1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው በየቦታው ተጠልለዋል

ሰኞ፣ ጥቅምት 13 2010

በኦሮሚያ ክልል በኢሉባቡር አካባቢ ባሉ ወረዳዎች ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በነበሩ ግጭቶች ሰዎች ሞተዋል፡፡ በግጭቶቹ በርካቶች ከቤት መጠለያቸው ተፈናቅለው እርዳታ እየጠየቁ ነው፡፡ በስፍራው ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን የአካባቢው እና የክልል ባለስልጣናት ቢገልጹም ትላንት ጭምር ቤቶች መቃጠላቸውንና ውጥረት እንደሰፈነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2mN43
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

አሳሳቢዉ የኢሉባቡር አካባቢዉ ግጭት

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኘው ዴጋ ወረዳ ከሰሞኑ ስማቸው ተደጋግሞ ከሚነሳ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አንዷሆናለች፡፡  ከበደሌ ከተማ በመኪና የአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ርቀት ላይ በምትገኘው በዚህች ወረዳ አጎራባች የሆኑት ጮራ እና መኮ ወረዳዎችም እንዲሁ የብዙ ኢትዮጵያውያን ትኩረት አርፎባቸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ በሚገኙት በእነዚህ ወረዳዎች ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ የነበሩ ተቃውሞዎች እና ግጭቶች አሁንም ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ይፋዊ መረጃ መሰረት በሶስቱ ወረዳዎች ብቻ 11 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ከሟቾቹ ውስጥ አብዛኞቹ የዴጋ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አቶ ካሳሁን አለሙ የወረዳው የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ በወረዳዎች የሞቱ እና የቆሰሉ እንዳሉ ያረጋግጣሉ፡፡ “እኛ አካባቢ አሁን ህይወቱን ያጣው በተጨባጭ ያለው 10 ሰው ነው፡፡ የቆሰለ፣ በመታከም ላይ ያሉት በተጨባጭ ወደ ስምንት የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ቆስለው ሌላ ቦታ ካለ ደግሞ ያው በማፈላለጉ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” ይላሉ ኃላፊው፡፡   

Symbolbild Kerze Flamme
ምስል Colourbox

በእርሳቸው ጽህፈት ግቢ ውስጥ ተጥልለው ስለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡ “በቁጥር ወደ 600 ይሆናሉ፡፡ አሁን እነዚህ ከዴጋ ከተማ የወጡ ሰዎች አሉ፡፡ ከተለያየ የገጠር ቀበሌ የመጡ ሰዎች ናቸው ያሉት፡፡ ወደ አምስት ቀበሌ ነው፡፡ በተፈጠረው አለመረጋጋት የተፈናቀሉ ስለሆኑ ለጊዜው እዚሁ ተጥልለው አሉ፡፡ በወረዳው አቅም የተደረገው የአካባቢውን ህዝብ በማስተባበር ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ አሁን ከዚህ ችግር መፍትሄ ለመሆን ደግሞ የአካባቢውን ህዝብ አወያይተን ፣ወደ መንደራቸው እንዲመለሱ፣ የጸጥታው ነገር እየተረጋጋ ስለሆነ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ ነው” ይላሉ አቶ ካሳሁን፡፡  

አቶ ካሳሁን ችግሮ የተፈጠረባቸውን ቀበሌዎች መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና አድማ በታኝ ፖሊስ ተከፋፍለው ጸጥታውን እየተቆጣጠሩ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በቀበሌዎቹ የጸጥታ ኃይሎች ከገቡ በኋላ አካባቢው መረጋጋቱን ይገልጻሉ፡፡ ዴጋ ወረዳ ካሏት 16 የገጠር ቀበሌዎች አንዱ በሆነው ዱከቺ ኩሳዬ ለህይወታቸው ፈርተው በጫካ ተጥልለው የነበሩ ሰዎችን የክልሉ ልዩ ኃይል ማውጣቱን ይናገራሉ፡፡ “ዱከቺ ኩሳዬ የሚባል ቀበሌ ላይ ያው ልዩ ኃይል ገብቶ ሰዎቹን አውጥቷቸዋል አሉ፡፡ ወደ 91 የሚሆኑ ሰዎች ካሉበት ወጥተው ወደ መንደር ተሰባስበው በአካባቢው ህብረተሰብ እዚያው ባሉበት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው” ብለዋል የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ፡፡       

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አዶሳ ቦሩ በተባለ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብም በዱከቺ ኩሳዬ ያለው የጸጥታ መደፍረስ ወደነበረበት እየተመለሰ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም አጎራባች በሆነው ጮራ ወረዳ በትላንትናው ዕለትም ችግሮች እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡ በወረዳው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ ያለመጠለያ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡   

“በዴጋ ወረዳ በዱከቺ ኩሳዬ የተባለው በዚሁ ወረዳ ውስጥ ያለው ከሁለት ቀናት በፊት ካለው ሰላም ትንሽ ለውጥ አለው፡፡ ደህና ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተቻለ መጠን መከላከያዎችም፣ የክልል አድማ በታኞችም ያው እንቅስቀሴ እያደረጉ ነው ማለት ነው፡፡ ትንሽ ከበፊቶቹ ለውጥ አለ ማለት ይቻላል፡፡ አሁንም ቢሆን በጮራ ወረዳ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ጮራ ወረዳ በጊፎ፣ ዲገዛ እባ ጊፎ ኮርቦ የተባሉ ቀበሌዎች አዳሩን በዚያ ቀበሌ ሌይ ቤቶች ሲቃጠሉ አድረዋል፡፡ ትላንት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል እዚያ ቀበሌዎቹ ጊፎጊደጃ፣ ጊፎ ኮርቦ፣ ጨረቼ፣ ስሬጪጩት የሚባሉ ቦታዎች ትላንትና ለሊቱንም ቀኑንም እንደዚህ ዓይነት ቃጠሎ ነበር፡፡ እና ያው የሰው ሞት የለም፡፡

በጮራ ወረዳ  በትላንትናው ዕለት ህይወቱ ያለፈ ሰው የለም፡፡ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ድብደባዎች አሉ፡፡ በጮራ ወረዳ አባጎሮ በምትባል ቀበሌ ብዙ ህብረተሰብ ያለምንም አጥር እና ያለምንም መጠለያ  ሄደው ከገጠር የሰፈሩት፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች ደውለው እንደነገሩኝ ግምቱ ወደ ሁለት ሺህ የሚሆን ህዝብ ነው የሚሆነው፡፡ እና እነዚህ ሜዳ ላይ፣ ብርድ ላይ ያደሩት፡፡ የተወሰኑትን ከመሸ በኋላ በተቻለ መጠን መከላከያዎችም፣ ህብረተሰቡን አስተባብረው የተወሰኑ ቤቶችን፣ ነጋዴዎችን ለምነው ወደ ውስጥ ያስገቡት አለ፡፡ ይሁን እንጂ ከህዝቡ ብዛት አንጻር ይህን ሁሉ ህዝብ የሚችል ቤት ስለሌለ ወደ ጮራ ወረዳም በመኪናዎች ለሊት ያጓጓዙት አለ ብለው ነው የነገሩኝ” ሲሉ እማኝነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

እኚህ ነዋሪ “ቤት ንብረቴን፣ ቀዬን ለቅቄ የትም አልሄድም” ብለው ይቀመጡ እንጂ ከሰሞኑ በአካባቢያቸው በነበረ ተቃውሞ ተጠቂ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አንድ ሔክታር የሚሆን ቡና በተቃዋሚ ሰልፈኞቸች እንደወደመባቸው ገልጸዋል፡፡ የተቃውሞው መነሻ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት የደረሰው ጉዳት እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ በሰልፎች ላይ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን እና ብሶቶችንም ይዘረዝራሉ፡፡

“መነሻው በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል [በነበረው ግጭት] ስለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ነው፡፡ ወያኔ ነው የሚሉት እንግዲህ፡፡ ‘ወያኔ ኦሮሞን ከሶማሌ እንዲህ አድርጎ አፈናቅሎ፣ አንድ ነገር ሳያስተካክል ወይም የማረጋጋት ስራ ሳይሰራ የፌደራል መንግስት ጫና አድርጎብናል ስለዚህ ፌደራል የሚባል አንፈልግም፤ የታሰሩት ይፈቱ እነ መረራ፣ እነ በቀለ ገርባ ሌሎችም እያሉ፤ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ይኑሩልን፣ ለማ የእኛ ነው፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ይቆይልን ይኑርልን፤ ይሄ የኦሮሚያ ምድር መሬቱ የእኛ ነው፣ ኦሮሚያ የእኛ ናት’ የሚሉ መፈክሮች ነበሩ” ሲሉ የተቃውሞውን አነሳስ ያስረዳሉ፡፡  

ይህንን ገለጻ ሌላ የአካባቢው ነዋሪም ያጠናክራሉ፡፡ ችግሩ የተቀሰቀሰው ባለፈው ሐሙስ በዴጋ ከተማ እንደነበር እና በቀጣይ ቀናት ወደ ገጠር ቀበሌዎች እንደተዛመተ ይናገራሉ፡፡ የገጠር ነዋሪ እንደሆኑ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ በእርሳቸው ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን በአካባቢው ግን ቤቶች ሲቃጠሉ እና ንብረት ሲወድም መመልከታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቅዳሜ ዕለት በአካባቢያቸው የሶስት ሰዎች ቀብር ተፈጽሟል ይላሉ፡፡ 

“የኦሮሞ ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ወጣን ብለው ተሰለፉ፡፡ አሁን ሲሰለፉ እንዳለ ወጣቱ ጭፈራ ሲደልቅ በከተማ መሐል ጭፈራውን ተውና እንደገና ሱቅ የተባለን መጋዘን የተባለን እንክትክት አድርገው ሰብረው ንብረቱን አወደሙ። እንደገና ደግሞ ሐሙስ ደግሞ አዳር በገጠር ገቡ። በገጠር ገቡ በገጠር ደግሞ የዛን ጊዜ ብዙ ንብረት ሲያወድሙ አደሩ። አሁን ደግሞ ጁምዓ ደግሞ እንደገና ተመልሰው ከከተማው ያን ድርጊት ሲፈጽሙ ዋሉ” ሲሉ የዓይን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ሁለቱም ነዋሪዎች በአካባቢው ተጋብተው፣ ተዋልደው ለረጅም ጊዜ ኖረዋል፡፡ ሰሞኑን የተፈጸመው ድርጊት ግራ እንዳጋባቸው ይገልጻሉ፡፡ ለደረሰው ሞት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት የአካባቢው ባለስልጣናትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በመንግስት በኩል መደረግ ያለበት የሚሉትን አንደኛው ነዋሪ እንዲህ ይጠቆማሉ፡፡ “እንግዲህ መደረግ ያለበት በመንግስት በኩል አሁን የመጡት የጸጥታ አካሎች ህብረተሰቡን መስማት አለበት፡፡ አሁን ለምሳሌ ችግር ያደረሱ ሰዎች፣ እነዚያ መሪ ተብለው፣ ትጥቅ ታጥቀው፣ ህዝቡን ሲያዘርፉ ሲያስገድሉ የነበሩት ሰዎች በአንደኛ ቁጥር እየለቀመ ህጋዊ እርምጃ ቢወስድ አሁንም ጉዳዩ ይረጋጋል፡፡ ንብረት ያወደሙት በተቻለ መጠን ህጉ እና ህገ መንግስቱ በሚለው መንገድ በህጋዊ መንገድ [ቢጠየቁ] የሚል ሀሳብ አለኝ” ይላሉ፡፡      

የዴጋ ወረዳ የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊው አቶ አቶ ካሳሁን ለዚህ የነዋሪው ጥያቄ ምላሽ አላቸው፡፡ ጥፋት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋል መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ማንነታቸው ግን ወደፊት የሚጠራ ይሆናል ብለዋል፡፡ “ወደ 22 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች (አጥፊዎች ናቸው ማለት አይቻልም) ለጊዜው እስኪጣራ ድረስ ተይዘዋል፡፡ ይሄ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሎ የሚሰራ ይሆናል፡፡ አጥፊዎቹ ከየትኛው የህብረተሰብ ክፍል፣ ከየትኛው የመንግስት አካል ነው የሚለውን ነገር ግን ያው እጃችን ሲገባ እና ተጣርቶ ሲቀርብ [መልስ] መሰጠት የሚቻል እንጂ እነዚህ አካላት፣ እነዚህ ሰዎች፣ እነዚህ ተቋማት እና የመንግስት ኃላፊዎች ናቸው ብሎ ማለቱ አሁን ባለንበት ደረጃ የሚቻል አይደለም፡፡ እርሱን ለወደፊት በተጣራ ሁኔታ ማቅረብ ይቻላል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡  

Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በቡኖ በደሌ ዞን በአጠቃላይ 43 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል ብለዋል፡፡ በአካባቢዎቹ ሰልፎች ሲካሄዱ እንደነበር የተናገሩት አቶ አዲሱ“ ሰልፎቹ በሰላም እንዳይጠናቀቁ ስምሪት የወሰዱ አካላት” ነበሩ ይላሉ፡፡ 

“የኦሮሞን ህዝብ ለማስጠበቅ ያሉን የፖለቲካ፣ የኦኮኖሚ፣ የማህበራዊ ተጠቃሚነት ጉዳዮችን በማንሳት በመነጋገር ተቃውሞም፣ ድጋፍም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ገልጾ ከዚያ በኋላ ከሚመለከታቸው አካል ተነጋግሮ፣ ችግርን ለመፍታት ያለመ ሳይሆን ሆን ተብሎ ወደ ግርግር፣ ሁከት፣ ረብሻ አምርቶ በሚፈጠረው ግርግር እና ሁከት የሰው ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ የማድረግ ነው፡፡ ያ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ደግሞ ክልሉ ቀጣይነት ባለው፣ በማያቋርጥ ሁከት እንዲናጥ በማድረግ ለኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ለዘራፊዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ነው የሚመስለው፡፡

እንግዲህ አሁን በቁጥጥር ስር እያዋሉ ያሉ አካላት ወደ ምንጩ ይወስዱናል ብለን ነው የምናምነው፡፡ በተለያየ መንገድ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ፡፡ ትላንትናም የአምቦ ከተማ ፎሌዎች ይህን ነገር በመቀስቀስ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም ቡኖ በደሌ አካባቢ እንደዚሁ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይሄን በምርመራ፣ ሙያዊ በሆነ መንገድ የክልሉ ፖሊስ አጣርቶ፣ ምንጩን መነሻውን፣ ከየት ተነስቶ ወደየት እየሄደ እንደሆነ፣ እነዚህን ያሰማራ አካል ካለ ማን እንደሆነ በዝርዝር ወደፊት ለህዝብ እናሳውቃለን፡፡ አሁን ግን የማጣራት ስራው ስላልተጠናቀቀ ይሄ ነው ብሎ ለመግለጽ ለጊዜው ያስቸግረናል፡፡ ፖሊስ አጣርቶ እንደጨረሰ ለህዝባችን የምንሳወቅ ነው የሚሆነው” ሲሉ አቶ አዲሱ ቃል ገብተዋል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ