1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፋር አማራ ድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቷል

ረቡዕ፣ መስከረም 10 2010

በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተው ግጭት ሰሞኑን ዳግም አገርሽቷል፡፡ ግጭቱ ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ሰሜን ጎንደር ዉስጥ ባለፈዉ ዕሁድ ሕዝበ ዉሳኔ በተደረገበት አካባቢ በተነሳ ግጭት የሰዉ ሕይወት መጥፋቱ ተዘግቧል። 

https://p.dw.com/p/2kOka
Äthiopien Afar trockene Landschaft
ምስል DW/G. Tedla

በአፋር አማራ ድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቷል

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት መስከረም ከጠባ ጀምሮ ሰላም አላገኙም፡፡ ከአፋር ክልል ጋር ኩታ ገጠም በሆኑ አካባቢዎች ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲግም ሲቀዘቅዝ የቆየው የወሰን ግጭት ዳግም አገርሽቶ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የሰሞኑ ግጭት የተቀሰቀሰው መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ትላንት ምሽት በአካባቢው ተኩስ ይሰማ እንደነበር ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቼ ቨለ ተናግረዋል፡፡ 

“ግጭቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ አሁንም ትላንትም ተኩስ ነበር፡፡ ከትላንት በስቲያም ተኩስ ነበር፡፡ ያው ከባድ የተኩስ ልውውጥ አለ፡፡ ትላንትና ማምሻ ከሁለት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት የተኩስ ልውውጥ ነበረ፡፡ ያው በሁለቱም ወገን ግን የሞተ የለም፡፡ ከአፋር ወገን ግን አንድ አራት የቆሰለ ሰው አለ” ይላሉ ነዋሪው፡፡ 

ግጭቱ የደረሰበት ቦታ ጃራ ተብሎ የሚታወቅ እና ከወልዲያ ወደ አሳይታ በሚወስደው መስመር ላይ ባለ ቦታ እንደሆነ ነዋሪው ያስረዳሉ፡፡ ትላንት አምቡላንስ በአፋር ወገን የቆሰሉትን ሰዎች ሲያመላልስ እንደነበር ከጭፍራ ከተማ ነዋሪዎች መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የሚያረጋግጡት ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አካባቢው “አለመረጋጋቱን” እና በአማራ እና አፋር ወገን ያሉ ሰዎች በ“አፈ ሙዝ ፍጥጫ ውስጥ” እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ በሰሞኑ ግጭት ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ እኚሁ ነዋሪ ይገልጻሉ፡፡

“መስከረም 2 በሀብሩ ወረዳ የቁጥር 24 ነዋሪ ነው፡፡ ስሙን አልያዝኩም፡፡ አንዱ ቁጥር 23 ነው፡፡ ያሲን ይባላል፡፡ የአራት ልጆች አባት ነው፡፡ ያሲምን መሀመድ የሚባል ዕድሜው ወደ 30 የሚጠጋ ከዚያ ድንበር ላይ ወርዶ ከብት እያበላ ከከብት ላይ መጥተው ወድቀው ከብቶቹን ገድለው ሄደዋል በ[መስከረም] ሁለት፡፡ መስከረም አራትም ያሲን ደባስ ይባላል፡፡ እዚያው ቁጥር 24 ነዋሪ ድሬ ሮቃ የምትባል ነዋሪ ነው፡፡ ከብት እያበላ ነው ሊታጠብ ከወንዙ በርከክ ሲል መጥተው አላያቸውም ገድለውት ጥለውት ሄደዋል፡፡ ያን ተከትሎ በዚያ ምክንያት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ነው ሰኞ ለማክሰኞ ንጋት አማራው ወደ አፋሩ ሄዶ ድንበራቸው ላይ ገብቶ ተኩሶ መጥቷል ነው የሚሉን፡፡ መንግስት ግን ይህንንም እያየ ዝም ብሎ ነው ያለው፡፡ አሁንም ነገ ከነገ ወዲያ ይሄ ነገር ዋስትና የለውም፡፡ መደገሙ አይቀርም” ብለዋል ነዋሪው፡፡ 

ነዋሪውን “መደገሙ አይቀርም” ያስባላቸው ለግጭቱ መፍትሄ ተበጅቶለታል ከተባለ በኋላ የሰዎች ህይወት መጥፋት መቀጠሉ ነው፡፡ ባለፈው ግንቦት ወር በዚያው በሀብሩ ወረዳ በተነሳ ግጭት 12 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ባለፈው ነሐሴ እንዲሁ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ሞተዋል፡፡ የሁለቱን ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች እንዲህ እያቆራቆዘ ያለው የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ የሀብሩ ነዋሪ በዚህ ይስማማሉ፡፡ “ትልቁ ችግር የድንበር ነው፡፡ በድንበር ይገባኛል ነው፡፡ ድንበር አላካልልም በማለት ነው የሚጋጩት፡፡ ጭፍራ በፊት በደርግ ጊዜ ወደ ሀብሩ ወረዳ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ አፋር ክልል ስለወሰደው በዚያ ድንበር ግጭት ነው አፋሮችም አናስወስድም እያሉ እዚያው ገበሬው መኖሪያ መንደር ድረስ ነው እየገቡ ነው ውጊያ የሚያካሄዱት” ሲሉ መንስኤውን ያስረዳሉ፡፡

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው የሁለቱ ክልሎች ተወላጆች ከድሮ ጀምሮ በግጦሽ ሳር ምክንያት ይጋጩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ግን ግጭቱን ያባባሰው የድንበር ይገባኛል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ነገሮች እየተካረሩ ከመምጣታቸው የተነሳ በበቀልን ስጋት በአፋር ክልል ጭፍራ ከተማ ወዳለ የገበያ ቦታ መሄድ እንደተው ይናገራሉ፡፡ ከጅቡቲ ወደ መቀሌ በሚወስደው መንገድ የአፋር መኪኖች መጓጓዝ ማቆማቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀለት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል የተፈጠረው ሁኔታ በአካባቢያቸው እንዳይከሰት ይሰጋሉ፡፡ 

“እንግዲህ ይህንን መፍትሄ ለማግኘት የመንግስት ድርሻ ነው፡፡ ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ካላገኘ በእርቅ የሚፈታ ካልሆነ በስተቀር እየሰፋ ሄዶ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ያለው ችግር ይፈጠራል የሚል ስጋት ማህበረሰቡ የሚያወራው፡፡ ግን ይህን ነገር የሚመለከተው አካል ገብቶ ካልፈታው በስተቀር ሁለቱ ክልሎች ሊፈቱት አልቻሉም፡፡ ያው ኢህአዴግ አደረሰባቸው እያለ እየቀጠለ ነው፡፡ ነገም ከነገ ወዲያም እንደው ስጋት ነው፡፡ ጥይት ይተኮሳል? ሰው ይሞት ይሆን? ሰላም ይውላል ወይ? ሰው የሚጠያየቀው ይህን ነው እንጂ ከመሀከላቸው ላይ ምንም ዓይነት መፍትሄ የለም፡፡ ሊያረጋጋ የገባ የለም፡፡ ብቻ ከገፉ ያም ተኩሶ ይህም ተኮሶ መጋደል ነው” ይላሉ በተስፋ መቁረጥ ስሜት፡፡ 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የቅማንት አስተዳደር ህዝበ ውሳኔ ታቅዶባቸው ሳይካሄድ ከቀረባቸው ቀበሌዎች አንዱ በሆነው ገላ ድባ ሶስት ሰዎች ሰኞ መስከረም 8 ምሽት መገደላቸው ተነግሯል፡፡ በመተማ ነጋዴ ባህር በተባለ አካባቢም እንደዚሁ አንድ ሰው መገደሉ ተገልጿል፡፡ በጭልጋ ገላ ድባ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስ ቡክ ይፋዊ ገጻቸው አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ሰዎቹ የሞቱት “በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ዕለታዊ ግጭት ነው” ሲሉ ጉዳዩ ከህዝበ ውሳኔው ጋር የማይገናኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ