1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያ እና ፀረ ቦኮ ሀራም የጋራ ጦር ጓድ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 6 2007

አምስት አፍሪቃውያት ሀገራት በፅንፈኛው እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሀራም አንፃር አንድ የጋራ ጦር ጓድ ለመቋቋም ተስማሙ። የኒዠር፣ ቻድ፣ ካሜሩን እና የቤኒን መሪዎች ከሁለት ቀናት በፊት ባለፈው ሀሙስ 11-06-2015 ዓም በናይጀሪያ ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ አስተናጋጅነት በመዲና አቡጃ ባካሄዱት ጉባዔ ላይ ነበር እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት።

https://p.dw.com/p/1FgUk
Symbolbild Soldaten Nigeria
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

[No title]

የጋራው ጦር ጓድ አመራር በአምስቱ ሀገራት መካከል በየስድስት ወሩ እንዲዘዋወር ቀርቦ የነበረውን ሀሳብ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ፣ የጓዱ አመራር በዙር የሚያዝበት ድርጊት የተነሱበትን ትግል ዓላማ ሊያዳክመው ይችላል በሚል ምክንያት ውድቅ በማድረግ ጓዱ በሀገራቸው እዝ ስር እንደሚውል አስታውቀዋል። ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ እንዳስረዱት፣ ለጓዱ ከአራቱ ጎረቤት ሀገራት ጎን ብዙውን ወታደር የምታቀርበው ናይጀሪያ በመጀመሪያ ደረጃ የቦኮ ሀራም ሽብር ሰለባ እንደመሆንዋ መጠን ፣ አመራሩ በናይጀሪያ እዝ ስር መዋሉ የጓዱን የጦር ስልት በተቀላጠፈ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል። ይሁንና፣ የጋራው ጦር ጓድ ሠፈር ቀደም ሲል ታቅዶ እንደነበረው በሰሜናዊ ናይጀሪያ በምትገኘው የባጋ ከተማ ሳይሆን በቻድ መዲና ንጃሜና እንዲሆን መሪዎቹ ተስማምተዋል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ለብዙ ሺዎች ሕይወት መጥፋት እና በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ሰዎች መታገት ተጠያቂ የሆነው ቦኮ ሀራም እስኪደመሰስ ድረስ ትግላቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቆረጠው መነሳታቸውን ነው ናይጀሪያ እና ጎረቤት ሀገራት ያስታወቁት።

Nigeria - Präsident Muhammadu Buhari
ምስል picture-alliance/dpa

ቻድ፣ ኒዠር እና ካሜሩን በአውሮጳውያኑ 2015 ዓም የመጀመሪያዎቹ ወራት ናይጀሪያ የቦኮ ሀራምን ሽብር ትቋቋም ዘንድ ጦር እንደላኩ እና ይኸው ድጋፋቸውም በርካታ ድሎችን እንዳስመዘገበላቸው የሚታወስ ነው። እነዚሁ ድሎች ለንዑሳኑ የናይጀሪያ ጎረቤት ሀገራት ክብር ቢያስገኙም፣ ናይጀሪያ የአዲሱን የጋራ ጦር ጓድ አመራር ለብቻዋ ለመያዝ መፈለጓ በመካከላቸው ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችል አሁን በበርሊን የሚገኘው በምህፃሩ «ሞሴኮን» በመባል የሚታወቀው የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ ድርጅት ባልደረባ ያን ፒየር ገምተዋል።

« ቦኮ ሀራም እንቅስቃሴውን ናይጀሪያ ውስጥ ነው የጀመረው፣ በመሆኑም ችግሩ በዋነኝነት ናይጀሪያን ነው የሚመለከተው ተብሎ ከታሰበ የናይጀሪያ አመራሩን የመያዙ አቋም ትክክለኛ ነው ሊባል ይችል ይሆናል፣ ይሁንና፣ የቡድኑ ሽብር የሚያስከትለው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተፅዕኖ ይህን የናይጀሪያን ይበልጡን አዳጋች ያደርጋል። »

ይሁንና፣ የቦኮ ሀራምን ሽብር እንዲያበቁ ግፊት ያረፈባቸው አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ይህንኑ አቋማቸውን ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ነው ያን ፒየር ያስረዱት፣ ምክንያቱም፣ የጦር ጓዱ አመራር በየስደስት ወሩ የሚቀያየርበት ድርጊት አምስቱ ሀገራት ቦኮ ሀራምን ለመምታት ያስቀመጡትን ዓላማ ከግብ በሚያደርሱበት ጥረታቸው ላይ እንቅፋት እንደሚደቅን ነው ያን ፒየር ያመለከቱት ።

Boko Haram Flagge
ምስል S. Yas/AFP(Getty Images

« በናይጀሪያ መረጋጋትን ለማስፈን እንደሚሰሩ ያስታወቁት ፕሬዚደንት ቡሀሪ የጓዱ አመራር በዙር እንዲያዝ እንደማይፈልጉ ያቀረቡት መከራከሪያ ሀሳብ፣ በተለይ፣ ቦኮ ሀራም ያስፋፋው ሽብር ግዙፍ ያካባቢ ችግር እየሆነ የመጣበት ድርጊት ሲታሰብ ትክክል ነው። በጦሩ እዝ፣ እንዲሁም፣ በጦሩ ስልት አፈፃፀም ላይ ግልጽ አሰራር እንዲኖር ይፈለጋል፣ የተጓዳኝ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅምም ካካባቢው ጥቅም በልጦ እንዳይሄድ መከታተል የግድ ይላል። ለዚህም ነው የጋራው ጦር ጓድ አመራር ከስድስት ወራት በላይ የሚቀጥልበት አሰራር በጣም በጣም አስፈላጊ የሚሆነው። »

ናይጀሪያዊው ፕሬዚደንት መሀማዱ ቡሀሪ እአአ ባለፈው ግንቦት 29፣ 2015 ዓም ሥልጣናቸውን በይፋ ከተረከቡ ወዲህ ፣ ከርሳቸው በፊት ሀገሪቱን በመሩት ጉድላክ ጆናታን አንፃር፣ በቦኮ ሀራም ላይ በርካታ ርምጃዎችን ነበር ያንቀሳቀሱት። ከነዚህም አንዱ የናይጀሪያን ጦር እዝ ከመዲናይቱ አቡጃ የቦኮ ሀራም ጠንካራ ሠፈር ወደሚገኝባት ማይዱግሪ ከተማ ማዛወራቸው ይጠቀሳል። የፀጥታ ስጋቶችን በዘላቂነት ለማስወገድም የረጅም ጊዜ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብም ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ጎረቤት ቻድን እና ኒዠርን የጎበኙት እና ጀርመን እአአ ሰኔ ሰባት እና ስምንትን ባስተናገደችው በኢንዱስትሪ የበለፀጉት የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች ጉባዔ ላይ የተገኙት ፕሬዚደንት ቡሀሪ ሀገራቸው ፅንፈኝነትን ለመታገል ለጀመረችው ጥረቷ ተጨማሪ ርዳታ እንዲደረግላት ተማፅኖ አቅርበዋል። ናይጀሪያውያን አሸባሪውን ፅንፈኛ ቡድን ቦኮ ሀራምን በመደምሰሱ እና በሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ በመፍጠሩ ረገድ ከአዲሱ ፕሬዚደንታቸው ባፋጣኝ ቁርጠኛ ርምጃ እንደሚጠብቁ በሚገባ መገንዘባቸውን የአፍሪቃን ጉዳዮች የሚከታተል የአንድ ሌላ የአማካሪ ድርጅት ፖለቲካ ተንታኝ ኢማድ ሜስዱዋ አስረድተዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ