1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሸባብ በአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ላይ የፈጸመው ጥቃት

Eshete Bekeleማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2007

የአሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ የአፍሪቃ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ወታደሮች ተገደሉ። ታጣቂዎቹ ከሞቅዲሹ 80 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘውን የጦር ሰፈር ለተወሰኑ ሰዓታት ተቆጣጥረውት ነበር ተብሏል።ታጣቂዎቹ በርካታ የጦር መሳሪያዎች ዘርፈዋል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1GPjV
al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል picture alliance/AP Photo/Sheikh Nor

[No title]

በታችኛው ሸበሌ ግዛት ጃናሌ ከተማ የሚገኘዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ሠፈር ለሰዓታት በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር ወድቆ ነበር ተብሏል። አሸባብ በጥቃቱ 50 የአፍሪቃ ወታደሮችን ገድያለሁ ቢልም እስካሁን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። በሞቅዲሹ የሚገኘው የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ዑመር ሁሴን የአሸባብ ታጣቂዎች ከአፍሪቃ ህብረት የጦር መሳሪያዎች መዝረፋቸውን ይናገራል።

«የአፍሪቃ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የፈጸሙት ወደ 50 የሚጠጉ የአሸባብ ታጣቂዎች ሲሆኑ ከአካባቢው ባገኘነው መረጃ መሰረት በጥቃቱ ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። የጦር ሰፈሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችን የማረኩ ሲሆን በማከማቻ ያገኙትን የምግብ ክምችት ለአካባቢው ነዋሪዎች አከፋፍለዋል።»

Kämpfer von Al-Shabaab in Somalia
ምስል picture-alliance/AP Photo/F.-A.Warsameh

የአካባቢው ነዋሪዎች በጦር ሰፈሩ መግቢያ ላይ በአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ተጀምሮ ለሰዓታት የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ለሬውተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። የሶማሊያ ጦር ሰራዊት አባል የሆኑት ኮሎኔል አህመድ ሃሰን ታጣቂዎቹ የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች እንዳይሸሹ በቅድሚያ በአቅራቢያቸው የሚገኝ ድልድይን በቦምብ ማጋየታቸውን ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል። በጥቃቱ ወቅት በጦር ሰፈሩ ለሚገኙ ወታደሮች ርዳታ ሰጪ ጦር ለመላክ አልተቻለም ተብሏል። በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ጦር በትዊተር ማህበራዊ ድረ-ገጹ የጦር ሰፈሩ በቁጥጥሬ ስር ይገኛል ሲል አስታውቋል። አሸባብ የዛሬው ጥቃት መርካ በተባለ አካባቢ የኡጋንዳ ወታደሮች ለፈጸሙት ግድያ የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው ሲል ማስታወቁን መሐመድ ዑመር ሁሴን ይናገራል።

«ከጥቃቱ በኋላ አቡ ሙሳብ የተባሉ የአሸባብ ቃል አቀባይ ጥቃቱ የኡጋንዳ ወታደሮች በመርካ በሰርግ ስርዓት ላይ ሳሉ የገደሏቸውን (ሠላማዊ) ቤተሰቦች ደምን ለበቀል የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።»

ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጠናው አገራት፤የአፍሪቃ ህብረት ጦርና የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የዘመቱበት አሸባብ ተሸንፏል አሊያም በጣም ተዳክሟል የሚለው ድምዳሜ ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ይመስላል። ቡድኑ በዚህ ወር ብቻ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ የወታደሮች ማሰልጠኛ ላይና በሞቅዲሹ ከተማ ተደጋጋጋሚ ጥቃቶች ፈጽሟል። በጥቃቶቹ የሟቾችና ቁስለኞች ቁጥር ከፍተኛ ነዉ። የጸጥታ ተንታኞች የሶማሊያ መንግስትም ይሁን የአፍሪቃ ህብረት ጦር በስለላ ስራው ጠንክረው የአሸባብ ጥቃቶችን ማክሸፍ አለመቻላቸውን ይተቻሉ። በአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም ተመራማሪ እና ተንታኝ የሆኑት አኔሊ ቦታ የአሸባብ-ታጣቂ ቡድን የመረጠው የሰርጎ ገብ ጥቃት በራሱ ለመከላከል አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።

05.10.2013_DW_online_Somalia_Barawe_Eng

«የሰርጎ ገብ ጥቃትን መዋጋት አመታት ይወስዳል። በአፍሪቃ ህብረትም ይሁን በአንድ አገር ፖለቲከኞች የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን ለማጥፋት ተቃርበናል በሚል የሚሰጥ አስተያየት እጅጉን አከራካሪ ነው። በሶማሊያ የሚሰሩ የጸጥታ ተንታኞች ግን የአሸባብ ታጣቂ ቡድንን ከሶማሊያ ግዛት ለማጽዳት የሚቻለው ያንን ማድረግ የሚችል ሃይል ሲኖር መሆኑን ይናገራሉ። ሶማሊያ ለመቆጣጠር እጅግ በጣም ሰፊ አገር ናት። ይህ ደግሞ በጥቂት ወራት የሚሆን አይደለም።»

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ