1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኔፓል፤ በመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾቹ ቁጥር አሻቀበ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 17 2007

ከቅዳሜው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ዛሬም በኔፓል እና ሕንድ በሬክተር መለኪያ 6,7 የደረሰ መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተዘግቧል። በመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳ በደረሰው ጉዳት የሟቾቹ ቁጥር 2500 መድረሱ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/1FEw3
Nepal Schweres Nachbeben nach Erdbeben in Bhaktapur
ምስል Reuters/N. Chitrakar

በኔፓሉ ብርቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾቹ ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ የሀገሪቱ ታሪካዊ ሀውልቶች እና የዓለም ቅርስ ተብለው የተሰየሙ ቦታዎች መፍረሳቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል። በኔፓል የመሬት መንቀጥቀ የተነሳ በጎረቤት ሃገራት ህንድ፣ባንግላዲሽ እና ቻይና ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የህንድ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ዜና ምንጭ እንዳስታወቁት በጦሩ ተራራ ወጪዎች የ18 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል። በወቅቱ «ኤቨረስት» የተሰኘው የዓለማችን ከፍተኛው ተራራ ላይ ይወጡ የነበሩ ቢያንስ 18 ሰዎችም መሬት መንቀጥቀጡ ባስከተለው የድንጋይ መንሸራተት ተቀብረው ሞተዋል።

ከአንድ ደቂቃ በላይ የቆየው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር መመዘኛ 7,5 መለካቱን ጀርመን የሚገኝ አንድ የመሬት የምርምር ማዕከል ሲገልፅ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያ ማዕከል ደግሞ ርእደ-መሬቱ በሬክተር መመዘኛ 7,9 እንደነበር ገልጿል። ርእደ-መሬቱ ሲከሰት የኤቨርስት ተራራ ላይ የተጋገረ የበረዶ ክምር እንደ ጎርፍ እየተገለባበጠ መውረዱም ተጠቅሷል። እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ1800 እንደተገነባ የሚነገርለት ታሪካዊው ዳራሐራ የተሰኘው ማማ መውደሙ ተነግሯል። ይኽን ታሪካዊ ማማ ለመጎብኘት በቦታው የነበሩ በርካታ ሰዎች በፍርስራሹ ተውጠው ሳይሞቱ እንዳልቀረም ተዘግቧል።

Nepal Schweres Nachbeben nach Erdbeben in Kathmamdu
ምስል imago/Xinhua

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት እበበ