1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻድ ከምርጫዉ በኋላ ስትቃኝ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 1998

የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ቻድ ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አካሂዳለች።

https://p.dw.com/p/E0ii
ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ
ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢምስል AP

በዉጤቱም ከአዉሮፓዉያኑ 1991ዓ.ም. ጀምሮ የስልጣን ርካብ የተቆናጠጡት የአገሪቱ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ ማሸነፋቸዉ ተነግሯል። በተለያዩ ችግሮች በተወጠረችዉ ቻድ የዴቢ በድጋሚ ለምርጫ መቅረብ የአገሪቱን ዜጎችና አምስቱን የአገሪቱን አማፅያን ቡድኖች አላስደሰተም። የቻድ መንግስት በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በስፋት ከሚንቀሳቀሱት አማፅያኑ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን መንግስት ጋርም ሰላማዊ ግንኙነት ስለሌለዉ ሁኔታዎች የተረጋጉ አይደሉም።
ዋና ከተማዋ ንጃሚና እጅግ ሞቃት ነች። 42 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በአዛኛዉ የሚመዘገብ የሙቀት መጠን ነዉ እንደዉም በዚህ ዓመት በዚህ ወቅት የታየዉ የሙቀት ሁኔታ ደህና ነዉ ተብሏል።
የዋና ከተማዋ አዉራ መንገዶች ብቻ ናቸዉ በወጉ የተሰሩት። ከመዲናዋ ሲወጣ ወዲያዉ የሚያጋጥመዉ አዋራ መንገድ ነዉ።
በምርጫዉ ዕለት በየምርጫ ጣቢያዉ በጎዳናዉ ከሚታዩት ይበልጥ በርካታ እስከአፍንጫቸዉ የታጠቁ ወታደሮች ነበሩ ስፍራዉን የተቆጣጠሩት።
ጋዜጠኞች በተዘዋወሩባቸዉ ሁሉ የምርጫ ጣቢያዎቹ ባዶ ሆነዉ ነዉ ያገኙዋቸዉ። በአብዛኛዉ ወታደሮች፤ ፖሊሶችና የደህንነት ሰዎች ነበሩ ለመምረጥ የሄዱት።
«ለመምረጥ ሄጄ ነበር። በዚህ ወቅት የነበረዉ ሁኔታ ከወትሮዉ የተለየ ነዉ። ሰዉን በሚያስፈራራ መልኩ በርካታ ወታደሮች ነበሩ።» በማለት ነዉ ከመራጮቹ አንዱ በዕለቱ ያዩትን የገለፁት
«ህዝቡ ዉጤቱ ከመነሻዉ የታወቀ መሆኑን ነዉ የተናገረዉ። ለምርጫ መሄዱም አስፈላጊ አልነበረም። እኔም መጀመሪያ መሄድ አልፈለኩም ነበር።»
ይህም ማለት በወሬ ደረጃ ገለልተኛ የተባለዉ የምርጫ ኮሚሽን ምርጫዉ 70 በመቶ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል ብሎ እንዲናገር አያበቃዉም ነበር የሚል ትችት አስከትሏል።
ምንም እንኳን ለይስሙላ ሌሎች አራት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ዴቢ ተመልሰዉ ስለመመረጣቸዉ ማንም አልተጠራጠረም።
አምባገነን የሚያስብለዉን ተግባር እየፈፀመ የሚገኘዉ በዲሞክራሲ ካባ ራሱን የሸፈነዉ የዴቢ አስተዳደር በምርጫዉ ብቻዉን ሮጦ የማሸነፉን ምስጢር የገለፀዉ ተቃዋሚዎቹ በምርጫዉ አንሳተፍም ብለዋል በማለት ነዉ።
«ዴቢ በሌላ የማይተኩና ከእሳቸዉ ሌላ አገር የሚመራ የሚገኝ የማይመስላቸዉ አሉ። ያ በመሰረቱ ስህተት ነዉ። ሰዉየዉ የአገሪቱን ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ችግር መፍታት ያልቻሉ ናቸዉ።»
የሚለዉ ያልዲት ቤጎቶስ ዑላታር የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አይደለም፤ የአገሪቱ የመጀመሪያ የግል ጋዜጣ የሆነዉ ንጃሜና ሄብዶ ጋዜጣ አሳታሚ ነዉ። ዑላታር ፕሬዝደንት ዴቢን ተችቷል በሚል ክስ በእስር ላይ ይገኛል።
«የአሁኑ መንግስት በሁለት መመሪያዎች መካከል እየሰራ ነዉ የሚገኘዉ። በአንድ ወገኑ ሙስና በሌላዉ ወገን ኋላ ቀርነት ይዘዉታል። ምህረት የማድረግ ነገር ሊኖር ይችላል ነገር ይህ መንግስት የተሳሳተ አካሄዱን ለማረም ያደረገዉ አንዳች ነገር የለም።» ይላል ዑላታር።
ያለፉት ዓመታት ሲቃኙ አገራቸዉ ቻድ ከዓለም ድሃ ሀገራት በአምስተኛ ደረጃ መገኘቷን የሚያዉቁት ዴቢ እድገት አመጣለሁ ብለዉ ነበር።
በትጥቅ ትግል፤ በሱዳንና በፈረንሳይ ደጋፊነት ቀዳሚያቸዉን አምባገነን መሪ ሂሴኒ ሀብሬን ከስልጣን በማስወገድ ሁለት እግራቸዉ መዲናዋን ረገጠ።
ከዚያም ሌሎች ፓርቲዎች በአገሪቱ እንዲቀሳቀሱ፤ ነፃ ፕረስ እንዲኖርና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ ፈቀዱ።
ታሪክ ራሱን የደገመ ይመስላል እሳቸዉን ወደስልጣን መንበር ለማዉጣት የደገፈቻቸዉ ሱዳን አሁን ደግሞ አምስቱን በእሳቸዉ ላይ ያመፁ ቡድኖች በመደገፍ ልታወርዳቸዉ እንደምትሞክር ነዉ የሚናገሩት።
«ካለፈዉ ዓመት ማለቂያ ጀምሮ በርካታ መኮንኖች ከጦሩ በመዉጣት ወደሱዳን ገብተዋል። መፈንቅለ መንግስቱም ሆነ ሌሎቹ ድርጊቶች የተፈፀሙት በእነሱ ሲሆን የገንዘብ ድጋፍን የሚያገኙት ደግሞ ከሱዳን ነዉ።»
በሌላ ወገን ደግሞ ለዲሞክራሲ እንቀሳቀሳለሁ የሚሉት ዴቢ የመንግስታቸዉን ቡራኬ ያላገኘ ድርጅት በቻድ እንዳይኖር እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ።
«ዛሬ በአገሪቱ ከመንግስት ጎን ያልቆመ ገለልተኛ አካል መኖር አይችልም። ይህም አዲስ አሰራርና እጅግ ከባዱ አካሄድ ነዉ።»