1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አለ በጅምላ የት አለ?

ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2008

የጅምላ ንግድ ግብይትን ለማዘመን እና የሸቀጦች ዋጋን ለመቆጣጠር የተቋቋመው አለ በጅምላ በሁለት አመታት ውስጥ ከ20 በላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ቢያቅድም ያሳካው ስድስቱን ብቻ ነው። በ1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተው ድርጅት የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠሩ ረገድም ያመጣው ለውጥ እምብዛም ነው።

https://p.dw.com/p/1J2bL
Deutschland Einzelhandel Lebensmittel im Supermarkt
ምስል picture-alliance/Rainer Hacken

አለ በጅምላ የት አለ?

አለ በጅምላ በሚል መጠሪያው የሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት ከሶስት አመታት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ በሸቀጥ ገበያ የ30% ባለድርሻ ለመሆን አቅዶ ነበር። ድርጅቱ የዋጋ ተመንን የመቆጣጠር እና ግብይቱን የማዘመን እቅድም ነበረው። አለ በጅምላ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በአነስተኛ ዋጋ በማከፋፈያዎቹ እያቀረበ ቢሆንም የዋጋ ግሽበት አሁንም በገበያው ላይ ይታያል። የኢትዮጵያ ስታስቲክ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረት በዚህ አመት የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበቱ 10.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የመጀመሪያውን የአለ በጅምላ ማከፋፈያ በመገናኛ አካባቢ ሥራ ሲያስጀምሩ አንገብጋቢውን የዋጋ ግሽበት መቆጣጠር እንደሚያስችል እና ድርጅቱ የሚያቀርባቸውን ሸቀጦች ከተፎካካሪዎቹ ከ5 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ያቀርባል ብለው ነበር።

በሶስት አመት ጊዜ ውስጥም ከፍተኛ የህዝብ ክምችት አለባቸው ተብለው በተለዩ 27 የክልል ከተሞች ውስጥ ወደ 36 የማከፋፈያ ማዕከላት ይከፈታሉ ተብሎም ነበር። ዛሬ አለ በጅምላ በመገናኛ፤መርካቶ እና ቃሊቲ የሚገኙ ሶስት የአዲስ አበባ ማከፋፈያዎችን ጨምሮ በአዋሳ፤ባህር ዳር እና ሻሸመኔ ቅርንጫፎቹን ከፍቷል።

Bio Food Obst Gemüse Regal Bioladen
ምስል picture-alliance / Rainer Hackenberg

እቅዶቹ ግን እንደታሰበው አልሰመሩም። ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር የአለ በጅምላ ኃላፊዎችን ከሥራ ማገዱን እና የህግ ጥሰት ፈጽመዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል። ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ ለተወካዮች ምክር ቤት ከሥራ ታግደዋል፤ክስም ይመሰረትባቸዋል ያሏቸውን ኃላፊዎችም ይሁን ፣ተፈጸመ የተባለውን የህግ ጥሰት ግን አልገለጡም።አቶ አብዱልመናን ሞሐመድ ሐምዛ ኢትዮጵያ ውስጥ ለስድስት አመታት በኦዲተርነት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም ፖርትቤሎ በተሰኘ ኩባንያ የአካውንቲግ ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው። አቶ አብዱልመናን በ1.5 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተመሰረተው አለ በጅምላ የንግድ ሥርዓቱን በማዘመንም ይሁን የዋጋ ግሽበቱን በመቆጣጠር ረገድ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ይተቻሉ።

በጥቂት ግለሰቦችን እና ድርጅቶች ቁጥጥር ስር ወድቋል የሚባለውን የኢትዮጵያ የጅምላ ንግድ ስርዓት ለመቀየር የመንግስት ባለስልጣናት እንደ ዎል ማርት ያሉ ተቋማትን ወደ አገሪቱ ለማስገባት አቅደው ነበር። አለ በጅምላ ሲመሰረት ኤ.ቲ. ኬርኔይ (AT Kearney Inc.) የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ድርጅቱን የማቋቋምና የማደራጀት ሃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ኩባንያው በወቅቱ ይፋ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ከውጭ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ ከሚገባው በ50 በመቶ ጭማሪ ተደርጎባቸው ለገበያ እንደሚቀርቡ አለ በጅምላ ይህን የግብይት ሥርዓት ማስተካከል አልቻለም። አቶ አብዱልመናን ሞሐመድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ድርጅቱን ሲመሰርቱ የገበያውን ባህሪ በቅጡ እንዳልተረዱት ይናገራሉ።

አለ በጅምላ በአላማውም ይሁን በአወቃቀሩ በ1985 ዓ.ም. ከተመሰረተው የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) ልዩነት የለውም። ሸቀጦችን ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገር መግዛትና በጅምላ መሸጥ፤ የማከፋፈል፤ እና ገበያን ማረጋጋት ስራው ያደረገው ጅንአድ 83 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን እንደ አለ በጅምላ ሁሉ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው። አቶ አብዱልመናን በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታየው ቢሮክራሲ እና ፖለቲካዊ ቁጥጥር ለአለ በጅምላ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

Paradoxes Indien verrottendes Getreide im Angesicht des Hungers
ምስል DW

አለ በጅምላ ሲመሰረት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በግብይቱ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ መንግስት ከንግድ ስርአት ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት ሲሉ ተደምጠው ነበር። ለዘመናት የሃገሪቱን የጅምላ ንግድ ሲመራ የቆየው ጅንአድ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። አቶ አብዱልመናን የኢትዮጵያን የጅምላ ንግድ ስርዓት ለማዘመን አለ በጅምላ ሁነኛ አማራጭ አይደለም የሚል አቋም አላቸው። ባለሙያው በውስብስብ እና ዘገምተኛ የቢሮክራሲ ሥርዓት ውስጥ የተመሰረተው አለ በጅምላ ከግል አስመጪዎች ጋር መወዳደር አይችልም ሲሉ ይናገራሉ።

አለ በጅምላ ከተመሰረተ ጀምሮ ለሶስት አመታት አካባቢ በሥራ አስፈጻሚነት የመሩት አቶ ኑረዲን መሐመድ ተነስተው በቦታው ወ/ሮ ሲትራ አሊ ተሾመዋል። አቶ ኑረዲን መሐመድም ሆኑ ወ/ሮ ሲትራ አሊ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ለማድረግ ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። አቶ አብዱልመናን የአለ በጅምላ መጻዒ እጣፈንታ ብሩህ እንዳልሆነ ያምናሉ።
ባለሙያው የኢትዮጵያ የጅምላ ግብይትን ለማዘመን ከአጭር ጊዜ ይልቅ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። እንደ እርሳቸው ከሆነ መንግስት በግብይቱ ውስጥ የሚኖረው ተሳትፎም ይሁን የሚያደርገው የዋጋ ቁጥጥር ለውጥ አያመጣም።

እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ