1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኑሮና የዋጋ መናር በኩባ

ዓርብ፣ ሐምሌ 29 1997

የሶሻሊስቱ ጎራ ከተዳከመ ብሎም ከፈራረሰ ወዲህ ኩባ ምጣኔ ሃብቷ ከዓመት ወደዓመት እየወደቀ መሄዱ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/E0eS

ይህ በርዕዮተ ዓለም ልዩነት በአገሪቱ የመጣዉ ችግር ያስከተለዉ የዋጋ መናርንና የገቢ አለመመጣጠንን በመሆኑ በኩባ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ኑሮ ከአቅም በላይ ሆኗል።
የአገሪቱ መንግስት አማራጭ የሚላቸዉን መንገዶች እየሞከረ መሆኑን ለህዝቡ በየጊዜዉ ቢገልፅም ተስፋ ከአድማስ ማዶ ርቃ የተሰቀለች ዳቦ ሆናለች ለኩባዉያን።
«ቀላል አይደለም» ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኩባዉያን ስለኑሯቸዉ ሲጠየቁ ቅሬታቸዉን የሚገልፁበት የተለመደ አባባል።
ከወር ወር ስለማያፈናፍነዉ ደሞዛቸዉም ሆነ በየቀኑ ይባስ እየከፋ ስለሄደዉ የህዝብ ማመላለሻ ዘዴ፤ ሲናገሩ ምሬታቸዉ እየቀደመ መጥቷል።
በዚያ ላይ በተደጋጋሚ በሚቋረጠዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ሳቢያ በሙቀት በተጨናነቀ ሌሊት የሚገፉት ህይወት አንገሽግሿቸዋል።
በዚህ መሃልም የሶሻሊስቱ የፊደል ካስትሮ መንግስት አገር ወዳድ ኩባዉያንን በአብዮቱ እምነታቸዉ እንዲፀና መማፀን ቀጥለዋል።
አንዱ ቀን አልፎ ሌላዉ ቀን ሲተካ 11.2 ሚሊዮን ህዝብ ባለባት በዚች የካሪቢያን ደሴት አገር ኑር እየከበደ መሄዱን ተያይዞታል።
ከተጠቀሰዉ የአገሪቱ ህዝብ መካከልም 70 በመቶ የሚሆነዉ ወገን ካስትሮ የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት ከአዉሮፓዉያኑ 1943ዓ.ም. ወዲህ የተወለደ መሆኑ ይነገራል።
እሳቸዉ በእነሱዉ ዘመን አቆጣጠር በ1959 ስልጣን ለመያዝ ከበቁ ወዲህም ፆሙን የሚያድር፤ ያልተማረና በህክምና እጦት የሚሞት በቀላሉ ፈልጎ ማግኘት እንደማይቻል ታዛቢዎች ይናገራሉ።
እዉነተኛዉ ድህነት በኩባ የመጣዉ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ ተደግፎበት የነበረዉ የበፊቷ ሶቭየት ህብረት ስትፈራርስ የተከሰተዉ የምጣኔ ሃብት ድቀት ወቅት ነዉ።
ከፍተኛ የህክምና አገልግሎትና እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ድረስ ያለዉ የትምህርት ዕድል ለማንኛዉም በኩባ ምድር ለሚኖር ሁሉ እስከዛሬም በነፃ ይሰጣል።
በዚያም ላይ የአገልግሎት ክፍያና መሰረታዊ የምግብ አይነቶች በድጎማ የሚገኙ ናቸዉ።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አብዛኛዉ ኩባዉያን አስተማማኝ ባልሆነዉ የመጓጓዣ አገልግሎት፤ በመኖሪያ ቤት እጦት፤ በዝቅተኛ የወር ገቢያና በከፋዉ የኤሌክትሪክ ችግር ህይወቱ ተጨናንቋል።
ስማቸዉን ለመጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ኩባዊ ምሁር እንደገለፁት ይሄ ማንኛዉም ዜጋ ሊያጣዉ የማይፈልገዉ ከአብዮቱ ያገኘዉ ጥቅም ቢሆንም የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብታዊ አካሄድ አገሪቱ ከገባችበት ድቀት አትወጣም።
በሌላ ወገን ደግሞ መጠነኛ መሻሻልና መረጋጋት እየታየ ነዉ የሚለዉ የኩባ መንግስት በያዝነዉ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ አጠቃላይ ያገሪቱ ምርት 7.3 በመቶ ከፍ እንዳለ ያስረዳል።
በዚህ ሳቢያም የምንዛሪ ለዉጥ ስለታየ መንግስት የጡረታ ገቢና የጤና ባለሙያዎችና የመምህራን ደሞዝ ላይ በመጠኑ ጭማሪ አድርጓል።
43,000 ቤተሰቦች በችግር ላይ መሆናቸዉን መንግስት ስላመነ በማህበራዊ ድጎማዉ ለዉጥ በመደረጉም 39.9 በመቶ ከሚሆነዉ ህዝብ መካከል 4.4 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸዉ ታዉቋል።
ያም ቢሆን ግን ኑሮ በኩባ እየተወደደ በመሄዱ ጭማሪ የተደረገበት ደሞዝም ሆነ የጡረታ ገቢ የቤተሰብ ሃላፊነት ይዞ ለሚመራዉ ዜጋ በቂ አልሆነም።
ማርታ ሄርናንድዜ የተባቡት መምህርት እንደገለፁት እሳቸዉና ባለቤታቸዉ በወር 900 ፔሶ ማለትም 37 ዶላር ደሞዝ ያገኛሉ።
ከዚህ ላይ ከ35 እስከ 40ፔሶ ገደማ በወር ለስልክ፤ ለኤሌክትሪክ ኃይል፤ ለዉሃና ለማብሰያ ጋዝ አዉጥተዉ የሚቀራቸዉ ከ15 ቀናት በላይ አያዘልቃቸዉም።
ምሁራን ያደረጉት ጥናት እንደሚያሳየዉ ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ መሰረታዊ የሚባሉት የእርሻ ምርቶች ዋጋ 8.5 በመቶ አሻቅቧል።
በኩባ አራት አባላት ያሉት መጠነኛ ቤተሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን አሟልቶ ኑሮዉን ለመምራት ከ1,200 እስከ 1,500 ፔሶ ማለትም ከ50 እሰ 63 ዶላር እንደሚያስፈልገዉ ጥናቱ ጨምሮ አሳይቷል።
ከዚህ በመነሳትም በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሚታየዉን የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በተከሰተዉ የኑሮ መናር ሳቢያ ዜጎች ተቃዉሟቸዉን የሚገልፁበት መንገድ ነዉ የሚሉ አሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የፓለቲካ እስረኞች ይፈቱ በሚል መጠነኛ የተቃዉሞ ሰልፎች በከተማዋ መታየት ጀምረዋል።
ካስትሮም ባለፈዉ ወር መገባደጃ ከሃዲዎችና በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉ ነፍሰ ገዳዮች ለሚያካሂዱት የተቃዉሞ ሰልፍ ትዕግስታቸዉ ማለቁን በመግለፅ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ያዘኑትን ዜጎች አማራጭ የሃይል ምንጭ ይፈጠራል እስከተባለበት እስከመጪዉ ዓመት አጋማሽ እንዲታገሱ ተማጽነዋል።
ካስትሮ ምጣኔ ሃብታቸዉን ከቻይናና በነዳጅ ሃብት ከበለፀገችዉ ቬንዝዌላ ጋር ለማቆራኘት የሚያደርጉት ጥረት ዉጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አላቸዉ።
በቅድሚያ ግን አሁን በአገሪቱ ዉስጥ የተፈጠረዉን ዉጥረት አለዝቦ መያዝ ለኩባ መንግስት የግድ ነዉ።
በዚህ በበጋዉ ወራት በኤሌክትሪክ ኋይል መቋረጥ ሳቢያ በማቀዝቀዣ የተቀመጠ ምግብ ስለሚበላሽ ጥያቄዉ የህልዉና ጉዳይ እንጂ የቅንጦት አይደለምና።