1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አለማቀፍ የአዝማሪ ጉባኤ

ቅዳሜ፣ የካቲት 3 2004

ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪ መለስ ቢጭኑት መኪና ቢጋልቡት ፈረስ ብሎ አዚሞአል። ማሲንቆ ተጫዋቹ እና፣ ክራር ገራፊዉ አዝማሪ፤ አገሩ የናፈቀዉን በዉጭ አገር የሚኖረዉን ኢትዮጽያዊ በዜማዉ ሲያዝናና።

https://p.dw.com/p/13m4Z
የጉባኤዉ ተሳታፊዎችምስል DW

 እንደምን ከረማችሁ አድማጮች፣ ባለፈዉ ሁለት ሳምንት እዚህ ጀርመን ሂልደስ ሃይም ከተማ ስለተካሄደዉ የመጀመርያዉ አለማቀፍ የአዝማሪ ጉባኤ የጀመርነዉን መሰናዶ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል። በጀርመን በተደረገዉ ጉባኤ ላይ አዝማሪዉ «በጦር በግንባር ያዋጋ ነበር ለሰላም ጸሎትም ያዘምር ነበር ታድያ ሲያገለግል እንደማክበር አዝማሪ በመባል ለምን ይወርወር» ብሎም ጠይቆአል። አማረኛ ቋንቋችን የጎለበተ በመሆኑ አዝማሪዉ በሰምና ወርቅ ዜማ ለህብረተሰቡ ለአስተዳደሩ መልክቱን የሚያሰማበት መሳሪያም እንደሆነ በጉባኤዉ ላይ የቀረቡት ምሁራን ገልጸዉታል። በጉባኤዉ ላይ በድሮ ግዜ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት የግላቸዉ አዝማሪዎች ማለትም ሊቀመኳስ እንደነበራቸዉ የገለጹት በዩናይትድ ስቴትስ የታሪክ ተመራማሪዉ ፕሮፊሰር ሰለሞን አዲስ ጌታሁን፤ ሊቀመኳሱ ወይም አዝማሪዉ ንጉሱን በዜማዉ ማሞካሸት ብቻ ሳይሆን፣ በጦር ሜዳ አይዞህ ብሎ የሚያዋጋ፣ ንጉሱ ወይም ባላባቱ በደል ከፈጸመ ደግሞ በመሰንቆዉ እየተጫወተ በሰምና ወርቅ ግጥሙ፤ አይገባም ተዉ እያለ ከበደሉ እንዲቆጠብ የመገሰጽም ስልጣን እንደነበረዉ ትንተናን ሰጥተዋል። በአዝማሪ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የነበሩት እና በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዙርያ ጥናት እንዳደረጉ የገለጹልን በዪናይትድ ስቴትስ ሚችገን ዪንቨርስቲ የታሪክ መምህር ፕሮፊሰር ሰለሞን አዲስ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቅማዉ ግዜ የቅድመ አብዮቱ ወቅት ሳይሆን ከአብዮቱ በኋላ ነዉ ሲሉ እንዲህ ያስረዳሉ
«ከቅድመ አብዮቱ በፊት የነበረዉን ግዜ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ነበር ይባላል። እኔ ደግሞ አይደለም በዝያ ዘመን የኢትዮጵያ ሙዚቃ በፈረንጆቹ ቅኝት ገብቶ ዲቃላ የሆነ ባህል የተወለደበት ዘመን በአማረኛችን ትዊስት የሚደነስበት ዘመን ነበር እላለሁ- ስለዚህም ወርቅማ ዘመን ነበር አልለዉም። ሁለተኛ ዘፈኑ በአብዛኛዉ አማረኛ ሲሆን የሚቀርበዉ ለነገስታቱ እና ለመኳንንቱ ብቻ ነበር። በርግጥ የፍቅር ዘፈን መዝፈን ይችል ነበር፤ ግን ለሰፊዉ ህዝብ የሚደርስ አልነበረም፣ ቴሌቭዝንም ሆነ ራድዮ በጥቂቶች እጅ ብቻ ነበር። በዚህም ለሙዚቃችን ከቅድመ አብዮቱ በፊት የነበረዉ ግዜ ወርቅማ ነበር ሊባል አይችልም ባይ ነኝ። በእኔ ግምት ካሉት አንዳንድ ተጨባጭ ማስረጃዎች አንጻር ሲታይ ከአብዮቱ በኋላ ያለዉ ዘመን ነዉ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ግዜ ሊባል የሚቻለዉ ብዪ እገምታለሁ። ለምን ብንል አንደኛ ደርግ ለራሱ ጥቅም ሲል እያንዳንዱ ቀበሌ በተለይ የብሄር ብሄረሰቦች ችግር እንገብጋቢ ስለነበር የብሄር ጥናት ማዕከል አቋቁሞ ቋንቋቸዉ ተጠንቶ እንዲማሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረበት ግዜ ስለነበር፤ ሙዚቃንም የማሳደግ አንደኛዉ እርምጃ ነበር፣ በዚህም በርካታ የኪነት ቡድንን አቋቋመ። እዚህ ላይ የኪነት አላማዉ አብዮቱን መደገፍ ነበር። የኪነት ቡድኑ አሰልጣኖች ደግሞ አዝማሪዎች እና አንዳንድ ድምጻዉያን ነበሩ። በዚህም ነዉ አዝማሪዎች በአብዮቱ ተከበሩ ማለት የሚቻለዉ። በቅድመ አብዮቱ ዘመን ከአዝማሪ ጋር መስራት እንደ ነዉር ይቆጠር ነበር»
አዝማሪ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚተገብረዉ ሞያ ብዙ በመሆኑ ለመዘርዘር አስቸጋሪ ነዉ ያለን በጉባኤዉ ለመሳተፍ ከአዲስ አበባ ከኢትዮጽያ ጥናትና ምርምር ተቋም የመጣዉ ወጣት ስሜነህ በትረዮሃንስ፣ ሙዚቃ፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮነሚ፣ ከታሪክ ባለፈ፣ ሊጠቁመን የሚችለዉን አዲስ እይታ ለማሳየት ጥረት ላይ እንደሆነ እንዲህ ይገልጻል።
«ሙዚቃ ያላየናቸዉን ለማሳየት የሚችል መነጽር አለዉ ብዪ አስባለሁ። ግዜ በሄደ ቁጥር የፖለቲካዉ የኢኮነሚ የባህል ለዉጥ ልዩነቶች በመጡ ቁጥር የአዝማሪዎች የስራ ድርሻም እንዲሁ በየግዜዉ ሲለያይ ነዉ የመጣዉ። በድሮ ግዜ አዝማሪ የከፋዉ ሰዉ፣ አልያም በአጠቃላይ የህብረተሰብ ድምጽ ነበር። የነገስታት እና የገዥዎች ድምፅም ነበር። በህብረተሰብ እና በገዥዎች መካከል የነበረዉን ፍትግያ እና የነበሩትን ቅብብሎሽ የሚያሳይ ነበር። አሁን በሚታየዉ ማህበረሰብ ዉስጥ ደግሞ እንደዚህ አይነት ድርሻዎችን አያይም ግን በዘመናዊ ሙዚቃ ባህል ዉስጥ አዝማሪዎች ራሳቸዉን በዚያ በኩል ቃኝተዉ ትልቅ ስፍራን ይዘዉ እና ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነዉ ማለት እንችላለን። በዚህም የሙዚቃ እንዱስትሪ እየጫጫ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አዝማሪዎች ያላቸዉን የፈጠራ ስራ እና ህያዉ በሆነዉ የመድረክ አቀራረባቸዉ ብዙ ነገርን እየተቋቋሙ ነዉ፣ ምሳሌ እየሆኑ ነዉ፣ የባህል አንባሳደር እየሆኑ ነዉ እላለሁ»
በጉባኤዉ ሁለተኛ ቀን አንጋፋዋን የጥበብ እንቁ አስናቀች ወርቁን በጽሁፋቸዉ ያወሱት በበርሊን ነዋሪ የሆኑት የሙዚቃ ምሁሯ ዶክተር ትምክህት ተፈራ ስለ ጉባኤዉ  
«እስከ ዛሪ ድረስ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሙዚቀኞች አለመከበር፤ የሙዚቃ አለመወደስ፤ የሙዚቃ ቦታ አለመሰጠት እና እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ በማህበረሰቡ በኩል ትክክል አይደለም በሚል አዝማሪዎቻችንን እስቲ እናወድሳቸዉ ሞያዉንም እናክብረዉ እና በዚህ አይነት መልኩ አደባባይ እናዉጣዉ በሚል አለማ ነዉ ይህ ጉባኤ ሊካሄድ የበቃዉ። በጉባኤዉ ላይ የተደረጉት ዉይይቶች እና ትምህርታዊ ገለጻዎች በሚዲያ እና በሚወጡት ጽሁፎች ለህዝብ ይፋ ስለሚሆን፤ በኢትዮጽያ ሙዚቃ በተለይም በአዝማሪዉ ረገድ እንዲጤን እና በተለይም ሙዚቀኞቻችን እና ሞያዉ መከበር እንዳለበት ትምህርት ይሰጠዋል። ይህ ጉባኤ ታድያ ለዚህ ሁሉ ጎህ ቀዳጅ ነዉ ብዪ እገምታለሁ»  

አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ባህል እንዲሁም ሙዚቃ ከጃፓን ባህልና ሙዚቃ ጋር ተመሳሳይነት ስላለዉ ጃፓናዉያን ለኢትዮጵያ ፍቅር እንዳላቸዉ የገለጸልን ጃፓናዊዉ ዶክተር ኢቱሱሺ ካዋሴ በተለይ በጎንደር ከሁለት አመታት በላይ ኖረዉ በጎንደር ያለዉን ልዩ ባህል በተለይ የአዝማሪዎችን ልዩ ቋንቋ አጥንቷል፣ በጉባኤዉ ላይም ለጥናቱ የሰበሰባቸዉን መረጃዎች አሳይተዋል። ሌላዉ የጉባኤዉ አስተባባሪ አማረኛ ተናጋሪ ጀርመናዊዉ ዶክተር አንድርያስ ቬተር የአማረኛ ቋንቋን እና አዝማሪን ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ ዉዝዋዜን እና እስክስታን ጠንቅቆ እንደሚያዉቅ በጉባኤዉ መጠናቀቅያ ምሽት ላይ በተደረገዉ የሙዚቃ ምሽት ላይ ለማየቴ ምስካሪ ነኝ። ከኢትዮጽያ የመጡት የጉባኤዉ ልኡካን በጉባኤዉ ለመገኝት ወደ ጀርመን ቪዛ መግቢያ ለማግኘት የነበረባቸዉ ችግር በአንድርያስ ትጉህነት መሳካቱን በተደጋጋሚ ገልጸዋል አመስግነዋል።

በሌላ በኩል በእስራኤል ቴላቪቭ ዉስጥ የክራር እና የማሲንቆ አጨዋወት ትምህርት የሚሰጥዉ እና የጉባኤዉ ተካፋይ የነበረዉ አዝማሪ ደጀን ማንችሎት በጉባኤዉ መደሰቱን ገልጾአል።
የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ አቶ ታደለ የድነቃቸዉ ተሰማ ከመቶ አመት በላይ የሆነዉን የጀርመን የኢትዮጵያ የወዳጅነት ግንኙነት ህያዉ መስካሪ ሆነዉ በመገኘታቸዉ በተለይ የጀርመኑን የጉባኤ አዘጋጅ ፕሮፊሰር ቤንደርን እጅግ ያስደሰተ ይመስላል። የታሪኩ ባለቤት አቶ ታደለም ታሪኩን ለምዕራባዉያኑ በእንጊሊዘኛ ፈትፍተዉ በአማረኛ ቋንቋ ደግሞ እንዲህ ነበር ያስረዱት

«የዝያን ግዜ ምኒልክ ዘመናዊነትን ከኢትዮጵያዉያን ጋር ለማስተዋወቅ የሚታገሉበት ዘመን ነበር። እነ ባቡርን፤ እነ ስልክን፤ እነ መኪናን እና ፖስታን ማለት ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ ወግ አጥባቂዉ መኳንንት እና የሃይማኖት አባቶች ደግሞ ነገሩ፣ ከሃይማኖት ያርቀናል በሚል ስጋት ላይ ወድቀዉ ነበር። እንደዉም ለማስታወስ ያህል የመጀመርያዉ ሲኒማ አዳራሽ የሰይጣን ቤት እንዳሉት ሰይጣን ቤት ተብሎ መቅረቱ ይታወቃል። ምኒልክ ተሰማን የመረጡዋቸዉ ይህን የሰይጣን ስራ እንዲሰሩ ነዉ። አንደኛዉ የሙዚቃ ሸክላን እና ሁለተኛዉ መኪናን ነዉ። በምኒልክ ዘመን መኪና የሰይጣን ነዉ በመባሉ ምኒልክ እራሳቸዉ መኪና ላይ እንዳይወጡ በቄስ ሁሉ ተለምነዉ እንደነበር ጽሁፎች ያሳያሉ። ተሰማ እሸቴ ግን በጉዳዩ ብዙ የተጨነቁበት አይመስሉም.....ሙሉዉን ቃለ ምልልስ ያድምጡ

በመጨረሻ የመጀመርያዉ የአዝማሪ ጉባኤ እዚህ ጀርመን እንዲደረግ ጥረት ያደረጉት በሃንቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዪ በማጠቃለያ ንግግራቸዉ ይህ ጉባኤ የአዝማሪ ሞያ መጠናት መታወቅ እንዳለበት ለማሳየት የተነሳንበት በመሆኑ ጥናቱም ሆነ ዉይይቱ እንደሚቀጥል ተስፋ በማድረግ በኢትዮጵያ ያሉ ዩንቨርስቲዎች እና የምርምር ተቋማት ይህንን ጥናት እንደሚቀጥሉበት ተስፋ በማድረግ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።  ሙሉዉን ቅንብር ያድምጡ!


   

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ               

Konferenz über Azmari Kultur aus Äthiopien Universität Hildesheim
የጉባኤዉ ተሳታፊዎች በዉይይት ላይምስል DW
Azmari -Konferenz Hildesheim
የጉባኤዉ ተሳታፊ አዝማሪ ኢድሪስ ሃሰንምስል DW
Azmari -Konferenz Hildesheim
የሙዚቃ ምሁርዋ ዶክተር ትምክህት ተፈራምስል DW
Azmari -Konferenz Hildesheim
የአፍሪቃ ጉዳይ ተመራማሪ እና አማረኛ ቋንቋ ተናጋሪዉ ዶክተር አንድሪያስ ቬተርምስል DW
Azmari -Konferenz Hildesheim
የታሪክ ተመራማሪዉ ፕሮፊሰር ሰለሞን አዲስ ጌታሁንምስል DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ