1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የወጣቶች ዓለም

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥር ወር ጀምሮ ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ መምህራንን አለማካተቱ በርካታ መምህራንን አስቆጥቷል። በዚህም የተነሳ ሰሞኑን አንዳንድ መምህራን አድማ መምታታቸዉ ወይም ለተቃዉሞ መሰብሰባቸዉ እና አንዳዶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል። 

https://p.dw.com/p/2YwNl
Lehrerstreik in Guinea-Bissau
ምስል DW/Braima Darame

በ 2008 ዓም ለኢትዮጵያ መምህራን የደሞዝ ማስተካከያ መደረጉ ተሰምቷል። አሁን ግን መንግሥት ለሌሎች መስክ ሰራተኞች ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ መምህራንን አላካተተም። በዚህም የተነሳ መምህራኑ  ተቃውሞ እና ቅሬታቸውን እየገለፁ ነው።  ይህም በመማር ማስተማሩ ሂደቱ ላይ ተንፀባርቋል። 
በመርሳ ከፍተኛ መሰናዶ ት/ቤት የ 11ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ የገለፀልን ወጣት ጀማል ከሳምንቱ አጋማሽ አንስቶ በተገቢው ሁኔታ ትምህርት እያገኘ አይደለም።በመርሳ መሰናዶ የትምህርት ቤት ተማሪዎች እሮብ ዕለት ግቢ ሲገቡ ፤በስብሰባ ምክንያት ትምህርት የለም ተብለው እንዲመለሱ ተደርገዋል። ጀማል ስብሰባው ምንን አስመልክቶ እንደሆነ ባያውቅም አድማ ስለመሆኑ አይጠራጠርም።
በኮንቦልቻ ዩንቨርስቲም ቢሆን የሁለተኛ ወሰነ ትምሕርት  ገና አልተጀመረም ። የመጀመርያ አመት ተማሪ የሆነችው ቤቲ የግማሽ አመቱን ፈተና ወስዳ እርፈት እንደወጣች እስካሁን ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሰችም። ወጣቷ  ምዝገባ ያልጀመረበትን ምክንያትም ሆነ መቼ ተመልሳ ትምህርት እንደምትጀምር አታውቅም።  ስሙን እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ተማሪ እንደገለጸልን የትምህርት መስተጓጎሉ በአርባ ምንጭ ዩንቨርስቲም ተከስቷል። ምንም እንኳን ሁለተኛው ወሰነ ትምሕርት ትምህርት ያለፈው ሳምንት ቢጀምርም ሰሞኑን ተማሪው ዶርሙ ተቀምጧል።
«መምህራን አሁን ይባስ ብለው ክፍል ቢገቡም ተወያዩ ብለው ነው እሚወጡት» የሚል አስተያየትም የሰጠን ተማሪ ነበር። በደቡብ ወሎ መቅደላ ፤ አንድ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ፤ በርካታ መምህራን ለምን የማስተማር ፍላጎታቸው እንደቀነሰ ነግረውናል። 
በወረዳው የመማር ማስተማሩ ሂደት ሲቋረጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመትም የደሞዝ ማሻሻያውን አስመልክቶ መምህራን ቅሬታ አቅርበው ነበር። ያኔም የደሞዝ ማሻሸያው ተደርጎላቸዋል። በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት በአሁኑ ሰዓት በመምህራኑ ርምጃ ቢስተጓጎሉም፤ ተማሪዎቹ ምክንያቱን ይረዳሉ። ከደቡብ ወሎ ቦረና የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነ አንድ ወጣት በላከልን አስተያየት «ፓይለት፣ ፕሬዝዳንትም ሆንን ዶክተር ከመምህሮቻችን ነው የምንወጣው ይህ ትልቅ በደል ነው። ለመምህራን ነበር መንግስት እንክብካቤ መስጠት የሚገባው ብሎናል። የመርሳ ከተማው ተማሪ ጀማልም ጥያቄያቸው አግባብ ነው ይላል። ተማሪዎች ፤ በፖለቲካ እና ከዚሁ የመምህራን ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ መደረጉ የአርባ ምንጩን ተማሪ አበሳጭቷል። ምንም እንኳን ዩንቨርስቲ የሚገኙ ጓደኞቿ «ትምህርት» ተጀምሯል ብለው እስኪጠሯት የምትጠባበቀው ቤቲ  ለጊዜው ከቤተሰቦቿ ጋር በቂ ጊዜ ቢኖራትም፤ ኋላ ላይ በጊዜ ማጣት እንዳትጨናነቅ ስጋት አላት። 
ሰሞኑን የተፈጠረውን የትምህርት መተጓጎል የቃኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅም ያገኙታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥር ወር ጀምሮ ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ መምህራንን አለማካተቱ በርካታ መምህራንን አስቆጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥር ወር ጀምሮ ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ መምህራንን አለማካተቱ በርካታ መምህራንን አስቆጥቷል። ምስል picture-alliance/ dpa


ልደት አበበ

ነጋሽ መሃመድ