1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26 2005

ትኩረት በአፍሪቃ በሶማሊያ በረሀብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተጠቀሰው በላይ ከፍተኛ መሆኑ፣ እንዲሁም የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ለአፍሪቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ መፈለጋቸውን በሚዳስሱ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ቬስተርቬለ ለአፍሪቃ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለፁት በአምስት ቀናቱ የአፍሪቃ አገራት ጉብኝታቸው ወቅት ነው።

https://p.dw.com/p/18S7o
የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ
የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለምስል DW/R.da Silva

እጎአ ከ2011 እስከ 2012 የአፍሪቃ ቀንድን በመታው ረሀብ ያለቁት ሶማሊያውያን ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይፋ ሆነ። አሁን የተገለፀው ይህ አሐዝ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ከእጥፍ በላይ እንደሆነ ነው። ቬስተርቬለ አፍሪቃ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋታል ሲሉ አስታውቀዋል። የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን ማጠንጠኛ አበይት ጉዳዮች ናቸው። ሁለቱንም በቅደም ተከትል እናቀርብላችኋለን። በመጀመሪያ ወደ ሶማሊያው ርዕሰ-ጉዳይ እናቅና።

እጎ አ ከ2011 እስከ 2012 ድረስ በአፍሪቃ ቀንድ አገራት በተለይ በሶማሊያ ተከስቶ በነበረው ረሐብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ነው ከሰሞኑ የወጣ አንድ ዘገባ ያረጋገጠው። በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ FAO እንዲሁም በአሜሪካን መንግስት የሚደገፈው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቅንጅት ባሳለፍነው ሐሙስ በጋራ ያወጡት ዘገባ ነው በሶማሊያው ረሐብ ያለቁት ሰዎች ቁጥር አስደንጋጭ እንደሆነ ይፋ ያደረገው። በሶማሊያ የFAO ምክትል ኃላፊ ሩዲ ቫን አከን።

«በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነው። 258,000 ሰዎች ናቸው ያለቁት። ይህ እንግዲህ እስካሁን ከተደረጉት ጥናቶች በተጨባጭ የተከናወነ የመጀመሪያው ጥናት ነው።»


ከእዚህ ቀደም በሶማሊያ በረሐብ ምክንያት አለቁ የተባሉት ሰዎች ቁጥር ከ 50,000 እስከ 100,000 ይገመት እንደነበር በተደጋጋሚ መጠቀሱ ይታወቃል። ይህ አሁን ይፋ የሆነው ቁጥር ከእጥፍ በላይ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል ግማሽ ያህሉ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንደሆኑ ታውቋል። ከእዚህ ቀደም የተገመተው አሁን ከተጠቀሰው በእጥፍ ለምን ያነሰ እንደነበር ሩዲ ቫን አከን አብራርተዋል።

«ይህ በተጨባጭ ተገቢ የሆነውን ስታቲስቲካዊ ጥናት ተግባራዊ ያደረገ የመጀመሪያ ዘገባ ነው። ከእዚህ ቀደም የነበረን ግምት ነበር። የከዚህ በፊቱ ውጤቱ ጥሩም መጥፎም ሊሆን የሚችል በመስክ ላይ የተከናወነ ጥናትን ያላካተተ ግምት ነበር።»

ኦክስፋም የተሰኘው የእንግሊዝ ምግባረ-ሠናይ ድርጅት ያኔ ሶማሊያ ውስጥ ጠኔ ህፃናት አዋቂውን ሲያንገላታ ሊከሰት የሚችለው አደጋ ከፍተኛ እንደነበር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። ኦክስፋም ዕልቂቱን በወቅቱ መከላከል ተገቢም ብቻ ሳይሆን ይቻል ነበር ብሏል። የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ ዕልቂቱ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ለጋሽ መንግስታት አስፈላጊውን ፈጣን ምላሽ ግን በተገቢው ሠዓት አልሰጡም። ሩዲ ቫን አከን።


«እንደሚመስለኝ የቅድመ ማስጠንቀቂያው በተገቢ ነው የተከናወነው ግን የሚያሳዝነው ምላሹ በጊዜ አልደረሰም።»

ድርቅና ረሐብ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪቃ ቀንድ አገራትን በተደጋጋሚ እንደሚያጠቃ ይታወቃል። በአካባቢዎቹ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የፖለቲካ ጫና ዕልቂቱን ሲያባብሰው እንደሚታይም ተንታኞች በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። ረሐብ ተፈጥሯዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እንከን ውጤት እንደሆነ ኦክስፋም በበኩሉ አስታውቋል። በሶማሊያ ለተከሰተው ረሐብ አፋጣኝ ምላሽ እንዳይሰጥ ሰበብ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል በወቅቱ አብዛኛውን የአገሪቱ ክፍል ተቆጣጥሮ የነበረውና ከአልቃይዳ ጋራ ግንኙነት እንዳለው የሚጠቀሰው አሸባብ የተሰኘው አክራሪ ታጣቂ ቡድን ድርጊት ዋነኛው ነበር ተብሏል።

«በተባበሩት መንግስታት ስር ለሚገኙ ድርጅቶች በአጠቃላይ እንዲሁም መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በአሸባብ ቁጥጥር ስር በሆኑ ቦታዎች ለመስራት አዳጋች ነበር። አብዛኛዎቹ ለጋሽ ድርጅቶች እንደውም ከአገሪቱ ተባረው ነበር።»


ሶማሊያን ለሁለት ዓስርት ዓመት ያዳቀቃት የእርስ በእርስ ግጭት አገሪቱን ከዓለማችን ለሠብዓዊ ርዳታ ተግባር እጅግ አደገኛ ከሆኑ ቦታዎች በዋናነት እንድትፈረጅ አድርጓት ቆይቷል። ከእዚያም ባሻገር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሶማሌያውያን በጎረቤት አገራት በስደት ሲገኙ፤ ሌሎች አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ እዛው ሶማሊያ ውስጥ ተፈናቃይ እንደሆኑ ይታወቃል። የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ እና የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሶማሊያን እንዴት መርዳት እንደሚችል ለመምከር የፊታችን ማክሰኞ ለንደን ውስጥ ጉባኤ ጠርተዋል። ብዙዎች በእዚህ ጉባኤ ረሐብን ጨምሮ በሶማሊያ ለተከሰተው ውጥንቅጥ እልባት ሊያስገኙ የሚችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ይነሳሉ ሲሉ ተስፋ አድርገዋል።

የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ከሠሐራ በስተደቡብ የሚገኙ ሶስት የአፍሪቃ አገራትን ለአምስት ቀናት ከጎበኙ በኋላ አፍሪቃ በተለይ የአፍሪቃውያን ትኩረት እንደሚያሻት ገለፁ። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር «አፍሪቃዊ ችግሮች አፍሪቃዊ መፍትሄዎች» ያሻቸዋል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከደቡብ አፍሪቃዋ አቻቸው ማይቴ ንኮአና ማሻባኔ ጋራ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በተገናኙበት ወቅት ጀርመን ለትብብር ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል። ሆኖም አመራሩ በአፍሪቃውያን መከናወን አለበት ሲሉ አስረግጠዋል። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በተለይ ሶስቱ አገራትን ለምን መጎብኘት እንደፈለጉ የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር ኡልፍ ኤንገል ያብራራሉ።

ጊዶ ቬስተርቬለ ከሞዛምቢክ አቻቸው ኦዴሚሮ ባሎይ ጋራ
ጊዶ ቬስተርቬለ ከሞዛምቢክ አቻቸው ኦዴሚሮ ባሎይ ጋራምስል DW/R.da Silva
የሶማሊያ ረሐብ
የሶማሊያ ረሐብምስል AP
Afrika Hungerkatastrophe Archivbild 2005
ምስል picture-alliance/dpa
ጊዶ ቬስተርቬለ ከደቡብ አፍሪቃዋ አቻቸው ማይቴ ንኮአና ማሻባኔ ጋራ
ጊዶ ቬስተርቬለ ከደቡብ አፍሪቃዋ አቻቸው ማይቴ ንኮአና ማሻባኔ ጋራምስል picture-alliance/dpa


«የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እነዚህን አገራት ለመጎብኘት ሲመርጡ ማሳየት የፈለጓቸው ነገሮች ነበሩ። ከእዚያ በተጨማሪም ለአገራቱ ዕውቅና ለመስጠት በማሰብ ነው። በእነዚህ አገራት የዲሞክራሲ ሂደቱ ቀና በሆነ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ ለማሳየት፣ ብሎም አገራቱ ኢኮኖሚያቸውን በተገቢው መልኩ መምራት እንደቻሉ ግልፅ ለማድረግ በማሰብ ነው ምርጫውን ያደረገው።»

የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቬስተር ቬለ በዲሞክራሲ ጅምራቸው እና በኢኮኖሚ አያያዛቸው አብነት ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉትን ደቡብ አፍሪቃን፣ ሞዛምቢክንና ጋናን ነበር የጎበኙት። በደቡብ አፍሪቃ ቆይታቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከአፍሪቃ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር እንደሚያስፈግ ገልፀዋል። ለትብብሩም የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ብለዋል።

«ምርጥና ዘላቂ የሆነ መልስ ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ነው። የንዋይ ማፍሰስ፣ የንግድ ልውውጥ ማድረግ እንፈልጋለን። ወሳኝ ከሆኑ ሸሪካዎች ጋራ እኩል በሆነ መልኩ የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ወዳጅነት መመስረት እንፈልጋለን።»

ቬስተርቬለ ጋናን በጎበኙበት ወቅት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር የማሊን ቀውስ አንስተው ተነጋግረዋል። ለማሊ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተጨማሪ ወታደሮችን ለመላክ ቃል ገብተዋል። ሆኖም ውሳኔው በመጀመሪያ በጀርመን ፌዴራል ምክር ቤት መፅደቅ እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተዋል። እስካሁን ጀርመን ለልስለጠናና ለሎጂስቲክ ተልዕኮ 330 ወታደሮችን ወደ ማሊ ለመላክ ቃል መግባቷ ይታወቃል። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቬስተር ቬለ ከጋናዊቷ አቻቸው ሐና ቴቴህ ጋራ አክራ ውስጥ በተገናኙበት ወቅት የኢኮኖሚ ትብብር ጉዳይንም አብይ አጀንዳቸው አድርገው ተወያይተዋል።


«ጋና በምዕራብ አፍሪቃ ለእኛ ወሳኝ አገር ናት ስንል የእውነተኛ መረጋጋት መዓከልነቷን በመጥቀስ ነው። ጋና ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት የያዘችውን ጠንካራ አቋም በማወደስ ስኬታማ የኢኮኖሚ እድገቷን በቅርበት እንከታተላለን።»

ከጋና እና ከደቡብ አፍሪቃ ጉዞዋቸው በኋላ ቬስተርቬለ የጎበኙት እምቅ የነዳጅ ሀብት የተጎናፀፈችው ሞዛምቢክን ነበር። ሞዛምቢክ ከግማሽ በላይ ነዋሪዋ እጅግ መራር በሆነ የድህነት አዘቅት ውስጥ የሚማቅቅባት አገር ናት። ቬስተር ቬለ ከሞዛምቢኩ ጠቅላይ ሚንስትር አልቤርቶ ቫኩዊና ጋር በተገናኙበት ወቅት ከሞዛምቢክ ሀብት ደሀውም ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ብለዋል። አፍሪቃ ስኬታማ የምትሆነው ሁሉም ነዋሪዋ ከጥቅሟ እኩል ተካፋይ ሲሆን ነው ሲሉ በእጅ አዙር ለሌሎች በሙስና ለተዘፈቁ የአፍሪቃ አገራት ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

ጊዶ ቬስተርቬለ ጋና አየር ማረፊያ አቀባበል ሲደረግላቸው
ጊዶ ቬስተርቬለ ጋና አየር ማረፊያ አቀባበል ሲደረግላቸውምስል picture-alliance/dpa

ማንተጋፍቶት ስለሺ

መስፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ