1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያ እና የሰላሙ ጥረት

ቅዳሜ፣ መስከረም 30 2002

ናይጀሪያ ውስጥ በነዳጅ ዘይት በበለጸገው የኒዠር ወንዝ ደለል በመንግስቱ አንጻር ከሚንቀሳቀሱት ዓማጽያን መካከል አስራ አምስት ሺዎቹ ባለፈው ሳምንት የጦር መሳሪያቸውን ለመንግስቱ አስረከቡ።

https://p.dw.com/p/K3GZ
የጦር መሳሪያቸውን ያስረከቡት የኒዠር ደለል ዓማጽያንምስል picture alliance / dpa
የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኡማሩ ያር አዱዋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ያቀረቡትን የምህረት ሀሳብ ዓማጽያኑ ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውን የመንግስቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ምህረቱን ተቀብለው ጦር መሳሪቸውን ያስረከቡት ዓማጽያን ቁጥር መንግስት ከጠበቀው በላይ ከፍ ብሎ ተገኝቶዋል። ይህም፡ የሀገሪቱ መንግስት እነዚህን ዓማጽያን ወደመደበኛው ኑሮ የመመለሱንና በህብረተሰቡ ውስጥ የማዋሃዱን ተግባር በሚገባ መወጣት መቻሉን እና የምህረቱ ርምጃም በኒዠር ወንዝ ደለል የሚፈለገውን ሰላም ማምጣት መቻሉን ብዙዎች አጠያይቀዋል።
ናይጀሪያን በዓለም ካሉት ዋነኞቹ የነዳጅ ዘይት አምራች ከሆኑት ሀገሮች መካከል አንዷ ያደረጋት የነዳጅ ዘይት ንጣፍዋ የሚገኘው በኒዠር ወንዝ ደለል ነው። ይሁንና፡ በዚሁ አካባቢ የሚገኙት ግዙፎቹ የነዳጅ ዘይት ተቋማት በዚያ ከብዙ ዓመታት ወዲህ በመንግስቱ አንጻር በሚንቀሳቀሱት ዓማጽያን ጥቃት ሰበብ ስራቸውን አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ያህል ሊያከናውኑ አልቻሉም። ዓማጽያኑ በነዳጅ ዘይት ተቋማቱ ሰራተኞችና በዘረጉዋቸው የነዳጅ ዘይት ቧንቧዎች ላይ ጥቃታቸውን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋልና። ድሀው የኒዠር ወንዝ ደለል ህዝብ የናይጀሪያ መንግስት ከዚሁ አካባቢ ከሚመረተው የነዳጅ ዘይት ከሚያገኘው ገቢ እኩል ድርሻ እንዲያገኝ በመጠየቅ ነው ዓማጽያኑ በመንግስቱ አንጻር ትግል የጀመሩት። የሀገሪቱ መንግስት ጦር እስካሁን በዓማጽያኑ አንጻር ሁነኛ ርምጃ ለመውሰድ አልቻለም። በዚህም የተነሳ፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ቶማስ መሽ እንዳስታወቀው፡ በዚሁ አካባቢ የቀጠለውን ውዝግብ ለማብቃት በማሰብ ነበር ለዓማጽያኑ ምህረት ለማድረግና ላካባቢውም የኤኮኖሚ ርዳታ ለማቅረብ ቃል የገቡት፤ ይህንኑ የምህረት ሀሳብ በመቀበልም ብዙዎች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን ፈተዋል። ይህ ርምጃቸው በርግጥ በኒዠር ወንዝ ደለል ሰላም ያስገኝ ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።
በምህረት መስጠቱ ጉዳይ ላይ ፕሬዚደንት ያር አዱዋን ያማከሩት የምግስቱ ባለስልጣን ቲሚ አላይቢ ዓማጽያኑ ያስረከቡትን የጦር መሳሪያ፡ ማለትም፡ መትረየስ፡ ሽጉጥ፡ ጂ ሶስት ጠመንጃ፡ ወዘተ የመሳሰሉትን የጦር መሳሪያ ዓይነቶች ዝርዝር ሲያነቡ ነበር ያዳመጣችሁት። ዓማጽያኑ በምህረቱ ጥሪ ተነሳስተው የጦር መሳሪያ ያስረክቡበት የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ነበር የታየው። ይሁንና፡ እጅግ ብዙ ዓማጽኣያን የጦር መሳሪያቸውን ያስረከቡትመንግስት ያቀረበው የምህረት አዋጅ ባበቃበት ባለፈው እሁድ ነበር። በዚሁ ዕለት አምስት ሺህ ዓማጽያን የጦር መሳሪያቸውን አሳርፈዋል።
የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ያር አዱዋ ሀገሪቱ የነጻነት በዓልዋን ባለፈው መስከረም ባከበረችበት ዕለት ምህረቱን ከተቀበሉት ዋነኞቹ የዓማጽያን መሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት ከትልቁ የኢዣው ብሄረሰብ ተወላጁ ከአቴኬ ቶም ጋር ባንድነት በፕሬሱ ፊት በመቅረብ፡ አቴኬ ቶም የዕርቀ ሰላሙን ጥሪያቸውን በመቀበላቸው በይፋ አመስግነዋቸዋል። በዚሁ ወቅት ባሰሙት ንግግራቸውም፡
« ምህረት ማድረግ ብቻውን የችግሩን መጨረሻ ያስገኛል ማለት አይደለም። ግን ሊደረስበት የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳኪያ የሚጠቅም አንዱ ዘዴ ነው። የብረቱን ትግል እና በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ማብቃት አለበት። ምህረቱ በኒዠር ወንዝ ደለል ሰላም እና መረጋጋት ለማስገኘት የሚበጅ አንዱ ዘዴ ነው። »
ዓማጽያኑ የምህረቱን ጥሪ የመቀበላቸው ጉዳይ እስከመጨረሻይቱ ደቂቃ ጠራጣሪ ሆኖ ነበር የቆየው። በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል፡ በተለይም በመንግስቱና በትልቁ የኒዠር ወንዝ ደለል የኢዣው ብሄረሰብ መካከል ያለው አለመተማመን በጣም ስር የሰደደ ነው። እና ያማጭያኑ መሪ አቴኬ ቶም ከፕሬዚደንቱ ጋር ባልተለመድ ሁኔታ ቀርቦ በመታየት ርዕሰ ብሄሩ የገቡትን ቃል እንደሚጠብቁ መናገራቸው አበረታቺ ሆኖ ታይቶዋል።
« እናምንዎታለን። እኔ መቸም ሙሉ በሙሉ አምንዎታለሁ። የገቡትን ቃል አይጠብቁም ብየ አላስብም። ትዕግስት የሌለው ሰው ግን ይህን ሊረዳው አይችልም። ላቀረቡት የምህረት ጥሪ በጣም አመሰግንዎታለሁ። ከኢዣው ብሄረሰብ ጋር ተስማሙ። እና ከምንገኝበት አስከፊ ሁኔታ ነጻ አውጡን። እኛም በገባነው ቃል መሰረት፡ የጦር መሳሪያ ትጥቃችንን እንፈታለን። እኔም የጦር መሳሪያዬን አስረክባለሁ። »
በእርግጥ፡ አቴኬ ቶም እንዳሉትም ባለፈው የሳምንት መጨረሻ የጦር መሳሪያቸውን አስረክበዋል። በፕሬዚደንት ያር አዱዋ ስም ከዓማጽያኑ ጋር በጠቅላላ የተደራደሩት ቲሚ አላይቢ እንዳስታወቁት፡ ሁሉም የምህረቱን ጥሪ ተቀብለውታል። ይህ ሊሆን የቻለውም፡ እንደ አላይቢ ገለጻ፡ የሀገሪቱ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓማጽያኑ ጋር በቀጥታ በመደራደር ተቀናቃኞቹ ወገኖች ከፍጥጫ ሊወጡ የሚችሉበትን መንገድ በመጠቆሙ ነው።
« ይኸው ቀጥ’ተኛ ግንኙነት ነበር እስከዛሬ ድረስ ተጓድሎ የነበረው። በሀገሪቱ አመራርና በተራው ህዝብ መካከል ክፍተት ተፈጥሮ ነበር። »
የናይጀሪያ መንግስት ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ፍላጎት አለው። በዚህም የተነሳ ዓማጽያኑ ወደፊት የኒዠር ወንዝ ደለል ጉዳዮችን በሚመለከት ከምግስቱ ጋር ባንድነት ውሳኔ ይደርሳሉ። እንግዲህ፡ ፕሬዚደንት ያር አዱዋ ያቀረቡት የምህረት ጥሪ የተሳካ ውጤት ማስገኘቱ የሚታየው መንግስታቸው መሪዎቻቸውን ተከትለው የጦር መሳሪያቸውን ለፈቱት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ወጣቶች ሁነኛ የወደፊት ዕድል ሲከፍት ነው። የዚህን ርምጃ ወሳኝነት የተገነዘቡት የፕሬዚደንቱ አማካሪ ቲሚ አላይቢ እንዳስታወቁት፡ የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የፈቱትን ወጣቶች ወደመደበኛው ኑሮ ለመመለስና በህብረተሰቡ ውስጥ ለማዋሃድ በሚረዳ መንግስት ባቋቋመው አንድ ማዕከል ውስጥ ይቆያሉ፤ ለያንዳንዱም አስፈላጊው ርዳት ይቀርብለታል።
« ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚፈልጉትን ወደ ትምህርት ቤት እንልካቸዋልን። በንግዱ ለመሰማራት ለሚፈልጉትም ማበረታቻውንን እና አስፈላጊውን ስልጠና እንሰጣለን። በመርከበኝነት መስራት የሚፈልጉትን ደግሞ ወደ ተገቢው የስልጠና ማዕከል እንልካቸዋለን። »
የኒዠር ወንዝ ደለል ነዋሪዎች ካሁን ቀደምም ከመንግስቱ ተመሳሳዩ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፤ ግን እስካሁን በኑሮዋቸው ላይ አንዳችም ለውጥ አላዩም።በዚህም የተነሳ አሁንም ጥርጣሬ ያላቸውና አሁን በመንግስት ማዕከል የሚገኙት ወጣቶቹ የኒዠር ወንዝ ደለል ነዋሪዎች መንግስት የገባውን ቃል እንዲያሟላ በጥብቅ ጠይቀዋል።
« አትሞ »
የናይጀሪያ መንግስት ለቀድሞ ዓማጽያን ገንዘብ ለመስጠት ከሁለት ሳምንታት በፊት የገባውን ቃል እንዲ፧ተብቅ ወጣቶቹ እየጠየቁ ነው። ቃሉን ካላከበረ ግን ሁኔታዎች ባፋጣኝ ሊበላሹ እና ወጣቶቹም ኑሮዋቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን ስራ ባስቸኳይ ካላገኙ፡ ፊታቸውን ገንዘብ ‘ና የጦር መሳሪያ ሊሰጡዋቸው ወደሚችሉ ቡድኖች ሊያዞሩ እንደሚችሉ ነው ብዙዎች የሚገምቱት።
ፕሬዚደንት ያር አዱዋ በኒዠር ወንዝ ደለል ሰላም የሚወርድበት ሁኔታ ከጦርነት የበለጠ ጥቅም እንደሚያስገኝ ከዓማጽያኑ በስተጀርባ በመሆን የብረቱን ትግል የሚያራምዱትን ወገኖች ማግባባት መቻል አለመቻላቸው እስካሁን በውል አልታወቀም። እንደሚታወቀው፡ ብዙ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ስልጣን እና ከነዳጅ ዘይቱ ገቢም ተጠቃሚ ለመሆን ይችሉ ዘንድ አዘውትረው በምርጫ ዘመቻ ወቅት በነዳጅ ዘይት የታደለውን የኒኀር ወንዝ ደለል ወጣቶችን የጦር መሳሪያ አስታጥቀዋል። እና በሀገሩ ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ወደ ሁለት ዓመታት ገደማ ብቻ የቀረው የናይጀሪያ መንግስት በዚሁ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ውዝግብ በጠለበት አካባቢ ሁኔታዎች ይበልጡን እንዳይበላሹ ከፈለገ ውዝግቡ የሚያበቃበትን መንገድ ለማስገኘት ባስቸኳይ ጥረቱን ማጠናከር ይኖርበታል።
ቶማስ መሽ/አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ