1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2006

የሣምንቱ መገባደጃ ከመድረሱ በፊት በነበሩት ጥቂት ቀናት አፍሪቃ ስታነባ ነው መሽቶ የነጋላት። አብዛኛው የዓለማችን ክፍል ግን በሀሴት ተውጦ፣ በደስታ ሲሰክር ሰንብቷል። ዓለም የጎርጎሪዮሳዊውን አዲስ ዓመት ለመቀበል በርችት ዕሩምታና ፍንዳታ ሰማይ ምድሩን አደባልቋል።

https://p.dw.com/p/1Al5T
ምስል picture-alliance/AP
Konflikt zwischen Christen und Muslimen in Zentralafrikanischer Republik 8.12.2013
ምስል picture-alliance/AP

አፍሪቃ በአንፃሩ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በጥይትና በቦንብ ፍንዳታዎች ተንጣ መከረኛ ህዝቧ በእንባና ደም እየታጠበ ነው አዲሱን የጎርጎሪዮሳዊው ዓመት የተቀበለው። ከጎረቤት ሶማሊያና ኬንያ እንጀምራለን።

እንደተዳከመ የተነገረለት ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ያልጠፋው ኧል ሸባብ የተሰኘው እስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድን ጎረቤት ሶማሊያ መቅዲሾ ውስጥ በእዚሁ ሳምንት ውስጥ ነበር የቦንብ ጥቃት ያደረሰው። ጀዘሪያ በተሰኘው ትልቅ ሆቴል ደጃፍ ኧል ሸባብ ሁለት ተከታታይ የቦንብ ፍንዳታ ጥቃቶችን ሰንዝሯል። በጥቃቱ ቢያንስ 11 ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች 18 ሰዎችም መቁሰላቸውን የሶማሊያ ፖሊስ አስታውቋል። የዶቸቬለ የመቅዲሾ ዘጋቢ መሐመድ ዖማር ሁሴን ፍንዳታ የደረሰበትን ቦታ ተመልክቶ በወቅቱ እንደገለፀልን ከሆነ ኧልሸባብ ተዳከመ እንጂ ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም።

«በርግጥ አሸባቦች እንደ በፊቱ ጠንካራ አይደሉም ። ከዚህ ቀደም ይቆጣጠሯቸው ከነበሩት ከዋና ከተማይቱ ከመቅዲሾም ሆነ ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ እየተባረሩ ነው ። ሆኖም አሁን የትግል ስልታቸው ወደ ሽምቅ ውጊያ ተቀይሯል ። እውነቱን ለመናገር አሸባቦች አሁንም አሉ ። በየትኛውም የሶማሊያ አካባቢ በማንኛውም ጊዜ ጥቃት ማድረስ ይችላሉ ። »

ኧልሸባብ የፍንዳታ ጥቃት የሰነዘረበት ከመቅዲሾ ዓለም አቀፍ ዓየር ማረፊያ ብዙም የማይርቀው ሆቴል ውስጥ የሶማሊያ ፖለቲከኞችና የውጭ ሃገራት ባለስልጣናት ተሰብስበው ነበር። እንደ ዓይን ምስክሮች ከሆነ በሽብር ፈጣሪ ታጣቂዎቹ እና የፀጥታ ኃይላት መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። ሆኖም የሶማሊያ ፖሊስ ጥቃት ሰንዛሪዎቹ በርካታ ሰዎችን እንዳይገድሉ ለማድረግ ተሳክቶልናል ሲል ተደምጧል። መሐመድ ዖማር ተጨማሪ አለው።

«የደኅንነት ሚንስትርነትን ደርበው የሚሰሩት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ሚንስትሩ ሁልጊዜም እንዲህ አይነት ነገር ደጋግመው ይናገራሉ። ሆኖም እስከአሁን ድረስ መንግሥት ኧልሸባብን በማንኛውም መንገድ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉ እንደተሳካለት የሚያሳይ ነገር የለም።»

ተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ዒላማ በሆነችው ሌላኛዋ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ውስጥም የቦንብ ፍንዳታ ከትናንት በስትያ ተከስቶ ነበር። በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ቢያንስ 10 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል። የክዋሌ ቀበሌ ኮሚሽነር ኤቫንስ አቾኪ እንደተናገሩት ከሆነ በሞተር ብስኪሌቶች ላይ የተፈናጠጡ ሁለት ሰዎች በደንበኞች ወደተጨናነቀውና ዲያኒ አካባቢ ወደሚገኘው ታንዶሪ ምግብ ቤት ሲከንፉ ታይተዋል። ሞተሩ ተፈትልኮ ከመሰወሩ አስቀድሞ ከሞተረኞቹ አንዱ ወደ ደንበኞች ቦንብ ወርውሯል። ኬንያ ኧልሸባብን ለመውጋት ጦሯን ወደ ሶማሊያ ከላችበት ጊዜ አንስቶ የኧልሸባብ የሽብር ጥቃት ዒላማ ሆና ቆይታለች። ባለፈው መስከረም ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ግዙፍ የገበያ አዳራሽ ላይ በደረሰ የሽብር ጥቃት ቢያንስ 67 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።


ደቡብ ሱዳን ውስጥ የተጫረው የእርስ በእርስ ግጭት አሁንም አልበረደም። መፈንቅለ መንግስት ተዶልቶብኛል በሚሉት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና በቀድሞ ምክትላቸዉ ሪክ ማቻር ታማኞች የተጀመረው ፍልሚያ ባለበት እንደቀጠለ ነው። በሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድናት መካከል አዲስ አበባ ውስጥ ትናንት ድርድር ሲጀመር፤ ጦርነቱ ግን ባለበት እንደቀጠለ ነበር። የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርድሩ መጀመሩን ማረጋገጡን እና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት IGAD ም ለስኬቱ ቁርጠኛ ነዉ ማለቱን ማመልከቱን ዘገባዎች አትተዋል። የሠላም ድርድሩ በተናጠል አዲስ አበባ ላይ ትናንት ሲካሄድ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አስተማማኝ ባልሆነዉ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ተጨማሪ ሠራተኞቹ፤ እንዲሁም እዚያ የሚገኙ ቀሪ ዜጎች እንዲወጡ አሳስቧል።

የፈንጂ ጥቃት በሶማሊያ
ምስል Reuters
የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ስደተኞች
ምስል 2013 Marcus Bleasdale/VII for Human Rights Watch


የደቡብ ሱዳን ግጭትን ለማብረድ ድርድር አዲስ አበባ ውስጥ ሲጀመር መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ የሰፈነው ቀውስ መስመሩን የሳተ ይመስላል። ሴሌካ በተሰኘው በእስላም አማፂያን በሚመራው ታጣቂ ቡድን እና Anti balaka በቀጥተኛ ትርጓሜው ፀረ ቆንጨራ ተብሎ በሚጠራው የክርስቲያን ሚሊሺያዎች መካከል ሀገሪቱ ውስጥ የተጫረው ግጭት የከፋ ደረጃ ላይ ነው የደረሰው። በእዚሁ የጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት በባተበት ሣምንትውስጥ ቢያንስ ሁለት ህፃናት አንገታቸው ተቀልቶ ተገድለዋል። ከሁለቱ ህፃናት መካከል አንደኛው በተጨማሪ ተሰልቦ ነው የተገኘው። ይህ አሰቃቂ ድርጊት በተፈፀመባት መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ባንጉዊ ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የህፃናት መርጃ ድርጅት በምኅፃሩ ዩኒሴፍ ፕሮጄክት ኃላፊ ዣን ሎኬንጋ ከምንም በላይ ተጎጂዎች ህፃናት ናቸው ይላሉ።

«ህፃናት በግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂዎች ናቸው። ህፃናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሸሽ ነበረባቸው። አንዳንዶቹ በታጣቂዎች ተወስደው በጦርነቱ ተሳትፈዋል። አንዳንዶቹ ወደእነሱ በተነጣጠሩ ጥይቶች ወዲያውኑ ተገድለዋል፤ ወይንም ደግሞ በተባራሪ ጥይት ህይወታቸውን አጥተዋል። ሌሎቹ ደግሞ የእነሱን እምነት የሚከተለው ማኅበረሰብ ላይ ጥቃት ለማድረስ በሚፈልጉ ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።»

የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክን ያናጋት እምነትን መሠረት ያደረገ ግጭት እስካሁን ቢያንስ የ1000 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ግጭቱን ፍራቻ ለስደት ተዳርገዋል።

አድማጮች አሁን የመጨረሻው ርዕሳችን ላይ ደርሰናል። ወደ ደቡብ አፍሪቃ ነው የምናቀናው። የሩዋንዳ መንግሥትን በመቃወም የሚታወቁት የቀድሞው የሀገሪቱ የደኅንነት ባለስልጣን በስደት በሚገኙበት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በእዚሁ ሣምንት ተገድለው ተገኝተዋል። ፓትሪክ ካሬጌያ የተባሉት ሰው የሆቴል መኝታ ክፍላቸው ውስጥ ረቡዕ ዕለት ነው ሞተው የተገኙት። የ53 ዓመቱ ሩዋንዳዊ አስክሬን ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ምርመራ የአንገት እብጠት ተገኝቷል። ይህ ምናልባትም ሩዋንዳዊው ስደተኛ የቀድሞ ባለስልጣን የተገደሉት አንገታቸው በገመድ ታንቆ ነው የሚል መላምት አጭሯል። አስክሬኑ በተጋደመበት አልጋ ላይ በደም የተለወሰ ፎጣም ተገኝቷል። የቀድሞ ባለስልጣን ፓትሪክ ካሬጌያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በስደት ኖረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ