1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጥር 17 2006

የደቡብ ሱዳናውያን የተኩስ አቁም ስምምነት 24 ሠዓት ሳይሞላ መወነጃጀሉ ቀጥሏል። ጦርነቱ ማብቃቱን ያበሰረው የተኩስ አቁም ስምምነት ፊርማ ቀለም ገና በቅጡ እንኳን አልደረቀም። የውል ማሰሪያው ቃል ኪዳን ሃያ አራት ሠዓታትም አልሞላው። እንደተፈራው ሁሉ መወነጃጀሉ የጀመረው ሳይውል ሳያድር ነበር።

https://p.dw.com/p/1Awtn
ምስል Reuters

ሐይማኖታዊ ይዘት ተላብሶ ለወራት በዘለቀው የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ የእርስ በእርስ ጦርነት መካከል ሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንትን በጊዜያዊነት ሾማለች። በደቡብ አፍሪቃ ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ መትተዋል። የትኩረት በአፍሪቃ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

ደቡብ ሱዳን፤

ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት አዲስ አበባ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸው ሐሙስ ማታ ተነገረ። አርብ ጠዋት ግን አማፂያኑ በመንግሥቱ ጦር እየተጠቃን ነው ሲሉ አቤት አሉ። የደቡብ ሱዳን መንግሥት አፋጣኝ ማስተባበያ ሰጠ። በተኩስ አቁሙ ስምምነት ፍፁም ለመገዛት መቁረጡን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሐሙስ ማታ ሲገልፅ ግን «እርግጠኞች ነን» በማለት ነበር።

Unterzeichnung Waffenstillstandabkommen für Südsudan in Addis Abeba Äthiopien 23.01.2014
ምስል picture-alliance/dpa

«እንደ መንግስት በእኛ በኩል እርግጠኖች ነን። እኛ ያለን የSPLAጦር ሠራዊት ነው። ይህ ጦር ደግሞ መደበኛ ጦር በመሆኑ በማንኛውም መልኩ ለሚሰጠው ትዕዛዝ ተገዢ ነው። ችግሩ ያለው መደበኛ ባልሆነው ጦር ነው። ስለእዚህ ፍራቻው በመንግሥት በኩል ሳይሆን በሌላኛው ወገን ነው።»

የደቡብ ሱዳን ሪፓብሊክ መንግሥት ቃል አቀባይ ሚካኤል ማኩይ ሉዌዝ ነበሩ መንግስታቸው ለተኩስ አቁሙ ስምምነት ተገዥ እንደሚሆን ከአዲስ አበባ የገለፁት። ሆኖም ንግግራቸው በተደራዳሪ አማፂያን ላይ ሙሉ እምነት እንዳላደረባቸው ጠቋሚ ነበር። በሪክ ማቻር የሚመራውን የአማፂ ቡድን ወክለው ለጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉት ቃል አቀባዩ ማቢዮር ጋራንግ በበኩላቸው ጥያቄያቸው ሙሉ በሙሉ መልስ ባያገኝም ስምምነቱ ጥሩ ነው ሲሉ ገልፀው ነበር ።

«ጥሩ ስምምነት ነው። በእርግጥ የምንፈልገውን መቶ በመቶ ልናገኝበት አንችልም። ከመነሻው ፍላጎታችን ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ እና እስረኞችም በአፋጣኝ እንዲፈቱ ነበር። ሆኖም ያን ብንፈልግም አላገኘንም። በየትኛውም ስምምነት የፈለከውን ምንጊዜም መቶ በመቶ ልታገኝ አትችልም። ስለእዚህ ስምነቱን የግድ መቀበል አለብን።»

በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎችን የፈጀው፣ ከ400 ሺህ በላይ ያፈናቀለና ያሰደደው ጦርነት ማብቃቱን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በፊርማቸው አስረግጠው ሲያውጁ በተስፈኛ ቃላቸውም አስውበው ነበር። የደቡብ ሱዳን ሪፓብሊክ መንግሥት ቃል አቀባይ ሚካኤል ማኩይ ሉዌዝ።

Südsudan Soldaten 14.01.2014 in Juba
ምስል Charles Lomodong/AFP/Getty Images

«ይህ ስምምነት ግድያን፣ የንብረት መውደምን ብሎም መፈናቀልን ለማስቆም የሚያስችል በመሆኑ ለደቡብ ሱዳን ሪፓብሊክ መንግሥትና ሕዝብ ጠቃሚ ነው።»

በአዲስ አበባው ድርድር የአማፂያን ቃል አቀባይ ማቢዮር ጋራንግ በበኩላቸው የሚከተለውን ብለው ነበር።

«በእኛ በኩል ምንጊዜም ቁርጠኞች ነን። ይህ ግጭት የጀመረው እኛ በፓርቲያችን በኩል ለድርድር ጥረት እያደረግን ባለንበት ወቅት ነው። ለውይይት ያደረግነው ጥረት ተበላሽቷል። እናም የሚያሳዝነው እኛ ገና ከመነሻው ጥረት ስናደርግበት ወደነበረው ነጥብ ለመድረስ የበርካታ ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ነው። እኛ ምንጊዜም ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ስንጎተጉት ነው የከረምነው። ስለእዚህ ይህ የስኬታችን ውጤት እንደሆነ ነው የሚሰማን።»

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን በምኅፃሩ ኢጋድ ሸምጋይነት ከሁለት ሳምንታት በላይ የፈጀ የፊት ለፊት ድርድር አድርገዋል። አማፂያኑ የስምምነት ፊርማ ከማስፈራቸው በፊትም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ አሲረዋል ሲሉ ያሰሩዋቸውን 11 ደጋፊዎቻቸውን እንዲፈቱላቸው አማፂያኑ ቅድመ ሁኔታ አቅርበው ነበር።

Konflikt im Südsudan Flüchtlinge 17.01.2014
ምስል Reuters

«የታኅሣስ 18ቱ የኢጋድ ይፋዊ መግለጫ እና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ወደ ቀጣይ ደረጃ የሚሸጋገረውን ድርድር ጠቀሜታ አፅንዖት ይሰጥበታል። እንደሰማነው ከሆነ ቀጣዩ ድርድር የሚጀምረው ጥር 30 ነው። ይህ የሚያሳየው ስምምነቱ በተፈረመበት እና ቀጣዩ ድርድር በሚጀምርበት ጊዜ መካከል ባሉት ቀናት እስረኞቹ እንደሚፈቱ ነው። በተለይ በእዚህ ቀን ነው አይልም። ሆኖም ስምነቱን ብታነበው የተቀመጠው ይሄ ነው። ከመጀመሪያው አንስቶ ትኩረት የሰጠነው መፍትኄ የመሻቱን ጉዳይ ነው። ስለእዚህ ይህ ለእኛ ተስማምቶናል።»

ሐሙስ ማታ አዲስ አበባ ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ስምምነቱ ከተፈረመ ከ24 ሠዓታት በኋላ የሚፈጠር ማንኛውም ግጭት ውሉን በምንም መልኩ ማበላሸት እንደሌለበት ያስጠነቅቃል። ሆኖም የደቡብ ሱዳን መንግሥት በነዳጅ ይዞታዋ የበለፀገችው የዩኒቲ ግዛትና ጆንግሌ ውስጥ ትናንት አርብ ጥቃት መሰንዘሩን አማፂያን ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት አስተባብሎዋል። ቃል አቀባዩ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በአዲስ አበባው ንግግራቸው እንዲህ ሲሉ ነበር ቃል የገቡት።

«ራሳችንን ከባላንጣነት ለማቀብ ውል የገባን ስለሆነ እንደመንግሥት ለውሳኔው ሙሉ በሙሉ እንደምንገዛ አረጋግጣለሁ። ያም በመሆኑ ሕዝባችን ኑሮውን በሠላም መግፋት ይችላል።»

የግጭቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ዛሬም በስጋት ውስጥ ነው ያለው። በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተፋላሚ ኃይላት መካከል የቃላት እንጂ የተግባር ስምምነት ለጊዜው እውን የሆነ አይመስልም።

በጎሣ ተከፋፍለው የሚጠዛጠዙት ደቡብ ሱዳናውያን ባሳለፍነው ሐሙስ የተኩስ አቁም ውል ሲፈርሙ፤ ሐይማኖታዊ ግጭት ባዳቀቃት የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ ደግሞ ሴት ፖለቲከኛ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰይመዋል።

Catherine Samba-Panza Zentralafrikanische Republik 20.01.2014 Bangui
ፕሬዚዳንት ካትሪን ሣምባ-ፓንዛምስል Eric Feferberg/AFP/Getty Images

እጅግ የተወሳሰበ ሠብዓዊ ቀውስ ባጠላባት እና ሐይማኖታዊ ግጭት ባቆረቆዛት የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሐሙስ ዕለት የሀገሪቱ ርዕሠ-ብሔር ሆነው የተሾሙት ካትሪን ሣምባ-ፓንዛ ይባላሉ። የ59 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው። ፓንዛ ስልጣኑን የተረከቡት በቅርቡ ሥልጣን የለቀቁት የቀድሞው አማፂያን መሪ ሚካኤል ጆቶዲያን ተክተው ለቀናት የሀገሪቱ ተጠባባቂ ርዕሠ-ብሔር ሆነው ከተሰየሙት የሽግግር ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አሌክሳንደር ፈርዲናንድ ንጉዌንዴት ነው።

ቀድሞ የአማፂያን መሪ እና የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሚካኤል ጆቶዲያ ሀገሪቱን በቅጡ ማስተዳደር ተስኗቸዋል በሚል ነው በዓለም አቀፍ ግፊት ከስልጣን የተነሱት። ጆቶዲያ በዋናነት ሙስሊም አማፂያን በሚበዙበት የሴሌካ ጥምረት ተደግፈው ነበር የሀገሪቱ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንሷ ቦዚዚን የዛሬ አስር ወር ግድም አስወግደው ስልጣን የተቆናጠጡት።

ከእዚያን ጊዜ አንስቶም የእስልምና እምነት በሚከተሉ የሴሌካ ጥምረት እና በክርስትያን ሚሊሺያዎች በተዋቀረው «ፀረ ቆንጨራ» በተሰኘው ቡድን መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት መካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ ለወራት ስትታመስ ከርማለች። 10 ወራት ባስቆጠረው ግጭት ርዕሠ-ከተማ ባንግዊ ውስጥ ብቻ ከ1,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሎዋል። 100,000 የባንጉዊ ነዋሪ በመዲናዋ ዓየር ማረፊያ ውስጥ እና በአካባቢው የፈረንሳይ ወታደሮችን ተገን አድርጎ ተጠልሎዋል።

ፕሬዚዳንት ካትሪን ሣምባ-ፓንዛ በክርስትያን እና ሙስሊም ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቷ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ነፃ የሆኑ ሴት እንደሆኑ የሚነገርላቸው በመሆኑ በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይላት ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነትንያገኛሉ ተብሏል። በሀገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሣይም ከወዲሁ ይሁንታን ያገኙ ናቸው። ካትሪን ሣምባ ፓንዛ በበኩላቸው የፈረንሣይን ሚና አወድሰው ተናግረዋል። «ያለፈረንሣይ ጦር ጣልቃገብነት ሀገሪቱ ዛሬ የት ላይ ትገኝ እንደነበረ እንጃ። ለፈረንሣዮች ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው።» ሲሉ ተደምጠዋል።

Zentralafrikanische Republik Interimspräsidentin Catherine Samba-Panza 23.01.2014
ምስል Reuters

የመካከከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ካትሪን ሣምባ -ፓንዛ ወደፊት በሚያዋቅሩት መንግስት ውስጥ የሀገሪቱን እጅግ ዘግናኝ ሐይማኖታዊ ግጭት መቅረፍ የሚችሉ አባላትን እንደሚያካትቱ ቃል ገብተዋል።

ከማዕከላዊ አፍሪቃ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስንመለስ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማዕድን ሠራተኞች አድማ መምታቸውን እንመለከታለን። ደቡብ አፍሪቃ ሩስተንበርግ ውስጥ እጅግ ግዙፍ በሆኑት ሶስት የፕላቲኒየም ማዕድን ማውጫ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ በመጠየቅ የመቱት የስራ ማቆም አድማ ትናንት አርብ ሁለተኛ ቀኑን ይዞ ነበር።

ፖሊስ እንደገለፀው ከሆነ አድመኞቹ መንገዶችንና መግቢያ በሮችን በመሰናክል ዘግተው ቆይተዋል። አንግሎ አሜሪካን ፕላቲኒየም የተሰኘው የማዕድን ማውጫ ኩባንያ በማዕድን ሠራተኞቹ አድማ ሰበብ 10 በመቶ ተፅዕኖ ያረፈበት በመሆኑ ኩባንያው 9 ሚሊዮን ዶላር ግድም ማጣቱን ገልጿል።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት የማዕድን ኩባንያ ሠራተኞች የጠሩትን የስራ ማቆም በተለይም የተቃውሞ ሠልፍ ለመበተን ፖሊስ በከፈተው ተኩስ በርካቶች መገደላቸው ይታወሳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ