1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻድ እና ፀረ ቦኮ ሀራም ርምጃዋ

ማክሰኞ፣ ጥር 12 2007

ካሜሩን አሸባሪው ቡድን ቦኮ ሀራም በናይጀሪያ አጠናክሮ የቀጠለው ጥቃት ዒላማ ከሆነች ሰንበት ብሏል። ቡድኑ ያን ያህል ጥበቃ የማይደረግበትን ሁለቱን ሀገራት የሚያዋስነውን ድንበር እየተሻገረ የእገታ እና የኃይል ተግባሩን አስፋፍቶዋል።

https://p.dw.com/p/1ENLw
Soldaten aus dem Tschad
ምስል AFP/Getty Images/M. Medina

የናይጀሪያ መንግሥት የቦኮ ሀራምን ጥቃት ለማብቃት በሰሜናዊ የሀገሩ አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ ቢያውጅም፣ ይኸው ቡድን ባለፉት ሳምንታትም በሀገሩ እና በጎረቤት ካሜሩን በርካታ መንደሮችን አጥቅቷል። የናይጀሪያ ጎረቤት ሀገራት እና የአውሮጳ ህብረት በዚሁ አሳሳቢ ሂደት አንፃር ሊያደርጉት ስለሚችሉት ጉዳይ በሚንስትሮች ደረጃ ለመምከር ዕቅድ የያዙ ሲሆን፣ ቻድ ወታደሮችዋን እና ታንኮችዋን በወቅቱ ወደ ካሜሩን ልካለች። ይህ ዓይነቱ ርምጃ የቦኮ ሀራምን የኃይል ተግባር ያበቃል አያበቃም የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ካሜሩን የቦኮ ሀራምን ጥቃት ለመከላከል በጀመረችው ጥረቷ ላይ ርዳታ ማግኘቷ ተሰምቶዋል። በዚሁ መሰረትም፣ ለዓለም አቀፍ ውዝግቦች መፍትሔ የሚሻው «ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ» የተባለው ቡድን የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ ኮምፈርት ኤሮ እንዳስታወቁት፣ የመጀመሪያዎቹ የቻድ ወታደሮች ካሜሩን ገብተዋል።
« የቻድ ጦር ወደ ካሜሩን በመግባት ላይ ይገኛል። የቻድ ወታደሮች እና ታንኮች በሳምንቱ መጨረሻም ካሜሩን እንደሚገቡ የተሰማበትን ዜና ካሜሩናውያኑ በደስታ ተቀብለውታል። እና በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን ለማወቅ ሙከራ በማድረግ ላይ ነን። »

የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ ለፈረንሳይ ጋዜጣ « ላ ክሯ» በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በሳምንቱ መጨረሻ 400 ተሽከርካሪዎች የሚገኙበት አጀብ፣ እንዲሁም፣ ሄሊኮፕተሮች ወደ ካሜሩን መላካቸውን አስታውቀዋል። ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ሰሜናዊ ናይጀሪያን እያጠቃ ያለው እና ባለፈው ሚያዝያ ወደ 300 የሚጠጉ ልጃገረድ ተማሪዎችን ያገተው አሸባሪው የቦኮ ሀራም ቡድን ባለፈው እሁድ ከናይጀሪያ ጋር በሚያዋስነው የካሜሩን ድንበር የሚገኙ በርካታ መንደሮችን አጥቅቶ ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎችን ማገታቸውን ያይን ምስክሮች ለዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ሞኪ ኪንድዜካ ገልጸዋል።
« ቤት ለቤት እየገቡ ያገኙዋቸውን ሴቶች እና ሕፃናትን በጠቅላላ በኃይል ወስደዋል። ያካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ከ60 እስከ 80 የሚጠጉ የቤተሰብ አባላት በናይጀሪያው አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሀራም ታግተዋል። »

የካሜሩን ጦር በዚሁ በካሜሩን ምድር እስካሁን ከተካሄዱት የቦኮ ሀራም ጥቃቶች ሁሉ እጅግ አስከፊው ባለው ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ብዙዎች መገደላቸውን ገልጾዋል። ጦሩ ከታጋቾቹ መካከል አንዳንዶቹን ማስለቀቅ ቢችልም ፣ ብዙዎቹ ግን ወደ ናይጀሪያ መወሰዳቸውን አመልክቶዋል።
ቦኮ ሀራም ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በሰሜናዊ ናይጀሪያ ባስፋፋው ሽብር ቢያንስ 13,000 ሰዎች ሲገደሉ፣ 1,5 ሚልዮን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ወይም ተሰደዋል። አሸባሪዎቹ ጥቃታቸውን፣ ከናይጀሪያ ጋር 500 ኪሎሜትር ርዝመት እና የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ሞኪ ኪንድዜካ እንደሚለው፣ ጥብቅ ቁጥጥር የማይደረግበት ድንበር ወደምትጋራዋ ወደ ጎረቤት ካሜሩንም አስፋፍተዋል። የቦኮ ሀራም አባላት ድንበሩን በቀላሉ በመሸጋገር የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት፣ እግ,ታ እና ግድያ ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል። በዚህም የተነሳ፣ ይላሉ ሁኔታውን ከናይሮቢ በመከታተል ላይ የሚገኙት «ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ» የተባለው ቡድን የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ ኮምፈርት ኤሮ፣ የቻድ እና የካሜሩን ጦሮች ድንበሩን በጋራ ለመቆጣጠር ወስነዋል።
« የቻድ ጦር ባሸባሪ ቡድን ዓማፅያን አንፃር በጣም የተሳካ ርምጃ በመውሰዱ ይታወቃል። እንደሚታወሰው ፣ ጦሩ ወደ ማሊ በመሄድ በዚያ በሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን አንፃር በተካሄደው የጥቃት ዘመቻ ላይ እንዲተባበር ተጠይቆ ነበር። የቻድ ጦር ጠንካራ እና ቀልጣፋ መሆኑ ነው የሚነገርለት።
ይሁንና፣ ቻድ ብቻዋን የቦኮ ሀራምን ጥቃት ማብቃት እንደማትችል ያስታወቁት የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ ያካባቢ ሀገራት በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ድርጅት፣ ኤኮዋስ መሪነት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። የካሜሩን ፕሬዚደንት ፖል ቢያ ቀደም ባሉ ጊዚያት ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ ሳያገኙ ቀርተዋል። እርግጥ፣ የኤኮዋስ አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት እአአ ግንቦት 2014 ዓም በፓሪስ ባካሄዱት ፀረ ሽብርተኝነት ጉባዔ ላይ ለመተባበር ዝግጁነት ቢያሳዩም፣ እስከዛሬ ፣ ናይጀሪያ በማመንታቷ፣ አንድ ልዩ ያካባቢ ቡድን አልተቋቋመም። ለዚህም በሀገራቱ መካከል ያለው አለመተማመን ምክንያት መሆኑን ኮምፈርት ኤሮ ቢገልጹም፣ ይህ እየተለወጠ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
« በነዚህ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ። ግን፣ አሁን ቦኮ ሀራም ባካባቢው ጥቃቱን እያጠናከረ በመምጣቱ ሀገራቱ እርስ በርስ ሊተባበሩ እንደሚገባ እየተረዱት ሳይመጡ አልቀረም። »
እንደሚታወቀው ፣ ፅንፈኛውን ቦኮ ሀራምን በተመለከተ፣ በተለይ፣ ቡድኑን ማን ይረዳል፣ ማንስ ፀረ ሽብር ጥቃት ያካሂዳል በሚለው ጥያቄ የተነሳ በናይጀሪያ፣ ቻድ እና ካሜሩን መካከል ከብዙ ጊዜ ወዲህ አለመተማመን አለ። ግን፣ አሁን ቦኮ ሀራም ጥቃት የሚያካሂድበትን አካባቢ ከናይጀሪያ ወደ ሰሜናዊ ካሜሩን ማስፋፋቱ ምን ያህል ላካባቢው አስጊ መሆኑን ግልጽ እየሆነላቸው ተገኝቶዋል። በመሆኑም፣ ከመተባበር የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ተረድተውታል፣ እንደ ኮምፈርት ኤሮ አስተሳሰብ።

Kamerun Mora Armee Soldaten Anti Boko Haram 07/2014
ምስል Reinnier Kaze/AFP/Getty Images
Nigeria Potiskum Selbstmordanschlag 12.01.2015
ምስል Aminu Abubakar/AFP/Getty Images
Idriss Deby Präsident Tschad
ምስል AFP/Getty Images/Seyllou

ዩሊያ ሀን/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ