1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

እሑድ፣ መስከረም 3 2002

የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ በእንግሊዘኛ ምህፃሩ SADC የሁለት ቀናት ጉባኤውን ባሳለፍነው ረቡዕ አጠናቋል። ሳዴክ ማዳጋስካርን አስመልክቶ በስፋት የመከረ ሲሆን፤ የዚምባብዌ ጉዳይን ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ ሊመለከት በቀጠሮ ማስተላለፉ ታውቋል። የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታና የጋዜጦች አምድም በዝግጅታችን ተካተዋል።

https://p.dw.com/p/Je4A
ሙጋቤ ላይ የተጣለው ማዕቀብ
ሙጋቤ ላይ የተጣለው ማዕቀብምስል AP

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማን ጨምሮ የሳዴክ አባል ሀገራት የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ የተቻላቻቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። የአውሮፓ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንትን የምትመራው ስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር በበኩላቸው የአውሮጳ ህብረት በሮበርት ሙጋቤ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት እንዳልተዘጋጀ ገልጸዋል።

የሮበርት ሙጋቤ አፈ ቀላጤ ጆርጅ ቻራምባ በበኩላቸው ባለፈው ረቡዕ ለአልጀዚራ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሳዴክ ለራሱ ሲል በዚምባብዌ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማስነሳት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።

እንግዲህ ሳዴክ ራሱ አሜሪካውያንን፣ አውሮፓውያንን፤ ዚምባብዌ የድርጅታችን ማዕከላዊ አባል ናት የማለት መብት አለው። በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ዚምባብዌ ባሳዴክ በራሱ እምብርት ውስጥ ነው ያለችው። እነዚያን መሰል ፍትህ አልባና ሀገ ወጥ ዕቀባዎችን መጫን በመቀጠል ሳዴክን ትጎዳለህ። እባካችሁ ያን በማስወገድ ውለታ ዋሉልን

ብሪታንያና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሙጋቤና ዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች ላይ የበረራ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወቃል። ከዚያም ባሻገር አውሮፓውያኑ ሙጋቤን ጨምሮ በነዚሁ ግለሰቦች ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም የባንክ ዝውውር አግደው እንደያዙ ቆይተዋል።

የስዊድኑ ጠቅላይ ሚንስትር ፍሬድሪክ ራይንፌልድት አርብ ከፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ «በዚምባብዌ ላይ ያደረግነውን እገዳ ለማንሳት የአውሮጳ ህብረት ዝግጁ እንዳልሆነ ግልፅ ለማድረግ እፈልጋለሁ» ሲሉ በሙጋቤ ላይ የተጣለው እገዳ ገና ቀጣይ መሆኑን አስረግጠዋል። ውጤቱ ዚምባብዌ በዓለማችን ወደር ያልተገኘለት የዋጋ ግሽበት ክፉኛ የመታት ሀገር እንድትሆን ከማድረጉም ባሻገር ሀገሪቱ በምጣኔ ሀብት እንድትንኮታኮት አድርጓል። አውሮፓውያኑ ለማዕቀብ ተግባራቸው ምንጩ ሙጋቤ እ.ኤ.አ. በሁለት ሺህ ሁለት ያካሄዱት ምርጫ ጫና የበዛበት የነበረ ከመሆኑም በላይ የሰብዓዊ ጥሰት በሀገሪቱ የተንሰራፋ በመሆኑ እንደሆን ይጠቅሳሉ።

ሳዴክ ባለፈው ረቡዕ በቋጨው የሁለት ቀናት ጉባኤው ማዳጋስካርን ከሳዴክ አባልነት ያባረረበት ተግባሩን አሁንም እንዳፀና ጠቅሷል። የማዳጋስካሩ የሰላሳ አምስት ዓመቱ ወጣት ፕሬዚዳንት አንድሬ ራጆሊና ለፕሬዚዳንትነት የበቁበት ሁናቴ ከማዳጋስካር ህገ መንግስት ውጪ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ሳዴክ በድጋሚ አፅንኦት ሰጥቷል። በሳዴክ ጉባኤ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌቴን ወክለው የተገኙት የታንዛንያዊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በርናርድ ሜምቤ ማዳጋስካርን በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል።

የማዳጋስካር ቀውስ ገና በመጋቢት ወር ሲጀምር፤ የሳዴክ ማህበረሰብ ተገናኝተው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። ያም ከምንም በላይ የአንድሬ ራጆሊና መንግስት በህዝብ የተመረጠውን መንግስት በመጣሉ ሳዴክ ዕውቅና አይሰጠውም የሚል ነው። በሁለተኛ ደረጃ አንድሬ ራጆሊና በመንግስት አስተዳደር ሊቀመጥ አይፈቀድለትም፤ ምክንያቱም የማዳጋስካር ህገ መንግስት በግልፅ እንዳስቀመጠው አንድ ፕሬዚዳንት ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ መሆን አለበት። እሱ ሰላሳ አምስት ዓመቱ ነው። ህገ መንግስቱን የመጣስ እና በህብ የተመረጠን መንግስትና ፕሬዚዳንት መጣል ከዕድሜው ጋር ተያይዞ ሳዴክ አስተዳደሩን ዕውቅና እንዳይሰጥ ከማድረጉም በላይ ሀገሪቱ ባስቸኳይ ወደ ህገመንግስታዊ ስርዓት እንድትመለስ ጠይቋል። ሳዴክ በተጨማሪ እነዚህ ሰዎች ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይገባል ብሏል። የማዳጋስካር አስተዳደር ባጠቃላይ ማዕቀብ ሊጣልበት ይገባል።

በደሴታማዋ ሀገር ማዳጋስካር በብዙዎች ዘንድ ህገ ወጥ የተሰኘው የስልጣን ሽግግር ከተከናወነ ስድስት ወራትን የስቆጠረ ቢሆንም፤ በሀገሪቱ አሁንም ድረስ የፖለቲካ ትኩሳቱ እንዳልበረደ ታውቋል። ዓለም አቀፍ አራዳሪዎች ወጣቱ የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት በሀይል ካስወገዷቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከዛ በፊት ከነበሩ ፕሬዚዳንቶች ጋር የስልጣን መጋራት ድርድር እንዲካሄድ ጥረት ሲያደርጉ ሰንብተዋል። እንደዓለማቀፍ አራዳሪያኑ ምኞት ከሆነ እ.ኤ.አ. በሁለት ሺህ አስር ላይ በማዳጋስካር አጠቃላይ ህዝባዊ ምርጫ እስኪካሄድ ግድ ይላል። እስከዚያው ድረስ ታዲያ ወጣቱ አንድሬ ራጆሊና የፕሬዚዳንትነቱን እና የጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ቦታዎችን ከቀድሞ ፕሬዚዳንቶቹ ጋር በመጣመር እንዲካፈሉ የሚጠይቅ ነበር። ያ ተግባራዊ ባለመሆኑም ሳዴክ በጉባኤው ማዳጋስካርን ከአባልነት እንደሰረዛት መፅባቱን አስታውቋል። በአንጻሩ ፕሬዚዳንት አንድሬ ራጆሊና ሀገራችን ካሁን በኋላ ያለ ልገሳ መዝለቅ መቻሏ ይደንቀኛል። የሀገሪቱን ዕዳ ባጠቃላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶቿ ይዘው ሄደዋል ሲሉ መሳለቃቸው የሚታወስ ነው።


MS/GT/YH