1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሸባብ ላይ ያነጣጠረው የኬንያ በቀል

ረቡዕ፣ መጋቢት 30 2007

የኬንያ መንግስት የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ሊዘጋ መሆኑን የጀርመን የዜና ወኪል ዘገበ። በጣቢያው የሚገኙ ከ500 ሺ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ወደ ማይገኝባቸው የሶማሊያ ግዛቶች እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሏል። የኬንያ መንግስት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው በጋሪሳ ከተፈጸመው ጥቃት በኃላ መሆኑን የዜና ወኪሉ አክሎ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1F3pp
Flagge von Kenia
ምስል picture-alliance/dpa

የኬንያ ጦር፤ የአሸባብ የጦር ሰፈር ያላቸውን አካባቢዎች በተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች ለሁለት ተከታታይ ቀናት መደብደቡን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የአውሮፕላን ድብደባው የጋሪሳ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው የጋሪሳ ከተማ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ላይ አራት የአሸባብ ታጣቂዎች 148ሰዎችን መግደላቸዉን መንግስታቸዉ እንደሚበቀል የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከዛቱ በኋላ መሆኑ ነዉ።

ባለፈዉ እሁድ እና ሰኞ በምዕራብ ሶማሊያ የጌዶ ግዛት የተፈጸመው የአውሮፕላን ድብደባ የአሸባብ ታጣቂ ቡድን የጦር መጋዘኞችን እና የልምምድ ሰፈሮችን ኢላማ ያደረገ እንደነበር የዜና ወኪሉ ዘግቧል። ስለ ድብደባዉ ስኬታማነት ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የአየር ድብደባው አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለግጦሽ በሚያሰማሩበት አካባቢ መፈጸሙንና የአሸባብ የጦር ሰፈር ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ « ጥቃት ተፈጽሞብን ዝም አላልንም። የአጸፋ ርምጃ ወስደናል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የታሰበ ይመስላል።» ሲሉ የኬንያ መንግስት እርምጃ የይስሙላ መሆኑን ይናገራሉ።

Kenia Attentat in Garissa
ምስል picture-alliance/AP Photo

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቤ የዌስጌት የገበያ ማዕከል ላይ የአሸባብ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ «በፍጹም አይደገምም» በማለት የገቡት ቃል አልያዘላቸዉም። በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አራት የአሸባብ ታጣቂዎች 148 ሰዎችን ሲገድሉ ከጸጥታ ሃይሎች ይልቅ ጋዜጠኞች ቀድመው በቦታው መድረስ ችለዋል ተብሏል። ከአራቱ ታጣቂዎች መካከል አንደኛው የኬንያ ማንዴራ ግዛት ባለስልጣን ልጅ እና በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ ነበር።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ጥቃቱን እንዳይደርስ ባለመከላከላቸዉ ተጠያቂ ያደረጉት ባለስልጣን ባይኖርም ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል ያስፈልገናል ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ አቤል አባተ የአሁኑ ጥቃት «በቀላሉ መሳሪያና የተለያዩ ነገሮች ለማሳለፍ የሚያስችል በሙስና የተበላሸ እና ብቁ ያልሆነ የጸጥታ ሃይል» በኬንያ መኖሩን ይጠቁማል ሲሉ ተናግረዋል።

Kenia Garissa Universität Anschlag Kenias Präsident Uhuru Kenyatta äußert sich zu dem Anschlag
ምስል Reuters/Thomas Mukoya

ፖሊስ ከጋሪሳው ጥቃት ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም ያላቸውን አምስት ኬንያውን እና አንድ ታንዜንያዊ ለተጨማሪ 30 የምርመራ ቀናት በእስር ለማቆየት ያቀረበውን ጥያቄ ያገሪቱ ፍርድ ቤት መቀበሉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሰራተኛ የነበረ ሲሆን ቀሪዎች ወደ ሶማሊያ ለመሻገር ሲሞክሩ ድንበር ላይ የተያዙ ናቸው ተብሏል። ታንዛኒያዊው ተጠርጣሪ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመያዝ ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቅጥር ግቢ በሚገኝ አንድ ክፍል ጣሪያ ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን የኬንያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምዌንዳ ንጆካ ተናግረዋል። አምስቱ ተመርማሪዎች ለጥቃቱ ፈጻሚዎች የጦር መሳሪያ ሳያቀብሉ አይቀርም በሚል ጥርጣሬ መያዛቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ