ትኩረት በአፍሪቃ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26 2004የኬንያ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ሰሞኑን እረፍት ሳታገኝ ነው የሰነበተችው። አንድ መንፈሳዊ መሪ ሼክ አቦድ ሮጎ መሐመድ ሰኞ ዕለት በጥይት ተመተው ከተገደሉ በኋላ በሞምባሳ ከተማ ግጭት መነሳቱ ይታወሳል።
« አገሪቷን በጉልበተኛ ስርዓት አመራር ልናራምድ አንችልም ሲሉ የኬንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ዕሮቡ ዕለት፤ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሙአይ ኪባኪ እንዲሁ ዓመፁ ወደተካሄደበት ቦታ ተጉዘው ሀሙስ ዕለት መቻቻል በሞምባሳ ከተማ እንዲወርድ ጥሪ አድርገዋል።
« በፍፁም መጥፎ ተግባር የሚፈፁሙ ኃይላት እንዲከፋፍሉን በምንም መንገድ መፍቀድ የለብንም። የአገሪቷን የሰላም መድረክ እና የብሔራዊ ሰላም ጉባኤዎችን ማጠናቀቃችን ነው። በነዚህ ዝግጅቶች ወቅት ኬንያውያን አንዳቸው ከሌላኞቻቸው ጋ ተቻችለው የመኖርን አስፈላጊነት አጥብቀው ለመከተል በአንድነት ተስማምተዋል።»
ኪባኪ አክለውም ለችግሩ በፍጥነት መፍትሄ ማግኘት አለብን ነው ያሉት። ሼክ አቦድ ሮጎ መሐመድ ባልታወቀ ሰው ከተገደሉ በኋላ ደጋፊዎቻቸው ለሁለት ቀናት ባስነሱት አመፅ ዓብያተ ክርስትያን እና መኪናዎች በእሳት ተለኩሰዋል። በሱቆች ላይ ዘረፋ ተካሂዷል። ዶቸቬለ ያነጋገራቸዉ በሞምባሳ የስነ ልቦና ቢሮ ተጠሪ አብዱልራህማን ባዳዊ ዉጥረቱ በሙስሊምና በክርስትያን መካከል አይደለም ይላሉ፤
«ጦርነቱ በክርስትያን እና በሙስሊም መካከል አይመስለኝም። እንዲህ አይነትነገር የለም። አመጹን ያስነሱት ሰዎች መሪያቸዉ ጥበቃ ስላልተደረገላቸዉ ነዉ የተበሳጩት። አንድ ግዜ ሟቹ፤ ህይወቴ አደጋ ላይ ናት ሲሉ ለጸጥታአስከባሪዎች ስሞታ አቅርበዉ ነበር ግን ከዝያ በኋላም ምንም አይነት ጥበቃ አልተደረገም።በዝያ ላይ ደግሞ ሼክ ናቸዉ። ተከታዮቹ በሙሉ በጣም የተበሳጩት። ከተገደሉ በኋላተከታዮቻቸው ተቃዉሞአቸዉን በማሰማት ሱቆችን ተሽከረካሪዎችን አወድመዋል።ቤተ-ክርስትያን ላይ ሳይቀር ጥቃት አድርሰዋል።ግን ይሄ በክርስትያን እና በሙስሊም መካከል የተነሳ ጦርነት አይደለም።እንዲህም አይነት ነገር በኬንያም ሆነ በሞባሳ ከተማ ይከሠታል ብዬ አላስብም»
ከቤተሰባቸው ጋ ከሞምባሳ ወደ ማሊንዲ ሲጓዙ በጥይት ህይወታቸው ያለፈው መንፈሳዊ መሪ፤ ከአሸባብ ቡድን ጋ ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይታመናል። ለቡድኑም ሶማሊያ ውስጥ ገንዘብ እና ተዋጊዎች አቅርበዋል በማለት ይተቻሉ።ዩናይትድ እስቴትስ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሸባሪነት እቀባ ከተደረገባቸው ስም ዝርዝር ውስጥ ከተዋቸዋል።
ናይሮቢ ውስጥ እኢአ 1998 ዓም በአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ለደረሰው ጥቃት እና ከ200 በላይ ህይወት ለጠፋት አደጋ ዩናይትድ እስቴትስ ፤ ሼክ አቦድ ሮጎ ተጠያቂ ናቸው ብላ ደምድማለች። የመንፈሳዊ መሪው በኬንያ ያለፍቃድ የጦር መሳሪያ በመያዝ ተከሰው ዋስ ከከፈሉ በኋላ ነው የተለቀቁት። በርግጥ ከግድያው በስተጀርባ ስላለው ሰው እስካሁን የኬንያ መንግስትም ይሁን የሰብዓዊ መብት ተሟጋጅ ድርጅቶች አልደረሱበትም። ርግጥ ግን በነበረው አመፅ እስከ ትናንት ረፋዱ ድረስ የ4 የፖሊስ አባላት እና 3 ሲቪሎች ህይወት አልፏል። አመፁን ያካሄዱት ወጣቶች ከጎረኔት ሀገር ሶማሊያ ጋ ግንኙነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የሞምባሳ ፖሊስ ምክትል ሃላፊ ሮበርት ኪቱር ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።
« አገራችን ሙሉ በሙሉ ሰላም ነው። እነዚህ ጥቂት ወጣ ያሉ፤ ላለፉት ጥቂት ቀናት ሞምባሳ ውስጥ የተዘገቡ ጉዳዮች ናቸው። ግን ለህዝቡ ልገልፅለት የምወደው ማንኛውንም ህዝቡን ለማስፈራራት የሚጥር ታጣቂን ለመጋፈጥ ዝግጁ እንደሆንን ነው።»
ያለፈው ማክሰኞ የሶማሊያ ምክር ቤት የቀድሞዉን ሚኒስትር ሞሀመድ ኦስማን ጃዋሪን አዲሱ የምክር ቤት አፈጉባኤ እንዲሁኑ ሾሞአል። ከተወዳደሩት 5 እጩዎች፤ ጃዋሪ መበጀመሪያው ዙር 119 ድምፅ በማምጣት የ2ተኛነትን ቦታ ከያዙት አሊ ክሊፍ ጋላር ፊት ተሰልፈዋል። የጃዋሪ ማሸነፍ እንደተነገረ ጋላር ወዲያውኑም ከእጩ ተወዳዳሪነት ራሳቸውን አግለዋል። ጃዋሪ ከደቡቡ የሶማሊያ ክፍል ባይዶዋ ሲሆኑ ጎሳቸው ከአገሪቱ 4ተኛው ትልቅ የራሃንወይን ጎሳ ነው። ። አዲሱየሶማሊያየምክር ቤት አፈጉባኤ መምረጡ በርግጥ የተረጋጋ አመራር ላለፉት 20 ዓመታት ላልታየባት ሶማሊያ፤ አንድ ርምጃ ነው። ሆኖም ጃሚር ለምክር ቤቱ አዲስ ሰው አይደሉም። በአምባ ገነኑ የሳይድ ባሬ ጊዜም ሚንስትር ነበሩ። በርግጥ ጃዋሪ ለሶማሊያ አዲስ ተስፋ ስለመሆናቸው በቀጣይነት የሚታይ ይሆናል።
የሀገሪቷ ባለስልጣናት፣እና የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች አዲሱን አፈጉባኤ ሲያወድሱ የተባበሩት መንግስትታት ልዩ ተወካይ አውጉስቲን ማሂጃ ደግሞ ርብ ዕለት ምርጫው በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ መካሄድ አለበት ብለዋል። የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ኮሚቴ ትናንት ከሰዓት እንዳስታወቀው ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እኢአ መስከረም 10 ይካሄዳል።
የምክር ቤቱ አባላት ማክሰኞ ዕለት አዲሱን የምክር ቤት አፈጉባኤ ለመምረጥ እንደታሰበው በሶማሊያ ምክር ቤት ሳይሆን የተገናኙት ለደህንነት ሲባል፤ በአንድ የፖሊስ ትምህርት ቤት ነበር። ሆኖም ጉባኤው ጨርሶ በሞቃድሾ መካሄዱ ለበርካታ የምክር ቤቱ አባላት ትልቅ አንድ ርምጃ ነበር። እስካሁን እንደዚህ አይነት ስብሰባዎች ከሶማሊያ ውጪ ነበር የተካሄዱት። የሶማሊያን ህገ መንግስት ያፀደቁት 135 የሀገር ሽማግሌዎች እስከ ትናንት ድረስ ከሚፈለጉት 275 አባላት 260ውን አባላት መርጠዋል። የም/ቤቱ አባላት ቁጥር ከተሟላም በኋላ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አሁንም በስልጣን ላይ የሚገኙት ሼክ ሸሪፍ አህመድ ፕሬዚዳንት ሆነው በድጋሚ ለመመረጥ ከፍተኛ ዕድል አላቸው።
በምዕራብ አፍሪቃውቷ ሀገር አንጎላ ትናንት ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ውሏል። 9 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብም ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪ ተደርጓል። ገና ምርጫው ሳይካሄድ የ70 አመቱ ዶሴ ኤዱዓርዶ ዶስ ሳንቶስ አሸናፊ እንደሚሆኑ ሲገለፅ ሰንብቷል። ዶስ ሳንቶስ የአንጎላ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ፓርቲ በምህፃሩ MPLA መግዛት ከጀመረበት 33 ዓመት ጀምሮ በስልጣን ላይ ይገኛሉ። ባካሄዱት የዘንድሮው የምርቻም ዘመቻ ሙሉ በሙሉ በራስ መተማመን አሳይተዋል።
« የሀገራችን መልሶ ግንባታ ተጠናክሯል። ስለሆነም የአንጎላውያን የህይወት ደረጃ እንዲሻሻል የበኩላችንን እያደረግን ነው። ከኔጋ ወደፊት መራመድ ይቻላል። ተቃዋሚዎች ግን ወቀሳ እና ዛቻ ነው የሚችሉት። እኛ MPLAዎች ግን ለአገራችን ልማት ነው የምንሰራው።»
አንጎላ ከፖርቹጋል ነፃ ከወጣች እኢአ 1975 ጀምሮ ነፃ ምርጫ ሲካሄድ በሀገሪቱ ገና 3ኛ ጊዜ ነው። ዶስ ሳንቶስ ድምፅ ለመስጠት ትናንት በመዲናይቱ ሉዋንዳ በተገኙበት ወቅትም « ይህ ኃላፊነት የምናሳይበት እና ሁሉም ድምፅ ሰጪዎች ያለባቸውን ህዝባዊ ግዴታ የሚወጡበት ጊዜ ነው ብዬ አስባለው ነው ያሉት።
ጋሉፕ የተባለው የአሜሪካ ታዋቂ ተቋም ያለፈው አመት እንዳወጣው ጥናት ከሆነ ዶስ ሳንቶስ ከአፍሪቃ ተወዳጅነት ከሌላቸው መሪዎች አንዱ ናቸው። 16 ከመቶ የሚሆነው የአንጎላ ህዝብ ብቻ ነው እሳቸውን የሚያወድስ። የዝምባዊው ሮበርት ሙጋቤ እንኳን 30 ከመቶ በሚሆነው ህዝባቸው ዘንድ ተወዳጅነት እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል።
ይሁንና የ MPLAን ፓርቲ ስልጣን ላይ ከመቆየት የሚያዳግተው ያለ አይመስልም። ለዚህም ምክንያቱ የተጠናከረ የተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ነው። ለዘንድሮው ምርጫም ገዢው ፓርቲ በምርጫ ዘመቻው ላይ ተፅዕኖ እንዳደረገ ፤ አንጎላዊው ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተማጋች ራፌል ማርኮስ ከምርጫው በፊት ገልጿል።
« አንጎላ ውስጥ ያለው የምርጫ ሂደት ገዢውን ፓርቲ በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ነው። ከፍተኛ ሙስና ያለበት ነው። ከ 9 ሚሊዮን ህዝብ 6,5 ሚሊዮኑ ድምፅን እንዴት እንደሚሰጥ አያውቅም። 1,5 ሚሊዮን የመራጭ ካርዱ በየምርጫ ጣቢያው መሳቢያ ተደብቀው ይገኛሉ። ማንኛውም ጤናማ አስተሳሰብ ያለው አንጎላዊ ይህ ምርጫ በሰላም እና በሀቅ ይካሄዳል ብሎ አያምንም።»
ከአንጎላ ሁለተኛው ትልቁ ፓርቲ ኃላፊ ኢሲያስ ሳማኩቫም ተመሳሳይ አስተያየት ነው በምርጫው ቀን የተናገሩት። የመላው አንጎላ ብሔራዊ ነፃ አውጪ ህብረት መሪ እንዳስታወቁት ምርጫውን ተቀባይነት እንደማይሰጡት እና ለነፃ ምርጫው ወሳኝ የሆኑት ነገሮች ባለመሟላታቸው ፓርቲው አስቀድሞ ምርጫው እንዲካሄድ ማለቱን አሳስበዋል።
ከምርጫው ጥቂት ቀናት በፊት ለምርጫው ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አለመሟላታቸውን ሊዛ ሪምሊ ተናግረዋል። ለሰብዓዊ መብት የሚሟገተው ድርጅት በሂውማን ራይትስ ዎች የአንጎላ ተንታኝ ናቸው።
« በ2008 ዓ ም በርካታ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ነበሩ። በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ለረዥም ጊዜ ተመድበው ቆይተዋል። ባሁኑ ምርጫ ግን ቁጥራቸው ትንሽ የሆነ የምርጫ ታዛቢዎች ነው ያሉት። እስከዛሬ ድረስ ኤምባሲውን ጨምሮ ፍቃድ አልሰጧቸውም። ይህ የተለያዩ የሲቪሉን ድርጅቶችንም ይጨምራል። ከነዚህ መካከል በርካታ ገለልተኛነታቸው የታወቁ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅቶች ይገኙበታል።»
ምንም እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ያሰሙ ቢሆንም ምርጫው ትናንት ተካሂዷል። እንደተገመተው የMPLA ፓርቲ ምርጫውን ካሸነፈ በቀጥታ የፓርቲው መሪ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ይይዛሉ። ያም ሰው፤ ዶስ ሳንቶስ መሆናቸው ነው።
ልደት አበበ
መስፍን መኮንን