1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያና የእርሳስ ማዕድን ብናኝ ብክለት

ሐሙስ፣ የካቲት 1 2004

በሰሜን ናይጀሪያ በእርሳስ ማዕድን ብናኝ የተመረዙ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት አስቸኳይ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚሟገተው ድርጅት፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ትናንት ያወጣው አንድ ጥናት አስታወቀ። የሂውማን ራይትስ ዎች የጤና ተመራማሪ ወይዘሮ ጄን

https://p.dw.com/p/13zI3
የእርሳስ ማዕድን ብክለትያስጋቸው ሕፃናትምስል DW/Katrin Gänsler

ኮኸን ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፡ በሰሜን ናይጀሪያ በእርሳስ ማዕድን ብናኝ የተመረዙ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት አስቸኳይ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚሟገተው ድርጅት፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ትናንት ያወጣው አንድ ጥናት አስታወቀ። የሂውማን ራይትስ ዎች የጤና ተመራማሪ ወይዘሮ ጄን ኮኸን ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፡ በተለይ በናይጀሪያ የዛምፋራ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ማዕድኑ እርሳስ ያስከተለው ብክለት በሀገሪቱ የቅርብ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊው ነው።
አሁንም ዘመናይ ባልሆነ ዘዴ ወርቅ የሚወጣባቸው በርካታ ማዕድናት በሚገኙባቸው የዛምፋራ ክፍለ ሀገር መንደሮች ችግሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደነበረው አሁንም እጅግ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉ ባካባቢው ነዋሪዎች፡ በተለይም በሕፃናቱ ጤንነት ላይ፡ እንዲሁም፡ በተፈጥሮ አካባቢው ጎጂ መዘዝ ማስከተሉን የሂውማን ራይትስ ዎች የጤና ተመራማሪ ወይዘሮ ጄን ኮኸን አመልክተዋል።
« ቢያንስ እስከአሁን ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ሕፃናት ሞተዋል፤ ሌሎች ሁለት ሺህ የሚሆኑ ደግሞ አስቻኳዩ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው እናውቃለን። ሕፃናቱ ለእርሳሱ ማዕድን ብናኝ ተጋልጠዋል። በሺዎቹ ለሚቆጠሩት ሕፃናት ሊኖሩበት የሚችሉ ንፁሕ የተፈጥሮ አካባቢ የለም ለማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የሚኖሩባቸው ቤቶች፡ ውሀው፡ በጠቅላላ አካባቢው በእርሳሱ ማዕድን ተበክለዋል። ብክለቱንም ለማስወገድ የተደረገ ነገር የለም። በወቅቱ ያልተበከለ አካባቢ የለም። ቤተሰቦቻቸውም በማዕድናቱ ውስጥ መሥራታቸውን በመቀጠላቸው መኖሪያ ቤቶቹ ብክለት ሊወገድ አልቻለም።»
እርግጥ፡ ድሀ በሚባለው ሰሜን ናይጀሪያ የሚኖረው ሕዝብ ኑሮው ለመምራት በነዚህ ኋላ ቀሮቹ ማዕድናት ውስጥ ከመስራት የተሻለ አማራጭ እንደሌለው ያመለከተው የሂውማን ራይትስ ዎች ጥናት የማዕድኑ ስራ ጤናን በማይጎዳ ሁኔታ ሊካሄድ እንደሚገባ አስገንዝቦዋል። የዛምፋራ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር መስተዳድር ይህን ብክለት ለመቀነስ፡ ከተቻለም ለማስወገድ ካንዳንድ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ጋ ባንድነት በመተባበር አንዳንድ አካባቢውን ከብክለት ነፃ የማድረግ የማፅዳት ርምጃ መውሰዱ እና ሕፃናቱን በማከሙ ተግባርም ድንበር ከማይገድበው የሐኪሞች ድርጅት፡ ሜድሰ ሶን ፍሮንትየርን ጋ በቅርብ ተባብሮ መስራት መጀመሩ ተሰምቶዋል። ይሁንና፡ ይላሉ፡ የሂውማን ራይትስ ዎች የጤና ተመራማሪ ወይዘሮ ጄን ኮኸን ይህ ተግባሩ ቀላል አይሆንም።
« ይህ ግዙፍና የተወሳሰበ ችግር ነው። እና ያካባቢው መስተዳድር ችግሩን ውጤታማ እና አጠቃላይ በሆነ መንገድ ለመታገል ቁርጠኝነት እና ከፌዴራሉ መንግሥትም ድጋፍ ያስፈልገዋል። ፌዴራሉ መንግሥት እስካሁን በዚሁ አኳያ ይህ ነው የሚባል ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም፡ የፌዴራሉ የማዕድን ሚንስትር ችግሩን ለመታገል በዛምፋራ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር ያሉ ማዕድናት ሁሉ እንዲዘጉ የሚያዝ መግለጫ ትናንት አውጥቶዋል። ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት የሚያስችል ትክክለኛው መንገድ አይደለም። ይህ ካሁን ቀደም ተሞክሮ ነበር፤ ግን ችግሩን ይበልጡን ነበር ያባባሰው። »

ከእርሳስ ማዕድን በሚተነው ብናኝ ሰበብ በሰሜናዊ ናይጀርያ መንደሮች ለተከሰተው ብክለት ማስወገጃ የናይጀሪያ ፌዴራል ማዕድን ሚንስቴር ያቀረበውን የመፍትሔ ሀሳብ ውጤታማነትን የሂውማን ራይትስ ዎች የጤና ተመራማሪ ወይዘሮ ጄን ኮኸን ይጠራጠሩታል።
« እኛ ሦስት ነጥቦች ያሉት የመፍትሔ ሀሳብ ነው የምናቀርበው። የመጀመሪያው አስተማማኝ የማዕድን አሠራር ዘዴዎችን ማስተዋወቅ ነው። ይህ ሲሆን ያካባቢው ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ላይ ሳይጥሉ በማዕድኑ ሥራ መሥራታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። ሁለተኛው የተበከሉትን አካባቢዎች በጠቅላላ ማፅዳት ነው። ሦስተኛው፡ ያካባቢው ሕፃናት በእርሳስ ማዕድኑ ብናኝ ተመርዘው መሆን አለመሆናቸውን በምርመራ ማጣራትና ማከም ይሆናል። »
እነዚህ ሦስት የመፍትሔ ሀሳቦች ባንድ ጊዜ ተግባራዊ እስካልሆኑ ድረስ ግን በእርሳስ ማዕድን ብናኝ ሰበብ በሰሜን ናይጀርያ የተከሰተው ብክለትና በነዋሪዎቹ ላይ የተፈጠረው የጤና ጉዳት ሊወገድ እንደማይችል ወይዘሮ ጄን ኮኸን አስጠንቅቀዋል።

Bleivergiftung in Nigeria
ምስል DW/Katrin Gänsler
Bleivergiftung in Nigeria
ምስል DW/Katrin Gänsler

አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ