እና መሰል አዋጆች ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው የሚያትተው አዋጅ በአምስት ክፍሎች የተዋቀረ ነው።  ይህን አስመልክቶም ሰነዱ ሆን ተብሎ የሰዉን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የተሰራጨ «የተንኮል ውጤት» ነው ሲሉ አስተያየት የሰጡ አሉ።

ይኽ አዋጅ እና ሰነድ የኦሮሞ ጥያቄን የያዘ ነው ሲሉ ድጋፋቸውን የቸሩትም ነበሩ። መዘዝ ሊያስከትል የሚችል፤ በሕዝብ መሀል ግጭት ሊያጭር የሚችል ነው ሲሉም አጥብቀው የተቹት አሉ። 

ሰነዱ ኦሮሚያን በሚያስተዳድረው ኦሕዴድ ነው የተዘጋጀው ተብሎ ቢለቀቅም የኦሮሚያ መንግሥት ግን ሰነዱን እንደማያውቀው በፌስቡክ በኩል በአጭር አረፍተ ነገር አሳውቋል። አቶ አዲሱ አረጋ ቅጤሳ፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ በፌስቡክ ገጻቸው ቀጣዩን አጠር ያለ መልእክት አስፍረዋል።  

«የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ ስለምታገኘዉ ልዩ ጥቅም ለመደንገግ «በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተዘጋጀ ረቂቂ አዋጅ» ነዉ ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለዉን ሰነድ የክልሉ መንግስት የማያዉቀዉ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን፡» 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ