1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ችሎትና ብይን በቀድሞው የቻድ አምባገነን መሪ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 20 2008

የቀድሞው የቻድ አምባገነን መሪ ኢስኔ አብሬ በስብዕና አንፃር ፈፅመውታል በተባለ ወንጀል የተመሰረተባቸውን ክስ የሚመለከተው በዳካር፣ ሴኔጋል የተጀመረው ችሎት የፊታችን ሰኞ እጎአ ግንቦት 30፣ 2016 ዓም ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1Iw7J
Hissene Habre Tschad Diktator
ምስል picture-alliance/AFP/Stringer

[No title]

የአንድ ሀገር ፍርድ ቤት በስብዕና አንፃር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በተከሰሱ የአንድ ሌላ ሀገር የቀድሞ መሪ ላይ ችሎት ሲያካሂድ የዳካር፣ ሴኔጋሉ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ሴኔጋል እና የአፍሪቃ ህብረት እጎአ በ2013 ዓም በዳካር በሚገኘው የሴኔጋል ፍርድ ቤቶች ስር መርቀው የከፈቱት የአፍሪቃውያን ልዩ ፍርድ ቤት ኢስኔ አብሬ የቻድ መሪ በነበሩባቸው እጎአ በ1982 እና በ1990 ዓም መካከል በሀገሪቱ በስብዕና አንፃር ለተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሆነውን ግለሰብ ወይም የሆኑትን ሰዎች ጉዳይ እንዲመለከት ታስቦ ነው የተቋቋመው። እጎአ ሀምሌ 20፣ 2015 ዓም ነበር የቀድሞው የቻድ ፕሬዚደንት ኢስኔ አብሬ በስብዕና አንፃር ወንጀል፣ በቁም ስቅል ማሳየት ተግባር እና በጦር ወንጀል ተከሰው ለመጀመሪያ ጊዜ በልዩው የዳካር የአፍሪቃውያን ፍርድ ቤት የቀረቡት።

የ73 ዓመቱ የቀድሞ የቻድ ፕሬዚደንት በምህፃሩ «ዴ ዴ ኤስ» የተባለውን የሰነዶች አያያዝ እና የደህንነት ክፍል በሚል መጠሪያ ይታወቅ የነበረውን ህቡዕ የፖሊስ ስለላ መረብን ይመሩ እና በፖሊስ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሰዎች ላይ የቁም ስቅል ማሳያው ተግባር ወይም ሌላ ቅጣት እንዲፈፀም በቀጥታ ትዕዛዝ ይሰጡ ነበር በሚል ነው የሚወቀሱት።
እጎአ በ1990 ዎቹ ዓመታት የወጣ አንድ የቻድን የሰብዓዊ መብት ይዞታ የዳሰሰ ዘገባ እንደሚያሳየው፣ በዚያን ጊዜ በብዙ መቶዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞ እስከ 40,000 የሚጠጉ ሰዎች የዚሁ ጥሰት ሰለባዎች ሆነዋል። የቀድሞው የቻድ ፕሬዚደንት ኢስኔ አብሬ በአንፃራቸው የተመሰረተውን ክስ በጠቅላላ ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል፣ ጠበቆቻቸውም ኢስኔ አብሬ ስለተባለው ክስ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነው ያመለከቱት።

Senegal Justizpalast in Dakar
ምስል Getty Images/AFP/Seyllou

በኢስኔ አብሬ አገዛዝ ዘመን የተፈፀመው ወንጀል ሰለባ የሆኑትን የቻድ ዜጎች ወክሎ በፍርድ ቤት የሚሟገተው ቡድን አካል የሆኑት ጠበቃ የሴኔጋላውያን የሰብዓዊ መብት ሊግ ፕሬዚደንት ፣ አሳን ዲዮማ ንዲያዬ የሀብሬን እና የጠበቆቻቸውን አባባል አይቀበሉትም።

« እርግጥ ነው፣ ተከሳሽ ጥፋተኛ ላይሆን ይችላል የሚለውን ግምት ማክበር ግዴታችን ነው፣ ስለሆነም ፍትሓዊ ውሳኔ ባላገኘ ጉዳይ ላይ ፍርድ ልንሰጥ አንችልም። ይሁንና፣ የአንድ ሲቭል ማህበረሰብ አባል ስትሆን እና የተፈፀሙ ብዙ በደሎችን በሰነድ ከያዝክ፣ የዓይን እማኞችን ቃል እና ማስረጃ ከሰበሰብክ እና በተለይ በብዙ ብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት ደንበኞቻችን ምን እንደሚጠብቁ ስናስብ፣ በፍርዱ ሂደት መተማመን አለብን። እንደማስበው፣ ልዩው ፍርድ ቤት አብሬ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን ሊሰጥ ይችል ይሆናል። ብይኑ ለእኛ የማይመች ከሆነ፣ የሲቭል ማህበረሰብ ቡድኖች ይግባኝ ማለታቸው እንደማይቀር መጠበቅ አለብን። »

የሴኔጋላውያን የሰብዓዊ መብት ሊግ ፕሬዚደንት ፣ አሳን ዲዮማ ንዲያዬ የመብት ረገጣው እና የቁም ስቅሉ ወንጀል ሰለባዎችንም ግምት በመጥቀስ አክለው እንዳስታወቁት፣ ሰለባዎቹ ችሎቱ በአንፃራቸው የተፈፀመውን በደል አውቆ በመቀበል ትክክለኛውን ብይን ይሰጣል።

Senegal Prozess gegen Hissene Habre in Dakar Pressekonferenz
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Blackwell

« ፍትሕ እንደሚያገኙ ሙሉ እምነት ያላቸው ሰለባዎች ናቸው፣ ምክንያቱም፣ የሰበሰብነውን ማስረጃ እና ሰነድ ያገኘነው ከሰነዶች አያያዝ እና የደህንነት ክፍል ወይም በምህፃሩ «ዴ ዴ ኤስ» በሚል መጠሪያ ከሚታወቀው ህቡዕ የፖሊስ ስለላ መረብ ነው። ስለዚህ ማንም ሰው የሀሰት ማስረጃ ወይም ሰለባዎችን አቅርበዋል በሚል ልሊወቅሰን አይችልም። ስቃይ የደረሰባቸውን ወይም በዘፈቀደ እስራት የማቀቁትን ሰለባዎች ዝርዝር ያዘጋጀው ራሱ «ዴ ዴ ኤስ» ነው። ይህ በመሆኑም፣ ሰለባዎቹ መስየ አብሬ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ ብለው በፍፁም አያስቡም። »

ኢስኔ አብሬ ሴኔጋል እና የአፍሪቃ ህብረት ካቋቋሙት እና ባለፈው ሀምሌ፣ 2015 ዓም ስራውን ከጀመረው በዳካር ከሚገኘው የሴኔጋል ፍርድ ቤቶች ስር ካለው ልዩ የአፍሪቃውያን ፍርድ ቤት ጋር ለመነጋገርም ሆነ ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆኑም። የፍርድ ቤቱን ስልጣን ያልተቀበሉት አብሬ ራሳቸው የቀጠሩዋቸውን ጠበቆቻቸውን ካሰናበቱ ወዲህ ለርሳቸው የሚሟገቱት ልዩው ፍርድ ቤት የመደበላቸው ጠበቆች ናቸው።

ፍርድ ቤቱ ለኢስኔ አብሬ ጥብቅና እንዲቆሙ ከሰየማቸው ሶስት ጠበቆች መካከል አንዱ ሙኒር ባላል ናቸው።
« የፊታችን ሰኞ፣ ሰኔ 30፣ 2016 ዓም የሚተላለፈውን ብይን በርጋታ እና እንደምንፈልገው እንደሚሆን በሙሉ እምነት እና በብሩህ አመለካከት ነው የምንጠብቀው። አንዳንዶች ፕሬዚደንት አብሬ ከፍርድ ቤቱ ጋር አለመነጋገራቸው ጉዳያቸውን ሊጎዳ ይችል ይሆናል ብለው ያስቡ ይሆናል፣ ይሁንና፣ ይኸው ዝምታቸው እና ሆን ብለው በችሎቱ ሂደት ለማናገር ወይም ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑበት ርምጃቸው በፍፁም አይጎዳቸውም። ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያየናቸው የማስረጃ አቅርቦቱ አብቅቶ ዓቃቤ ሕግ እና ጠበቆች የመጨረሻ መከራከሪያ ሀሳቦቻቸውን ባቀረቡበት የመጨረሻው የፍርድ ቤት ውሎ ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አላየናቸውም። »

Tschad Präsident Idriss Deby
ምስል picture-alliance/dpa/C. P. Tesson

በሴኔጋል መዲና ዳካር በቀድሞው የቻድ ፕሬዚደንት ኢስኔ አብሬ አንፃር የቀጠለውን ችሎት በጥሞና የተከታተለው ሕዝብ የአብሬን ጥፋተኛ መሆን አለመሆን ላይ የተለያየ አስተያየት ነው የሰነዘረው።« በርግጥ ፣ አንድ የሰሩት ነገር መኖር አለበት፣ ይሁን እንጂ፣ ከርሳቸው ይበልጥ የወቅቱ የቻድ ፕሬዚደንት ዴቢ ተጠያቂ ናቸው ብየ አስባለሁ፣ እኔ እንደምገምተው፣ አብሬ ጥፋተኛ አይደሉም። ኢድሪስ ዴቢም ተጠያቂ ናቸው ብየ አስባለሁ። »
« ከችሎቱ አካሄድ ስነሳ፣ አብሬ ከባድ ብይን ይተላለፍባቸዋል። እንደሚመስለኝ፣ ጥፋተኛ ተብለው፣ ቢያንስ 20 ዓመት የእስራት ቅጣት ይፈረድባቸዋል። »

« በዕድሜ ገፍተዋል፣ ዕድሜ ራሱ ፈርዷቸዋል። ስለዚህ፣ ኑሯቸውን እንዲኖሩ መተው ነው። የሰሩት ወንጀልም የለም። ቻድን በጥሩ ሁኔታ መርተዋል። » ሴኔጋል እና የአፍሪቃ ህብረት ያቋቋሙት በዳካር በሚገኘው የሴኔጋል ፍርድ ቤቶች ስር ካለው ልዩ የአፍሪቃውያን ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ በስብዕና አንፃር ወንጀል፣ በቁም ስቅል ማሳየት ተግባር እና በጦር ወንጀል የተከሰሱት ኢስኔ አብሬ ዕድሜ ይፍታህ እንዲበየንባቸው ነው የጠየቀ ሲሆን፣ ይኸው ጥያቄው በልዩ የአፍሪቃውያን ፍርድ ቤት ዳኞች ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ፣ ብሎም፣ ምን ዓይነት ውሳኔ እንደሚሰጡ የፊታችን ሰኞን ጠብቆ ማየት ግድ ይላል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ