1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትምህርት

ረቡዕ፣ ኅዳር 17 2001

የኅብረተሰብን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መሠረቱ ትምህርት ነው። ከትምህርትም --ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ!

https://p.dw.com/p/G2je
ወጣት ተማሪዎች፣ምስል Petra Reategui

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ ይበልጥ የምናተኩረው፣ በትምህርት ላይ ይሆናል። በመጀመሪያ ፣ በጥቂቱ ከሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ጋር ግንኙነት ያላቸው ዜናዎች---

በርሊን፣ የጀርመን የምርምርና ልማት ሚንስቴር ፣ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማነቃቃት የመደበውን ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያሰጠውን ሽልማት 8 የውጭ ዜጎች የሆኑ ተማሪዎች ማሸነፋቸው ፣ ትናንት በይፋ ተገለጠ። 1,65 ሚልዮን ዩውሮ(2,09 ሚልዮን ዶላር )የተመደበለትን ሽልማት 2 ኢጣልያውያን (አንዲት ሴትና ወንድ)ተመራማሪዎች ይገኙበታል። እ ጎ አ በ 1889 ዓ ም ፣ በእስዊድን የእሽቶክሆልም ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሆና ከመመደቧ በፊት ትምህርቷን በጀርመን ሀገር በተከታተለችው፣ በሂሳብ ሊቅነቷ ትታወቅ በነበረችው ሩሲያዊት ስም፣ በሶፊያ ኮቫሌቭስካያ ስም የተመደበውን ሽልማት ዘንድሮ ካሸነፉት መካከል ዳንኤል ኦሪቲና ቺንዚያ ካሲራጊ፣ የተባሉት ይገኙበታል። ኦሪቲ፣ በሮማና ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲዎች የተማረ ሲሆን አሁን በርሊን አቅራቢያ ፖትስዳም ውስጥ በስበት ነክ-ፊዚክስ ላይ፣ በመመራመር ላይ የሚገኝ ነው። በነባቤያዊ ፊዚክስ ላይ ያደረገው ትኩረት ጊዜንና ቦታን ያጣመረ ሲሆን ፍጥረተ-ዓለም እንዴት ለመጀመሪያ ጊዜ እውን ሊሆን ለቻለበት ምሥጢር መልሱን ለማግኘት፣ ሊረዳ ይችላል ነው የተባለው።

«ፖሊቴክኒኮ ዲ ሚላኖ» በተሰኘው የትምህርት ተቋም ተማሪ የነበረችው ካሲራጊ በበርሊን ነጻ ዩኒቨርስቲ፣ ገዝፍ ባለው ነገር ባተኮረችበት የፊዚክስ ምርምር ሳቢያ ነው ለሽልማት የበቃች።

ሮማ፣

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን (ቫቲካን) ከ 375 ዓ መት በፊት በታዋቂው የከዋክብት ተመራማሪ፣የሥነ-ፈለክ ሊቅ ጋሊሊዮ ጋሊሌይ ላይ የተካሄደውን ክስና የፍርድ ሂደት በኅትመት መልክ ይፋ እንደምታደርግ ተገለጠ። ይህን ያስታወቁት «ሳይንስ ጋሊሊዮ ካለፈ ከ 400ዓመት ገደማ በኋላ» በሚል ርእስ የተዘጋጀው ጉባዔ ከመከፈቱ በፊት በዋዜማው የርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳቱ የባህል ጉዳይ ተጠሪ ሊቀ-ጳጳስ ጂያንፍራንኮ ራቫሲ በሰጡት ቃል ላይ ነው።

እ ጎ አ በ 1564 ዓ ም በ ፒሣ ከተማ የተወለደው ጋሊሊዮ ጋሊሌይ ፣ ፀሐይ ሳትሆን፣ መሬት ናት በፀሐይ ዙሪያ የምትሽከረከር የሚለውን የኒኮላስ ኮፐርኒስ ነባቤ ቃል የተረጋገጠ ነው በማለቱ፣ እ ጎ አ በ 1633 ተከሶ ከመገደል ለማምለጥ ሳይሳሳት ተሳስቼአለሁ ቢልም፣ ላልተወሰነ ጊዜ እሥራት ተበይኖበት በእሥር ቤት ጊዜውን ማሳለፍ ግድ ሆኖበት ነበር። እ ጎ አ በ 1642 ዓ ም፣ እስከዕለተ-ሞቱ ድረስ ጊዜውን ያሳለፈው በፍሎሬንስ የገጠር ቦታው ሲሆን ፣ የምርምር ሥራዎቹ ሁሉ ህግ ታግደው ነበር። ይሁንና የተላለፈበት ብይን በያኔው ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዑርባን 8ኛ ፊርማ ያልጸደቀ እንደነበረ ታውቋል።

እ ጎ አ በ 1992 ዓ ም፣ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጉዳዩ እንዲጣራ አዘው 13 ዓመት ምርመራ ከተደረገ በኋላ ፣ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን በተጠቀሰው ነጥብ ረገድ መሳሳቷን አምናለች። የተባበሩት መንግሥታት መጪው 2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዐመት ፣ «የሥነ-ፈለክ መታሰቢያ ዘመን እንዲባል የወሰነ ሲሆን እ ጎ አ በ1609 ዓ ም ጋሊሊዮ የተጠቀመበት የሩቅ ማሳያ መነጽር ፣ቴሌስኮፕም አብሮ ይታሰባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የአሁኑ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛም፣ በአግዚአብሔር ማመንና የተፈጥሮ ሳይንስ የሚጋጩ አይደሉም ሲሉ ባለፈው ወር ተሰብስበው ለነበሩ ሳይንቲስቶች አስታውቀዋል። «ሳይንስ ማለት፣ እግዚአብሔር የፈጠረውን ለማወቀ የሚደረግ የምርምር ሂደት ነው» ማለታቸውምተጠቅሷል።

ፓሳዴና፣

የአሜሪካው የኅዋ ምርምር ድርጅት (NASA) በዓለም አቀፉ የኅዋ ጣቢያ ሽንትን አጣርቶ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ማቀረብ የሚችለውን መሣሪያ በአዲስ መልክ በማሻሻል ችግሩ እንዲወገድ ማድረጉን አስታወቀ። ይህም በመሳካቱ፣ በመጪው ዓመት ኅዋ ላይ የተመራማሪዎችን ቁጥር ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ብሩኅ ተስፋ ነው ያሳደረወ። የተመራማሪ ቡድን አባላት ቁጥር ከ 3 ወደ 6 ከፍ ሊል ይችላል ማለት ነው። ውሃ ከኤሌክትሪክ መሣሪያ ፣ ተረፈ-ምርት ሆኖ እንዲገኝ ፣ የሚያደረጉት የኅዋ መንኮራኩሮች ከ 2 ዓመት በኋላ ተግባራቸውን ስለሚያቋርጡ፣ አዲሱ ዘዴ ለ NASA ጥሩ አማራጭ ሆኗል።

ድህነትን ለመታገል ፣ ረሃብን ለማስወገድ፣ በሽታን ለመከላከልም ሆን ለማጥፋት ፣ የተሻለ ለማምረትና ፣ በአጠቃላይ የኅብረተሰብን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መሠረቱ ትምህርት ነው። ከትምህርትም ---ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ!

የ ተ መ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ፣ ከትናንት ጀምሮ እስከፊታችን ዓርብ ጀኔቭ ውስጥ በዓለም ዙሪያ የትምህርት ይዞታ ምን እንደሚመስል በስፋት የሚመረምር ጉባዔ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ጀኔቭ ላይ የተሰበሰቡት ከዓለም ዙሪኢ የተውጣጡት 1,500 የትምህርት ጠበብት ፣ «ሁሉን-አቀፍ ትምህርት » በተሰኘው መፈክር ዙሪያ ላቅ ያለ ትኩረት የሚያደርጉት በአካል ጉዳተኞች ላይ ነው። የአካል ጉዳተኞች ተማሪዎችን ይዞታ ከመዳሰሳችን በፊት እስቲ ባጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ትምህርት የቱን ያህል ለልጆች ተዳርሷል የሚለውን ሁኔታ እንመልከት። ----

ከዚያው ከደርጅቱ ከ UNESCO የተገኘው በጥናት የተመረኮዘ ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ በዓለም ዙሪያ 75 ሚልዮን ያህል ልጆች ከእነዚህም መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ልጃገረዶች የትምህርት ዕድል የተነፈጋቸው ናቸው። ለ1ኛ ደረጃ ትምህርት ፣ ዕድሜአቸው ብቁ ከሆነው ከሰሃራ ምድር-በዳ በስተደቡብ በሚገኙ አገሮች ያሉ ልጆች ሲሦው ፣ የትምህርት ብርሃን የማየት ዕድል ያልገጠማቸው ናቸው። በአጠቃላይ ከበለጸጉት አገሮች ጋር ሲነጻጸር፣ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚገኙ ልጆች፣ የትምህርት ዕድል ያለማግኘት መጥፎ ዕጣቸው በ 3 እጥፍ ከፍ ያለ ነው። ቢያገኙም እንኳ፣ የትምህርቱ ጥራት ደረጃውን የጠበቀሊሆን መቻሉ UNESCO ን የሚያጠራጥር ነው።

በአሁኑ ጊዜ፣ ከዓለም ህዝብ፣ 16% «ዐዋቂዎች» (ከእነዚህም መካከል አብላጫውን ቁጥር የያዙት ሴቶች ናቸው)ማንበብና መጻፍ አይችሉም። በአዳጊ አገሮች፣ ከየ 3 ቱ ልጅ አንዱ በተመጣጣኝ ምግብ እጦት ሳቢያ፣ በአእምሮ ዕድገት ረገድ እንከን ያጋጠማቸው ናቸው።

በ48ኛው የ UNESCO ጉባዔ፣ 1,500 ያህል የመንግሥታት ሚንስትሮች ፣ጠበብትና የመንግሥታት ያልሆኑ ድርጅቶች ተጠሪዎች የተገኙ ሲሆን ፣ የአእምሮ፣ ዝግመት ያለባቸው ልጆች በኅብረተሰብ ውስጥ ያላግባብ የሚገለሉ ወገኖች ፤ ልጆችና የመሳሰሉት ሁሉም የትምህርት ዕድል በሚያገኙበት ብልሃት ላይ ነው አጥብቀው የሚመክሩት። የዩኔስኮ የትምህርት ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ክሌሜንቲና አሴዶ፣ ትምህርት ሁሉንም የሚያጠቃልል፣ የሚያቅፍ መሆን አለበት የሚባለው ፈሊጥ አዲስ አይደለም ባይ ናቸው። ----

«ይሁንና አሁንም ቢሆን፣ በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ አገሮች የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆች፣ በአእምሮም ረገድ ድክመት አለባቸው በሚል አስተሳሰብ ፣ ልጆቹ፣ ከሌሎች ተለይተው ለብቻ በተዘጋጁላቸው ት/ቤቶች እንዲማሩ ያደርጋሉ።»

በጅርመን ሀገርም ቢሆን ፣ ገና መሟላትም ሆን መስተካከል የሚገባቸው የአሠራር ሂደቶች አሉ። እስካሁን፣ የአካል ጉዳተኞችና በዚህ ረገድ እንክን የማይታይባቸው ልጆች በኅብረት የሚማሩባቸው ት/ቤቶች፣ 17% ብቻ ናቸው። ጀርመን፣ የ ተ መ ድ ፣ የአካል ጉዳተኛልጆችን የትምህርት ጉዳይ አስመልክቶ ባወጣው ደንብ እ ጎ አ በ 2006 ዓ ም፣ የተስማማች ወይም የፈረመች አገር ስትሆን፣ 90%፣ ይህን ለማሟላት እንደምትጥር አስታውቃለች። በፌደራል ክፍላተ-ሀገር ደረጃ ሽልስቪኽ-ሆልሽታይን፣ 40% አሟልታ ስትገኝ ፣ ከ16 ቱ ፌደራል ክፍላተ-ሀገር፣ በዚህ ረገድ፣ ዝቅተኛውን ደረጃ የያዘች (7% ብቻ)፣ ዛኽሰን-አንሃልት ናት።

ኢጣልያ፣ ፖርቱጋል፣ እስፓኝ፣ ቆጵሮስ፣ ሞልታ፣ ብሪታንያ፣ እስዊድንና ሊቱዋንያ ግን፣ ከጀርመን በላቀ ሁኔታ 90% ት/ቤቶቻቸው የአካል ጉዳተኞች የሆኑትን ተማሪዎች እንደሚያስተናግዱ ታውቋል። ይህን ፈለግ የተከተለችው ፊንላንድም ፣ በትምህርት ደረጃ የኤኮኖሚና የልማት ተባባሪዎች ከሆኑት አባል ሀገራት መካከል የአንደኛነቱን ሥፍራ እንደያዘች መገኘት ወ/ሮ አሴዶን አላስደነቀም አይባልም። ---

«በሰሜን(አውሮፓ) አገሮች የሚያስግርመው አንድ ነገር፣ የትምህርት ሥርዓትን የሚመለከተው ጽንሰ-ሐሳባቸው፣ በኅብረት መማርን፣ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ነው። አቅድ፣ አደረጃጀት፣ የትምህርት መ,ሣሪያዎች፣ የትምህርት ግምገማና ውጤት ፣ ሁሉም አንድነትን ያካተተ ነው። ስለሆነም ፣ ይህ ጠቅላላውን ሥርዓት ከውጥኑ ጀምሮ የሠመረ፣ የተሻለ ያደርገዋል። ዘግየት ብለው እያሰላሰሉ የሚያስተካክሉ አገሮች ያን ያህል ሊሠምርላቸው አይችልም ይሆናል። »

ትምህርት፣ መሠረታዊ መብት በመሆኑ ፣ ለሁሉም እኩል ሊዳረስ ይገባል። ለአዳጊ አገሮች ደግሞ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው፣ ትምህርት፣ ለዕድገት ዋናው ቁልፍ ነው።