1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የደቡብ ሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 9 2006

በደቡብ ሱዳን ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ጦር እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር በሚመሩ ዓማፅያን መካከል የቀጠለው ውጊያ እና ያስከተለው መዘዝ የአካባቢው ሃገራት መረጋጋትን እንዳያናጋ ማስጋቱ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/1C1Uh
ምስል Reuters

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እአአ ለ2015 ዓም ታቅዶ የነበረውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ወደፊት ለመግፋት እንደሚፈልጉ ከጥቂት ቀናት በፊት አስታወቁ።

የሀገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ እንዳስረዳው፣ ለዚሁ ፍላጎታቸው ፕሬዚደንቱ የሰጡት ምክንያት ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ውዝግብ ባመሰቃቀላት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ በፊት ብሔራዊው ዕርቀ ሰላም ለማውረድ የተጀመረውን ጥረት ማነቃቃት ይገባል የሚል ነው። ፕሬዚደንት ኪር በዝርቡ በሀገሪቱ ያሉትን ፓርቲዎች በጠቅላላ የሚያቅፍ አንድ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ቃል ገብተዋል።

ይሁን እንጂ፣ የኪር ተቀናቃኝ የሆኑት የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት እና አሁን በሀገሪቱ በመንግሥቱ አንፃር የሚዋጉት ዓማፅያን መሪ ሪየክ ማቸር ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ወደ ሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የሚያስፈልግበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ነው ያመለከቱት። የሳልቫ ኪር የሥልጣን ዘመን ሲያበቃ የሀገር አመራሩን ስራ ለመያዝ እንደሚፈልጉ የሚነገርላቸው ማቸር ሀገሪቱን እዚህ ቀውስ ውስጥ ያስገቡት ሳልቫ ኪር በመሆናቸው ሥልጣኑን መልቀቅ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። ይኸው የፕሬዚደንቱ ሀሳብ የቀረበው የመንግሥት ጦር ኃይላት እና ዓማፀያን መሪዎቻቸው ከዘጠኝ ቀናት በፊት በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን አዲስ የተኩስ አቁም ደንብ እና የሽግግር መንግሥት ምሥረታን ያጠቃለለውን ውል በመጣስ ውጊያውን በቀጠሉበት እና የአምሥት ወራቱን ውጊያ ያበቃል በሚል ተፈንጥቆ የነበረውን ተስፋ መና ባደረገበት ጊዜ ነው።

Südsudans Präsident Salva Kiir Mayardit
ምስል Reuters

በተለይ ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ በነዳጅ ዘይት ሀብት በታደሉት የአፕር ናይል እና በዩኒቲ ግዛቶች በመንግሥቱ ጦር እና ባማፅያኑ መካከል ውጊያው ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን የጦሩ ቃል አቀባይ ፊሊፕ አግዌር እና ያማፅያኑ ቃል አቀባይ ሉል ሩዎይ ኳንግ አስታውቀዋል። አሁን ወደ ስድስተኛ ወር የተሸጋገረው ውጊያ ያፈናቀላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ውዝግቡ ባፋጣኝ እልባት ካልተገኘለት በስተቀር፣ የረሀብ አደጋ ስጋት ተደቅኖባቸዋል።

ውሉ ለተጣሰበት ድርጊት ተቀናቃኞቹ ወገኖች አሁንም አንዱ ሌላውን በመውቀስ ላይ ይገኛል። ሁኔታዎች እንዲህ መቀጠላቸው አሳሳቢ መሆኑን በደቡብ ሱዳን የቀድሞው የተመድ አስተባባሪ ፒተር ሹማን ገልጸዋል።

« ካሁን ቀደም እንደተጣሱት ስምምነቶች እንደማይሆን ተሰፋ አደርጋለሁ። ግን ወቅታዊው ሁኔታ እምብዛም የሚያበረታታ አይደለም። እንደሚታወሰው ፣ በርካታ፣ ለምሳሌ፣ የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙንን፣ የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪን የመሳሰሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትጁባን ጎብኝተዋል። እና እንደሚመስለኝ በጁባ በሚገኘው የደቡብ ሱዳን መንግሥት አመራር ላይ የሰላሙን ስምምነት እንዲፈርም ትልቅ ግፊታ ሳያርፍበት አልቀረም። ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ትልቅ ግፊት አርፎባቸዋል የሚሉ አንዳንድ ዘገባዎችም ወጥተዋል። እና ለማለት የምፈልገው፣ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል በቅን መንፈስ ድርድር አልተካሄደም፣ በመሆኑም፣ አሁንም እንደገና የምናየው ተቀናቃኞቹ ወገኖች የቀጠለው የኃይል ርምጃ እና ውጊያው ማብቃት እንዳለበት አምነውበት ሳይሆን በውጭ ኃይላት ጫና ስላረፈባቸው ብቻ የፈረሙትን ስምምነት ነው። የውሉን ፍረማ ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩትን ፎቶዎች ወይም የቪድዮ ሥዕሎች ስመለከት፣ በጠላትነት የሚተያዩ የማይተማመኑ ሁለት ግለሰቦችን ነው። እና በቤንቱ እና ሌሎች ነዳጅ ዘይት አምራች አካባቢዎች ውጊያው አሁንም መቀጠሉን መስማቴ ከአስተማማኝ የሰላም ስምምነት እጅግ ርቀን እንደምንገኝ ነው የምረዳው። »

Flüchtlinge in Minkaman Südsudan
ምስል Reuters

የኬንያ ዕለታዊ «ደይሊ ኔሽን» እንደዘገበው፣ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ስምምነቱን የፈረሙት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የእስራት ዛቻ ስላረፈባቸው ነው። የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ዛቻው ቀልድ እንደነበር ወደ ጁባ ከተመለሱ በኋላ ቢያስታውቁም፣ ዛቻው ኪር እና ማቸር ወደው ሳይሆን ተገደው ስምምነቱን መፈረማቸውን እና ይህ ዓይነቱ ዛቻም ወደፊት በሚደረጉት ድርድሮች ላይ ጫና እንደሚያሳርፍ ፒትር ሹማን ገልጸዋል።

« እንደሚመስለኝ፣ ሁለቱ መሪዎች ስምምነቱ በውጭ ጫና የተደረሰ በመሆኑ ዘላቂ እንደማይሆን አውቀውት ነበር። ሁለቱ መሪዎች ከፖለቲካ መፍትሔ ይበልጥ በውጊያ ከሚያምኑት ከተለያዩ የራሳቸው ቡድኖች ጠንካራ ግፊት አርፎባቸዋል። ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ምርጫውን ወደሌላ ጊዜ ይተላለፍ ስላሉበት ሀሳብ ፒትረ ሹማን በሰጡት አስተያየት፣ ሀገሪቱ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ እያለች ምርጫ ማካሄዱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ገልጸዋል።

« እንደምታውቀው፣ ምርጫ በአንድ የሰላም ሂደት ውስጥ የመጨረሻው ርምጃ ነው። ብዙ ጊዜ እንደምናየው የውጭ ኃይላት ምርጫ እንዲካሄድ ይወተውታሉ። ግን፣ የምርጫውን ውጤት ተግባራዊ በማድረጉ ላይ ብዙ ችግሮች ይፈጠራሉ። እና ባሁኑ ጊዜ ስለ ምርጫ ማንሳቱ ጊዜው አይመስልኝም። የሚያስፈልገው ምን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት፣ ፕሬዚደንታዊ ወይም በጠቅላይ ሚንስትር የሚመራ ምክር ቤታዉ ሥርዓት ይሻላል አይሻልም ሳይሆን በተከፋፈለው የደቡብ ሱዳን ህብረተሰብ ውስጥ ካሉት የተለያዩ ፓርቲዎች ቡድኖች ጋ በሰላም ሂደት ላይ፣ ሀገሪቱን አሁን ከምትገኝበት መጥፎ ቅዠት እንዴት ማውጣት እና የኃይሉን ተግባር እንዴት ማብቃት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ገንቢ ውይይት ማካሄድ ነው የሚያስፈልገው። »

Südsudan Riek Machar Soldaten April 2014
ምስል AFP/Getty Images

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ፣ ኢጋድ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ከዘጠኝ ቀናት በፊት የደረሱትን ሰበበኛውን የተኩስ አቁም ደንብ የሚያስከብር አንድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ወደ ደቡብ ሱዳን ባፋጣኝ እንዲልክ የዩኤስ አሜሪካ መንግሥት ጠይቋል። በፕሬዚደንት ኪር ጦር እና በሪየክ ማቸር ደጋፊ ዓማፅያን መካከል ውጊያ ከፈነዳ ካለፉት አምሥት ወራት ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች ወዲያውኑ የተጣሰ የተኩስ አቁም ደንብ ሲፈራረሙ ያለፈው ሳምንቱ ሁለተኛው ነበር። ሳልቫ ኪርም ሆኑ ሪየክ ማቸር ጦራቸውን እና ዓማፀያኑን በሚገባ ያልተቆጣጠሩበት ድርጊት ፣ ደጋፊዎቻቸው የተኩስ አቁሙን ደንብ እንዲያከብሩ ማድረግ ተስኖአቸዋል፤ በዚህም የተነሳ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ባለፉት ጊዚያት በሲቭሉ ሕዝብ ላይ አስከፊ የጭካኔ ተግባር ፈፀመዋል። 

ደቡብ ሱዳን ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት ነፃነቷን ባገኘችበ ጊዜ ዋና ሚና መጫወቷ የተጫወተችው ዩኤስ አሜሪካ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ድርድር ላይ ከኢጋድ እና ከአውሮጳ ህብረት ጎን የሸምጋይነት ሚና መያዟን በደቡብ ሱዳን የቀድሞው የዩኤስ አሜሪካ ልዑክ አንድሩ ናስዮስ አስታውቀው፣ ውዝግቡ አካባቢውንም እናዳያናጋ በማስጋቱ ባፋጣኝ መፍትሔ ሊገኝለት ይገባል ብለዋል።

« ይህ ቀውስ ዩጋንዳን፣ ኢትዮጵያን እና ኬንያን፣ እንዲሁም፣ ሱዳንን እና ኤርትራንም እየነካ ነው። እና በደቡብ ሱዳን እየተካሄደ ያለውን በቅርብ እየተከታተሉት ነው። በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ አንዳንዶቹ ያካባቢ ኃይላት ሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖችን የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ መጀመራቸውን የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች ተገኝተዋል። የጁባ መንግሥት በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ወደ ደቡብ ሱዳን ጦር ልከዋል። ይህ የዩጋንዳ ርምጃ አንዳንዶቹን ያካባቢ ኃይላት ቅር አሰኝቶዋል። እና ኢጋድ የሰላም አስከባሪ ጓድ እንዲልክ የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በጠየቁበት ጊዜ ግን የትኛዋ ሀገር የሚለው ጥያቄ አልተወሰነም፣ ምክንያቱም ይላክ በሚባለው ሰላም አስከባሪ ጓድ ላይ የአንዷ ሀገር ተፅዕኖ ሊያይል ይችላል በሚል በአባል ሀገራት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮዋል። »

በደቡብ ሱዳን ውጊያው ተጠናክሮ የቀጠለበት ውዝግብ ባካባቢው አለመረጋጋት እየፈጠረ ነው ስትል ሱዳን ከሁለት ቀናት በፊት ማስጠንቀቂያ አሰምታለች።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ