1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያማማቶ የአሜሪካ እና አፍሪካ ግንኙነት ጠንካራ ነው ይላሉ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 12 2010

“ለአፍሪካ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው?” በሚል የሚተቸው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ለመቀየር ያለሙ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ጥረቶች መካከል አንዱ የሆነው 37 የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት ስብሰባ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2o13w
Donald Yamamoto (L)
ምስል picture-alliance/dpa/J. L. Scalzo

ያማማቶ የአሜሪካ እና አፍሪካ ግንኙነት ጠንካራ ነው ይላሉ

ዶናልድ ያማማቶ በዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተከበረ ስም ካላቸው ዲፕሎማቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ላለፉት 37 ዓመታት በውጭ ጉዳይ መስክ የሰሩት ያማማቶ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ እና እስያ በተለያዩ ቦታዎች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ አብዛኛውን የስራ ዘመናቸውን ያሳለፉት ግን በአፍሪካ በአምባሳደርነት ነው፡፡ ዋሽንግተን በሚገኘው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኃላፊነት ባገለገሉባቸው ወቅቶችም በአፍሪካ ጉዳይ ወሳኝ ሰው ነበሩ፡፡ 

በጆርጅ ደብልዩ ቡሽ እና ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን የተሾሙበት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃላፊነት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም ተከትሏቸዋል፡፡ “ለአፍሪካ እምብዛም ትኩረት አይሰጥም” በሚል የሚተቸው የትራምፕ አስተዳደር ያማማቶን ለአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊነት ለዚያውም በጊዜያዊነት የሾመው ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ከተከረከቡ ዘጠኝ ወር በኋላ ነው፡፡ ያም ሆኖ ስለአህጉሪቱ ከፍ ያለ ዕውቀት እና ሰፊ የስራ ልምድ ያላቸውን ሰው ዘግይቶም ቢሆን በቦታው ላይ መመደቡ በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ እንደ “በጎ እና ለውጥ አምጪ እርምጃ” ተወስዷል፡፡  

ያማማቶ ወደ ቦታው ከመጡ በኋላ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍ ብለው መነሳት ጀምረዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው መስከረም በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን የአፍሪካ መሪዎችን ምሳ ጋብዘው አነጋግረዋቸዋል፡፡ ትራምፕ በአፍሪካ ላይ ስለሚከተሉት ፖሊሲ ፍንጭ በሰጡበት በዚህ ግብዣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ 

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ስብሰባ ላይ ቃል እንደገቡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን በቀጣዩ ወር ጥቅምት ጎብኝተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ጋባዥነት 37 የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች በዋሽንግተን ዲሲ ተሰብሰበው ነበር፡፡ ህዳር 8 እና 9 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው ከዚህ ስብሰባ ጀርባ የዶናልድ ያማማቶ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ያማማቶም ስብሰባውን እስከዛሬ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ከተሳተፉባቸው “በጣም ውስብስቡ እና ጥልቅ የሆነ የተቀናጁ ጉዳዮች” የተስተናገዱበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ ገና ይፋ ባታደርግም በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ ማለቁን ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ስብሰባ አስመልክቶ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ያማማቶ የአሜሪካ እና አፍሪካ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ላይ ለውጦች ይኖር እንደው ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ 

USA Treffen zwischen US Staatssekretär für afrikanische Angelegenheiten  mit der Afrikanischen Union
ምስል DW/M. Cura

“ለውጥ አልለውም፡፡ ይልቅስ አጽንኦት የተሰጣቸው ጉዳይ አሉ፡፡ [ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር] ቶም ሻነን የአሜሪካንን መንግስት ወክለው በአሜሪካ የሰላም ተቋም ባለፈው መስከረም ንግግር ባደረጉበት ወቅት ስለአራቱ ምስሶዎች ማለትም የኤኮኖሚ ዕድገት፣ ጸጥታ፣ ንግድና የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንደዚሁም ትምህርት አንስተው ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የመጣው ጉዳይ እና እዚህም ያለው ጭብጥ የወደፊቷን አፍሪካ  መመልከት ነው፡፡ ከ2050 እስከ 2100 ዓ.ም የአፍሪካ ህዝብ ቁጥር ከ2.2  ቢሊዮን እስከ 2.4 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ ከእዚህ ውስጥ 70 ከመቶው ከ30 ዓመት በታች ይሆናል፡፡ ነገር ግን እዚህ ጋር የሚመጣው ጥያቄ ለስራአጥነትን መፍትሄ ለመስጠት ከአፍሪካ ህብረትም ሆነ ከአጋር የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመስራት ፖሊሲዎችን እያዘጋጀን ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና ለወጣቶች ዕድሎችን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በራሱ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው” ሲሉ ያማማቶ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ያማማቶ ከዶይቼ ቬለ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚኖራት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስተማማኛ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም የትራምፕ አስተዳደር በበርካታ ዘርፎች የተገበረው የበጀት ቅነሳ በአፍሪካ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አልሸሸጉም፡፡ “እንግዲህ በአጠቃላይ የ2018 ዓም በጀታችንን አስመልክቶ ለህግ መወሰኛ ምክር ቤት ትንታኔ አቅርቤ ነበር፡፡ ቅነሳ እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበናል፡፡ ነገር ግን በእርዳታ እና በመዋዕለ ንዋይ ጉዳዮች ያለው ምጣኔ አልተቀየረም፡፡ የጤና አጠባበቅ 81 ከመቶውን እንደያዘ ሲቆይ ሰላም እና ጸጥታ ሰባት ከመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ለትምህርት፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፓወር አፍሪካ እና የወጣቶች አፍሪካውያን መሪዎች እቅድ (YALI) በዚሁ መልኩ ምጣኔያቸውን እንደጠበቁ ይቆያሉ፡፡ ነገር ግን መጠኑ ይቀንሳል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡    

በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቁልፍ ቦታ ያላቸው ያማማቶ ለኢትዮጵያውያ ጉዳዮች እንግዳ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ ያለፉት 15 ዓመታት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ናቸው፡፡ ሀገራቸውን ወክለው ለሶስት ዓመት በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ከዚያም አስቀድሞ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ግንኙነት ዋናውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ የ1997 ዓ ም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለመፍታት ከዋሽንግተን አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ተመላልሰዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ