1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 18 2007

የኢቦላ ስርጭት በምዕራብ አፍሪቃ የረሀብ አደጋም ደቅኗል። የምክር ቤት አባላትን ያቧቀሰው የኬንያ አዲሱ ፀረ-ሽብር ሕግ እንዲታገድላቸው ተቃዋሚዎች ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤት ብለዋል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ድርድር ዳግም ከተጨናገፈ ተፋላሚዎቹ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1EAQi
Sierra Leone Ebola
ምስል REUTERS/Baz Ratner

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን፤ ልጅ አዋቂ ሳይል እንደ ቅጠል አርግፏል፤ ኢቦላ። በምዕራብ አፍሪቃ ሦስት ሃገራት በተለይም በሴራሊዮን፣ ጊኒ እና ላይቤሪያ ተሐዋሲው ከ7,500 በላይ ሰዎችን እያጣደፈ ገድሏል። ከጨቅላ ህፃናት አንስቶ እጅግ እስከተከበሩ የሴራሊዮን ሐኪም ድረስ በተገቢው ሕክምና እጦት የተነሳ በርካቶች በአፍሪቃ ምድር ግብዓተ-መሬታቸው ተፈጽሟል። ብዙ አወዛጋቢ እና አስተዛዛቢ ክስተቶች የተስተዋሉበት የኢቦላ ወረርሽኝ የሃገራቱን ምጣኔ ሀብት አንኮታኩቶ የረሀብ አደጋም እንደጋረጠ ተነግሯል። የጀርመን መራሒተ-መንግሥት የአፍሪቃ ልዑክ፥ ጉይንተር ኑክ

«በእርግጥም መጠነኛ የምጣኔ ሀብት እድገቱን ሠንጎ የያዘ አዲስ ሳንካ ተጋርጧል። ወረርሽኙ የፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ሃገራቱ መገለል ስለደረሰባቸው በከፍተኛ ደረጃ ተጎድተዋል። እንደ አዲስ ከታች መጀመር ሊኖርባቸው ነው። በዛ ላይ በምዕራብ አፍሪቃ የረሀብ አደጋ ማንዣበቡ ተረጋግጧል።»

የኢቦላ ተሐዋሲ በተዛመተባቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት፤ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ለረሃብ ሊጋለጥ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት ቀደም ብሎ ነው ያስታወቀው። የረሀቡ ሰበብ ደግሞ የወሰኖች መዘጋት፣ ሕሙማን ተገልለው እንዲሠፍሩ መደረጉና አዝመራ በወቅቱ ያለመሰብሰቡ ነው ተብሏል።

ኢቦላ በሴራሊዮን፤ አንዲት ልጅ በፍሪታውን ከተማ
ኢቦላ በሴራሊዮን፤ አንዲት ልጅ በፍሪታውን ከተማምስል Reuters/R. Ratner

ይኽ በእንዲህ እንዳለ በሴራሊዮን ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር የኢቦላ ስርጭትን ለመግታት በሚል ወደ አካባቢው መግባት እና መውጣት መታገዱ ትናንት ተሰምቷል። በተለይ ለጎርጎሪዮሣዊው አዲስ ዓመት እና ለገና ሰሞን በሴራሊዮን ሰሜናዊ ክፍል ሰብሰብ ብሎ መገኘት መከልከሉም ተዘግቧል። በሌላ ዜና ደግሞ አውሮጳውያን የኢቦላ ተሐዋሲን በተመለከተ ጠንከር ያለ ውሳኔ ካላሳለፉ ከፍተኛ ጉዳት ሊከተል እንደሚችል አንድ የህክምና ተማራማሪ ተናግረዋል። አውሮጳ ኢቦላን «የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት» ብላ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ካልቆጠረችው «ለጉዳት ትጋለጣለች» ብለዋል የንዑስ ተሐዋስያን ጥናት ተማራማሪው ፔተር ፒዮት። እኚኽ ተመራማሪ የኢቦላ ተሐዋሲን በቤተ-ሙከራ እንዳገኙት ይነገርላቸዋል።

የኢቦላ ተሐዋሲ ግኝት እና በሙከራ ላይ ያሉ መድሐኒቶች ጉዳይ ሲነሳ በአሳዛኝ ሁናቴ በተሐዋሲው የሞቱት ሴራሊዮናዊ ሐኪም ይታወሳሉ። ዶክተር ሼክ ኡማር ካን በተሐዋሲው የተጠቁ ሰዎችን ለማከም ሲታትሩ እሳቸውም የተሐዋሲው ኃያል በትር ያረፈባቸው ሐኪም ናቸው። ዶክተር ሼክ ኡማር ሲያክሟቸው እንደነበሩ ኅመምተኞች እሳቸውም በሐምሌ ወር መባቻ አልጋ ለመያዝ ይገደዳሉ። አብረዋቸው የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጋ ሐኪም ባልደረቦቻቸው ግን ያኔ በወቅቱ በሰው ልጅ ላይ ሙከራ እንዳልተደረገበት የተነገረለትን Zmapp የተሰኘ መድሐኒት በእጃቸው ይዘው ነበር። መድሐኒቱን ለባልደረቦቻቸው ያቀበሉት የካናዳ የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው። የካናዳ የሕክምና ቡድን የጊኒ ድንበር ላይ በሚገኝ የኢቦላ ተሐዋሲ ቤተ-ሙከራ ምርምር ያደርግ እንደነበር ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ከወራት በፊት መግለጡ ይታወሳል።

በኢቦላ የሞቱት ሴራሊዮናዊው ሐኪም ሼክ ዑማር ካህን
በኢቦላ የሞቱት ሴራሊዮናዊው ሐኪም ሼክ ዑማር ካህንምስል Reuters

ሴራሊዮናዊው ሐኪም ስለሙከራ መድሐኒቱ አንዳች የሚያውቁት ነገር የለም። አልጋ ላይ ግን ያጣጥሩ ነበር። ሐኪሞቹም ከሴራሊዮኗ ምሥራቃዊ ክፍለሀገር እስከ ስዊትዘርላንዷ ጄኔቫ በስልክ ይወያያሉ። የሙከራ መድሐኒቱን እንስጣቸው አንስጣቸው? እያሉ ነበር የሚሟገቱት። መድሐኒቱን ላለመስጠት ካስወሰኑ ምክንያቶች አንዱ ሰው ላይ ባልተሞከረው መድሐኒት የተነሳ ምናልባት ሴራሊዮናዊው ሰውነታቸው ተቆጥቶ ቢሞቱስ የሚል እንደነበር በወቅቱ ተጠቅሷል። ሴራሊዮናዊውን ሐኪም ግን ሙከራው እንዲደረግባቸው አልጠየቋቸውም። ሐኪሙ ብዙም አልቆዩ። በ7ኛ ቀናቸው ያርፋሉ።

በሚደንቅ ሁናቴ ግን በቀጣዩ ቀን ላይቤሪያ ውስጥ ለሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ላላቸው የሕክምና አባላት ሰው ላይ አልተሞከረም የተባለው መድሐኒት ይሰጣቸዋል። ኹለቱ ሰዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተወስደውም ሙሉ ለሙሉ ድነው ከሐኪም ቤት መውጣታቸው ይታወሳል። ሌላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀና አንድ ላይቤሪያዊ በኢቦላ ተሐዋሲ ተሰቃይቶ የሙከራ መድሐኒቱ ሳይሰጠው መሞቱም ተዝግቧል። እነዚህ ክስተቶች በርካቶች በኢቦላ ተሐዋሲ ስርጭት እና መከላከል ዘርፍ ነገሮችን በጥርጣሬ እንዲያዩ ካደረጉ ነጥቦች ጥቂቶቹ ናቸው። የጀርመን መራሒተ-መንግሥት የአፍሪቃ ልዑክ፥ ጉይንተር ኑክ የኢቦላ ስርጭት መቀነሱ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

«ቀደም ሲል ከታየው የበለጠ ስኬት እናስመዘግባለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የተሐዋሲው የመሰራጨት ፍጥነት እጅግ በጣም ቀንሷል።»

የተሐዋሲው ስርጭት በቅርቡ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚችል የተመድ ዋና ጸሓፊ ባን ኪሙንም ተጠንቅቀው መናገራቸው ተዘግቧል።

አወዛጋቢው አዲሱ ፀረ-ሽብር ሕግ

የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አዲሱ ፀረ-ሽብርሕግ እንዲታገድላቸው ተቃዋሚዎች ያቀረቡትን አቤቱታ ረቡዕ ዕለት ውድቅ አድርጎታል። ተቃዋሚዎች አዲሱ ሕግ ውድቅ እንዲሆን አቤቱታ ያቀረቡት የሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል በሚል ነው። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ኢሣቅ ሌናኦላ መንግሥት ተቃውሞ ለቀረበበት የሕግ ጥያቄ መከራከሪያውን ለማቅረብ ዕድል ሊሰጠው ይገባዋል ብለዋል። አዲሱን ሕግ በመቃወም ፍርድ ቤት አቤት ያለው ቅንጅት ለለውጥ እና ለዲሞክራሲ የተባለው የኬንያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ ነው።

የኬንያ የምክር ቤት አባላት በከፊል
የኬንያ የምክር ቤት አባላት በከፊልምስል Reuters/T. Mukoya

የኬንያ መንግሥት አዲሱን ሕግ ያረቀቀው ከአሸባሪዎች የሚደርስበትን ጥቃት ለመዋጋት እንዲረዳው መሆኑን ጠቅሷል። አሸባብ የተሰኘው የሶማሊያው አሸባሪ እስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድን ከአንድ ዓመት በፊት በኬንያ ባደረሰው የሽብር ጥቃት ቢያንስ 67 ሰዎች ተገድለዋል። የኬንያ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ዳይሬክተር ዩሱፍ ሉሌ፤ ኬንያ በአሁኑ ጊዜ የፀጥታ ስጋት ቢኖርባትም ጨቋኝ ሕጎችን በማፅደቅ ያንን ማስቀረት አይቻልም ነው ያሉት።

«ይህ ሕግ የተረቀቀዉ ሀገሪቱ ከፀጥታ አኳያ በሚሊዮን የሚገመቱ ፈተናዎችን በተጋፈጠችበት ወቅት ነዉ። ላለፉት 12 ወራት ማለት እችላለሁ ክፉኛ ባለመረጋጋት ሁኔታ ተመትተናል። እነዚህ አለመረጋጋቶች ደግሞ በሽብርተኝነት፣ በፅንፈኝነትና በአክራሪነት የሚፈረጁ ናቸዉ። እንደአንድ ኅብረተሰብ ወይም እንደተቋም የፀጥታ ስጋት ችግር እጅግ ጨቋኝ ሕጎችን በማፅደቅ ይፈታል ብለን አናምንም።»

አዲሱ የጸረ-ሽብር ሕግ ከመፅደቁ አስቀድሞ የኬንያ መንግሥት፤ ሽብር ፈጠራን በገንዘብ ይደግፋሉ ያላቸውን 15 ቡድኖች ጨምሮ ባጠቃላይ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች በሕግ የተመዘገቡትን ደንብ ሽሯል። ታዛቢዎች በበኩላቸው መንግሥት በደሕንነት ጥበቃ ስም ፣ ሒስ አቅራቢዎችን ሁሉ ፀጥ ለማሰኘት ነው የተነሣሣው በማለት በመንቀፍ ላይ ናቸው። ከ 500 በላይ ከሆኑት የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች ምን ያህሉ በቀጥታ ከሽብር ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው እንደተጠረጠሩ ወይም በገንዘብ ረገድ እስከምን ድረስ እንደሚደግፉ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

የኬንያ ፖሊሶች የኬንያ ምክር ቤት ግቢ
የኬንያ ፖሊሶች የኬንያ ምክር ቤት ግቢምስል picture-alliance/AP Photo/Ben Curtis

በኬንያ የፀረ-ሽብር ሕግ መሠረት ጋዜጠኞች ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የምርመራ ውጤቶችን አንኳሰው ከዘገቡ እንደሚያስቀጣቸው ተጠቅሷል። ያለፖሊስ ፍቃድ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ምስል ማውጣትም እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል ተብሏል። ተቃዋሚዎች የጸረ-ሽብር ሕጉ የሰብዓዊ መብቶችን ከመደፍለቁም ባሻገር ኬንያን ወደ አምባገነን አስተዳደር ይገፈትራታል ብለዋል።

የሕግ ረቂቁ ለኬንያ ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ክርክር ከማስነሳቱም በላይ በጡጫ እስከማቧቀስም መድረሱ ተነግሮለታል።በክርክሩ ወቅት የነበሩ በርካታ የምክር ቤት አባላት በመጠኑ መቁሰላቸውም ተሰምቷል።

እልባት ያልተገኘለት የደቡብ ሱዳን ግጭት

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በአዲስ አበባ እጅግ ውድ ዋጋ በሚከፈልባቸው ዘመናይ ሆቴሎች ውስጥ በተደጋጋሚ የሠላም ንግግሮችን አድርገዋል። በዛው መጠን ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርጉም፤ ስምምነቶቹ በሠዓታት ልዩነት ሲጣሱም ተስተውለዋል። ተፋላሚዎቹ የጀመሩት የሠላም ንግግር በጎርጎሪዮሣዊው የገና በዓል ምክንያት መቋረጡ ተዘግቧል፤ ጦርነቱ ግን አልሰከነም። የሠላም ንግግሩ ከከሸፈ ተፋላሚ ኃይላቱ ማዕቀብ እንደሚጠብቃቸው ድርድሩ ከሚካሄድበት ከአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ባሳለፍነው ሰኞ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥትን እና ተፋላሚዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት በምኅፃሩ ኢጋድ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁ ይታወቃል።

የኢጋድ አባል ሃገራት ሠንደቅ ዓላማዎች
የኢጋድ አባል ሃገራት ሠንደቅ ዓላማዎችምስል Yohannes G/Eziabhare

የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን የቀጣናው ሃገራት ማዕቀብን እንደማስፈራሪያ እየተጠቀሙበት ነው ይላሉ። አንዳንድ ተንታኞች የአካባቢው ሃገራት በደቡብ ሱዳን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጠዋል።

በደቡብ ሱዳን ግጭት ከፈነዳ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር የያኔው ምክትላቸው ሪይክ ማቻር መፈንቅለ-መንግሥት ሊያኪያሂዱብኝ ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነበር ግጭቱ የተቀሰቀሰው። ከዛን ጊዜ አንስቶም 44 ,000 ነዋሪዎች በመዲናዋ ጁባ የተመድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። ከ1,9 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ከቀዬያቸው እንደተፈናቀሉ ይጠቀሳል። በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነቱ የተነሳ እንዳለቁ ይነገራል። ዓለም አቀፉ የቀውስ ተንታኝ ቡድን በደቡብ ሱዳን ግጭት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ50,000 ቢባዛ እንጂ አያንስም ይላል። ይኽ ሁሉ ሲሆን ግን ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃነቷን ካወጀች ገና ሦስት ዓመትም አላለፋት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ