1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጄሪያውያት ሴተኛ አዳሪዎች በጀርመን

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2003

የሰዎች ዝውውር በጀርመን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። በተለይም በጀርመን ሴተኛ አዳሪዎች ሊገኙ በሚችሉባቸው የተለዩ ቦታዎች በግድ ለዝሙት ስራ የሚጋዙ አፍሪካውያን ሴቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

https://p.dw.com/p/PjIW
ምስል Alamode Film

በዚህ በፈረንጆቹ ዐመት መጀመሪያ ላይ የጀርመን ፖሊስ ባደረገው አሰሳ 600 ያህል ሴተኛ አዳሪዎች የሚገኙባቸውን ቦታዎች ደርሶባቸዋል። በዚያም ከ170 በላይ ናይጄሪያዊ ሴቶች በህገ ወጥ የሴተኛ አዳሪነት ስራ ተሰማርተው አግኝተዋቸዋል። ከእነዚህም ቢያንስ 50 የሚሆኑት የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ናቸው። ሴቶቹ እንደሚናገሩት በምዕራብ አፍሪካ ባለው የቩዶ አስማት አማካኝነት ተገደው ወደሴተኛ አዳሪነት ስራ ተሰማርተዋል። የዶቸቬሌዋ የአፍሪካ ክፍል ባልደረባ አሱምፕታ ላቱስ ከፍራንክፈርት ፓሊስ ከፍተኛ መኮንን ጋር ሴተኛ አዳሪዎቹ በሚገኙባቸው አንዳንድ የፍራንክፈርት ክፍሎች በመሄድ ያጠናቀረችውን መሳይ መኮንን ያቀርበዋል።

ድምጽ--አትሞ

ባቡሩ ፍራንክፈርት መሃል ባቡር ጣቢያ ሲደርስ ቆመ። ይህ የፍራንክፈርት ክፍል ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት የሚገኙበት ቦታ ነው። በዚህ ስፍራ በመጀመሪያ የሚታይ ትልቅ በመብራቶች የደመቀ ቤት አለ። ሴቶች በብዛት ይታያሉ። በአካባቢው ያለው የመኪና ማቆሚያ ጢም ብሏል። ወንዶች ድምጽ ሳያሰሙ በእርጋታ ከዚያች ቤት ይወጣሉ። ይገባሉ። 140 ሴቶች ስራ ላይ ናቸው--የሴተኛ አዳሪነት ስራ።የፍራንክፈርት ፖሊስ ከፍተኛ መኮንን ማርኩስ እስታይነር እንደሚሉት በአጠቃላይ ፍራንክፈርት መሀል ባቡር ጣቢያ በሚገኘው የሴተኛ አዳሪዎች መንደር በየቀኑ 500 ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት ስራ ላይ ይሰማራሉ። ከቤቷ በስተጀርባ የተወሰኑ ወንዶች እይታ ውስጥ በማይገቡበት ሁኔታ ተኮልኩለዋል። የዶቸቬሌዋ ባልደረባና የፖሊስ መኮንኑ ወደቤቷ ሲቃረቡ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት መጮህ ጀመሩ። በአንድ ነገር እየተጣሉ ነበር።

አትሞ

የፖሊስ ከፍተኛ መኮንኑ ስለሁኔታው ይገልጻሉ።

ድምጽ

«ይህ እንግዲህ ሴቶቹ የሚሰሩበት ቦታ ነው። አንዲት ምኑንም የማታውቅ ከአንድ የናይጄሪያ መንደር የምትመጣ ወጣት ሴት የምታርፍበትና የምትሰራበት ቦታ ነው። እንዲህ ባለ የውጭ ሀገር ቦታ፤ ቋንቋውንና ባህሉን ለማታውቅ አፍሪካዊት ወጣት ይህን ዓይነቱ ግጭት የተለመደ ነው ለአንድ የጀርመን ሰው በእርግጥ ጥሩ ስሜት አይሰጠውም።»

ሴተኛ አዳሪዎቹ በሚገኙበት ቦታ አጠገብ መሽታ ቤት አለ። አንድ ሰው ከመሽታ ቤቷ ወጣ ሲል፤ የዶቸቬሌዋ ባልደረባ እንደገለፀችው የፖሊስ መኮንኑ በጆሮዋ የሀነ ነገር ሹክ አላት። የፖሊስ መኮንኑ ሹክ ያለው፤ ስውዬው ከመሽታ ቤቷ ባሌቤቶች አንዱ እንደሆነና ከሴቶቹ ገንዘብ የሚቀበል መሆኑን ነው። የፖሊስ መኮንኑ ማርኩስ እስታይነር በሌሎች በርካታ የሴተኛ አዳሪዎች መገኛ ቤቶች መግባት ቢችሉም ለዶቸቬሌዋ ባልደረባ ግን መግባቱ አልተፈቀደላትም። የአጋጣሚ ሆኖ የዚያን ቀን የፖሊስ መኮንኑና ባልደረባው ናይጄሪያዊ ሴተኛ አዳሪ የሆነች ሴትን አላገኙም።

ድምጽ

«ለጊዜው ጥቁር አፍሪካዊ ሴተኛ አዳሪ አላገኘንም። አንድም ናይጄሪያዊ የለም። ይህ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው። ይሁንና ማመን ያለብን፤ በፍራንክፈርት በሴተኛ አዳሪነት የተነሳ የተጎዳች ናይጄሪያዊ የለችም ማለት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሳቢያ አደጋ ውስጥ የገቡ የሉም ማለት አይደለም። ይህ ማለት እዚህ የነበሩት ወደሌሎች ከተሞች ማለትም ወደ ሀኖቨር ፤ ሀምቡርግ ፤ እሽቱትጋርት፤ ሙኒክና ወደሌሎች የጀርመን ከተሞች ተወስደዋል ማለት ነው።»

ናይጄሪያ የመንግስታቱ ድርጅትን የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የማስቆም ስምምነት ከፈረሙ በርካታ ሀገራት አንዷ ናት። ይሁንና ግን እድሜአቸው 15 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ናይጄሪያውያን ሴቶች ህገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ጀርመንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ይጋዛሉ። በናይጄሪያ በዚህ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቩዶ በሚል ከሚታወቀው ባህላዊ የምዕራብ አፍሪካ የአስማት እምነት ጋር መረብ ዘርግተው ነው ሴቶቹን የሚወሰደቸው። በአስማቱ አፍዘውና አደንግዘው ማለት ነው። የፍራንክፈርት ፖሊስ መኮንን ማርኩስ እሽታይነር ለዓመታት ህገወጥ ከሆኑ የናይጄሪያ ሴቶች ጋር ሰርተዋል። ግን ውጤቱ ብዙም አላስደሰታቸው-- ተስፋም የሚያስቆርጥ ሆኖባቸዋል። በፖሊስ የተያዙ አብዛኞቹ ናይጄሪያዊ ሴተኛ አዳሪዎች ለፖሊስ እውነቱን መናገር አይፈልጉም። ምክንያቱም የቩዶ እምነት አንዳች ጉዳት ያመጣብናል ብለው ይፈራሉና።ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኑ እንደሚሉት ሴቶች እውነተኛ ታሪካቸውንና የገጠማቸው እንዲናገሩ ለማድረግ ትዕግስትንና ልምድን ይጠይቃል። ያን ጊዜም ነው ሴቶቹን መርዳት የሚቻለው።

ድምጽ

«አንዲት የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆነች ናይጄሪያዊ ሴት በፍራንክፈርት ፖሊስ ከተያዘች እድለኛ ነኝ ብላ ነው ማሰብ ያለባት።የሚጠበቅባት ራሷን ባህላዊው እምነት ከፈጠረባት ተጽዕኖ ማላቀቅና ለፖሊስ ትብብር ማድረግ ብቻ ነው። ያን ካደረገች በትክክለኛ መስመር ላይ ወጣች ማለት ነው። ለእኛ ይህ ግልጽ ነገር ነው። ከዚያ በኋላ እሷም ወደናይጄሪያ ተመልሳ መሄድ አትችልም።»

ፖሊስ በእርግጥ ናይጄሪያዊ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሳቢያ ወደጀርመን የመጣች ናይጄሪያዊ ወደሀገሯ ብትመለስ የሚገጥማትን አደጋ የተገነዘበ መስሏል። ለዚህም ይህቺ ሴት ከመመለስ ይልቅ በቀጥታ የፖለቲካ ጥገኝነት እንድታገኝ ያደርጋል። ይሁንና ከባዱና አስቸጋሪው ነገር ሴቶቹ ደፍረው መናገር የማይችሉ መሆናቸው ነው። ጥብቁና ጠንካራው ሃይማኖታዊ እምነት የሆነውን የቩዶን አስማትን ከምንም በላይ ይፈሩታል። ሪታ ኤክዌዛ በቩዶ አስማት በኩል እ.ኤ.አ በ2007 ወደ ጀርመን መጥታ በሴተኛ አዳሪነት ስራ የተሰማራች ናይጄሪያዊት ናት። በፍራንክፈርት ፍርድ ቤት ቀርባ ወደዚህ ያመጣት አካል ያደረሰባትን በደል ተናግራለች። ሴተኛ አዳሪ ሆና የሰራችበትን ወቅት ስትገልጽ በምሬት ነው።

ድምጽ

«እንዲህ ቆሞ የደረሰውን መናገር ቀላል አይደለም። እዚህ ሲያመጡ የሚሉት ሁሉ ነገር ጥሩ እንደሆነ እየነገሩን ነው። በቃ! ሁሉ ነገር ቀላል ይመስላል። ሆኖም የገጠመን ፈጽሞ ተቃራኒው ነው። ካሰብነው የማይገናኝ አደጋ ውስጥ ነው የገባነው። ያደረጉን ነገር በጣም ጥሩ አይደለም። የእኛ መሰቃየትና ችግር ውስጥ መውደቅ ለእነሱ ጥቅም የሚያስገኝ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። አንቺን ያመጣሉ, ጥቅሙን እነሱ ይወስዳሉ።»

ሪታ ቀደም ሲል የተነገራት እሷን አውሮፓ ለማምጣትና ለአጠቃላይ ወጪዋ 60 ሺህ ዩሮ ቲ,ተከፈለ በመሆኑ ሴተኛ አዳሪነቱን ሰርታ ገንዘቡን መመለስ እንዳለባት ነው። ለዚህም በሳምንት ሰባት ቀናት በየዕለቱ ከወንድ ጋር ተገናኛለች። የተጣለባት ዕዳ ለመክፈል አንዳንድ ጊዜ በቀን ከ18 በላይ ወንዶች ጋር ግንኙነት እንደምትፈጽ ትናገራለች። ለፖሊስ ምስጋና ይግባውና፤ እ.ኤ.አ በ2008 የፍራንክፈርት ፖሊስ ህገወጥ በማለት ካሰራት በኃላ ከስራው ጋር ተቆራርጣለች። የሴቶች መብት የሰውልጅ መብት ነው በሚል የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያደረገላት ድጋፍ ለሪታ ከቩዶ እምነት ፍራቻም ነጻ አድርጓታል። ኤልቪራ ኒስነር የድርጅቱ ሃላፊ ናቸው።

ድምጽ

«መረጃና ምክር እንሰጣለን። እሷንም በማህበራዊ ህይወቷና በስነልቦና ረገድ እንድትረጋጋ ለማድረግ እየሞከርን ነው። ስለገጠማት መጥፎ ነገር ነገሮች ትናገራለች። ስለ ተስፋዋና ችግሮቿም እንዲሁ። የሚስፈልጓት ነገሮች ይሟሉላታል። አሁን ደህንነት እየተሰማት ይመስለኛል። ያ ዋናው ነገር ነው። ለመኖር የሚያስፈልጋት ገንዘብ ከኃላፊዎቹ ታገኛለች።»

የሴቶች መብት የሰውልጅ መብት ነው የተሰኘው ድርጅት ሃላፊ ኤልቪራ ኒስነር በየዓመቱ ከ900 በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ሴቶችን ተቀብለው የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። ትልቁ ፈተና በእርግጥ አሁንም አልተወገደም። የቩዶ ባህላዊ የአስማት እምነት ወደጀርመን የሚደረገውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲቆም እየተደረገ ላለው ጥረት ዋናው መሰናክል ሆኗል። ምንም እንኳን ፖሊስ አንዳንድ የህገወጡ ዝውውር ሰለባዎችን ከአስተላላፊዎቹ እጅ ነጻ ቢያደርጋቸውም ተመልሰው ወደሴተኛ አዳሪነቱ ስራ መግባታቸውን ግን አያቆሙም። ምክንያቱም በቩዶ የአስማት እምነት አባት ፊት ቀርበው ለአስተላላፊዎቹ ለመክፈል ቃል የገቡትን 60ሺህ ዩሮ ማግኘት አለባቸውና።