1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 «አብዮት ፣ህብረትና ዉበት» በቸርነት የጥበብ ስራዎች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 5 2010

እንደ ሙዚቃ ፤ሥዕል፤ቅርፃቅርፅንና ሥነ-ፅሁፍ የመሳሰሉት የኪነ-ጥበብ ስራዎች ልክ እንደ ታሪክ መዛግብት የኖሩበትን ዘመን ያንፀባርቃሉ፡፡ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ «አብዮት እንደ በረከት»በሚል ርዕስ ለተመልካች የቀረቡት

https://p.dw.com/p/2otkM
Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat

«አብዮት ፣ህብረት እና ውበት» በቸርነት ስዕሎች

የገጣሚና ሠዓሊ ቸርነት ወ/ገብርዔል የሥዕል ስራዎችም ወቅታዊውንና ነባራዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማሳየት ረገድ ተጠቃሽ መሆናቸዉ ተገልጿል።ያለፈዉ ህዳር መጀመሪያ፤ የተከፈተዉ ይህ አዉደ ርዕይ ለ2  ወራት የሚዘልቅ ነዉ። በቀደምቱ የሥነ-ጽሁፍ ሰዉ  በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ስም በተሰየመዉ የጥበብ ማዕከል ፤ለዕይታ ክፍት የሆኑት  የቸርነት የስዕል ስራዎች   27 ሲሆኑ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸዉ።  አብዛኛወቹ ግን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ማንነትን መሰረት አድርገዉ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸዉን አዘጋጁ ገልጿል።
የጥበብ ሰዎች ልክ እንደ ታሪክ ፀሀፊዎች ሁሉ  የሚኖሩበትን ዘመንና ማህበረሰብ ክፉም ይሁን በጎ ክንዉኖች በስራዎቻቸዉ በማንፀባረቅ ረገድ የጎላ ድርሻ አላቸዉ።ከዚህም አኳያ ሠዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወልደ ገብርኤል የጥበብ ስራዎቹ በዚህ የተቃኙና ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ መሆናቸዉን ያመላክታል።በተለይ  በሀገሪቱ በብሄርና በዘር ላይ ያተኮረ ግጭት እዚህም እዚያም መታየቱና  ለዘመናት የቆየዉን ፍቅርና አንድነት እየሸረሸረ መምጣቱ  ለቸርነት ቁጭት አሳድሮበታል።የሥዕል ስራወቹን «አብዮት እነደበረከት »ብሎ ለእይታ ሲያቀርብም መነሻዉ ይህንን የግጭት አዝማሚያ የሚለዉጥ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ «ተመናመነ »የሚለዉን ፍቅርና መተሳሰብ ወደ ቀደሞ ቦታዉ የሚመልስ« አብዮት» ያስፈልጋል በሚል እንደሆነ ያስረግጣል። ያም ሆኖ ግን አብዮት እርስ በእርስ የምንጠፋፋበትና ሰዉ የሚበላ ሳይሆን ፤በጎ  ሀሳብ ክፉ ሀሳብን የሚበላበት በበጎ ሀሳብ አሸናፊ የሆነ አብዮት እንዲመጣ ይመኛል። ይህ ሲሆን «ለአብዮት ያለን አሉታዊ ትርጉም ይቀየራል» ብሎ ያምናል።
«አብዮት እንደበረከት የተመረጠበት ስዕሎቼ አብዮት እንደ በረከት ስለሆኑ ነዉ። እሱን ይገልጻል ብዬ ስለማስብ ነዉ።ይሄ አብዮት የሚባለዉ ነገር በኛ ሀገር ነጌቲቭ ስለሆነ ፖዘቲቭ ለማድረግ አብዮት ያስፈልገናል።የሚል ግን ለሀገሪቱ እንደበረከት የሚሆን አብዮት ያስፈልገናል የሚል ሀሳብ ነዉ።ይህ ምኞቴ ነዉ። አብዮት ፈልጌ ግን አብዮት የሚባለዉ ነገር ለሀገሪቱ በረከት የሚሆን እንደ በፊቱ እርስ በእርሳችን የምንበላላበት ሳይሆን ክፉ ሀሳቦቻችንን የሚበላ ፣አንድ የሚያደርገን በልዩነታችን ላይ የተሰራዉን ስራ የሚበላ እሱን ለመናገር ፈልጌ ነዉ።»
ከዚህ ቀደም ባዘጋጃቸዉ  የስዕል አዉደ ርዕዮችም ሀገራዊ  ጉዳዮችን የሚጠቁሙ በርካታ ስራወች ማቅረቡን የሚናገረዉ ቸርነት ጥበብ ለህብረተሰቡ ቅርብ እንደመሆኑ መጠን የመሪዉን ችግር ማሳየት አለበት ይላል።ከህዝቡ ጉያ ዉስጥ ያለን የጥበብ ሰወች ነባራዊዉን ችግር ካልጠቆምን የሌላ ሀገር ሰዉ መጥቶ ያገባኛል ብሎ ሊሰራልን ይችላልን ? ሲልም ይጠይቃል።እናም የሚያገኛቸዉን የጥበብ መድረኮችም ማህበራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ህጸጾችን  ለመንቀስ  ይጠቀምባቸዋል። 
«እንዲህ ነዉ የማስበዉ  አሁን እኛ መሀል ነዉ ያለነዉ እዚሁ ነዉ ያለነዉ ።የሆነ ቦታ ፣የሆነ አገር አይደለም ያለነዉ ።ስንናገር መሃላቸዉ ሆነን ነዉ የምናወራዉ።ይህን ነገር በአደባባይ ስንሰቅል መንግስትም እንዲያይልን ነዉ።ሌላ እኮ አይደለም የመንግስትም አካል መጥቶ እንዲያየዉ ነዉ። ይሄ ልጅ እንዲህ ያስባል እንዲሉ ነዉ።ብዙ መድረክ ላይ ግጥሞቼን አቀርባለሁ አንድም ቀን ተሳቅቄ አላዉቅም።ብዙ የስዕል ኤግዚብሺንም አድርጌ አቃለሁ።ሀገሬን በሚመለከት መጠቆሚያ መንገዶችን እሰራለሁ ።ይበጃል የሚለዉን እሰራለሁ ።ሌሎቹም ጓደኞቼ ፤በዚህ መስመርም ያሉትም ሰዎች ፤በተለይ በግጥም በኩል እኛ ሀገር  በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ አለ ብዬ አስባለሁ።ጥሩ ነገር እየተሰራ ነዉ።እና የእዉነት ያገባናል።ሌላ የሚያገባዉ የሌላ ሀገር ሰዉ ልንፈልግ አይገባም።ተደማመጥንም አልተደማመጥንም እዉነቱን  ማዉራትና እዉነቱን ሰርቶ ማሳየት ለመሪወቻችን ያስፈልጋል።»
እርሱን ጨምሮ ከ7 እህትና ወንድሞቹ ጋር አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ በጥልቅ ቤተሰባዊ ፍቅርና ማህበራዊ ትስስር እንዳደገ የሚገልፀዉ ቸርነት፤ ይህ አስተዳደጉ  ስለ ሀገር አንድነትና ፍቅር «የተለየ ቦታ እንድሰጥ አድርጎኛል» ነዉ የሚለዉ። ሰዎች በመጡበት አካባቢ ሳይሆን በሰዉነታቸዉ ሚዛን ብቻ  ሊከበሩ ሲገባ  «በብሄሩ የተነሳ ከአንድ ክልል ሰዉ ተባረረ» የሚል ነገር መስማት ግን   ከዚህ አስተዳደጉ  የተለዬ በመሆኑ ለሠዓሊዉ  ህመም የሚፈጥር ነዉ። አንድ ከሚያደርገን ነገር ይልቅ የሚያለያየን ነገር ላይ እየተተኮረ መጥቷል ሲልም ይተቻል።
«ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የትም ቦታ ሄዶ መኖር ይችላል።በሀገሪቱ ዉስጥ በየትኛዉም ቦታ ሄዶ መኖር ይችላል ።የዘር ጥያቄ አያስፈልገዉም።ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነዉ። ኢትዮጵያዊነት በቂ ነዉ።የትም ቦታ ለመገኘት ፣በሀገር ዉስጥ የትም ቦታ ለመኖር አርሶ አንደፋርሶ መኖር መብቱ ነዉ ።በብሄሩ የተነሳ ከሆነ ክልል ተባረረ  የሚል ድምፅ መስማት ለኔ ያመኛል።በጣም።ስለዚህ ይህን አስተሳሰብ የሚጥል ያስፈልጋል።መታወቂያዉ ላይ ብሄሩ ተፅፎ የሱ መለያ ነዉ መባል የለበትም።ከመታወቂያችን ላይ ኢትዮጵያዊነታችን በቂ ነዉ።ብሄር መነሳት አለበት።በዚያ ላይ የማናዉቀዉ ብሄር ነዉ የሚለጠፈዉ።በጣም እኮ ይገርማል።አሁን ማነዉ ? ብቻዉን አማራ ።ማነዉ ብቻዉን ኦሮሞ? ማነዉ ብቻዉን ትግራይ? ማነዉ …….?እናቶቻችን የት ሄደዉ ነዉ ? የናታችንን ትተን ያባታችን ብቻ ተጠርቶ ።የአባታችንም ወደ ላይ ሲሄድ የሆነ ብሄር ዉስጥ ይገባል።እና ይሄ ነገር መነሳት አለበት «ኢንሲስት» ማድረግ ያስፈልጋል መንግስትን።በቃ ይሄ ነገር ይነሳልን ማለት ያስፈልጋል።ለሰላም  አይበጅም ጥሩነቱ አልታየኝም ።እንዲህ እንዲህ አይነት ነገሮችን እፈልጋለሁ ።ይሄ ለሀገሬ በረከት ነዉ ብዬ አስባለሁ። ሰዎች በእኩልነት በሰዉነታቸዉ ሚዛን ፤በቃ ሰዉ በመሆን ሚዛን ብቻ በሀገሪቱ ላይ መኖር የሚችልበት መብት ማግኜት አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህ ነዉ አብዮት እንደበረከት።»
ለቸርነት ኢትዮጵያ በህብር የምትደምቅ፤ህዝቡም ፍቅር ፈላጊ ነዉ።ይህንን የህዝብ ፍላጎት  መንግስትም ቢሆን ሊገነዘብ ይጋባል ባይ ነዉ። ሰዓሊዉ መልዕክቱን«ህብረትና ዉበት » በሚለዉና በህብረ ቀለም ባሸበረቀዉ  የስዕል ስራዉ ደህና አድርጎ አጠናክሮታል። ከቸርነት ስዕሎች ዉስጥ ያለፈ ታሪካችንን በጎም ይሁን መጥፎ ሰርተዉት ላለፉ ሰዎች ትተን ፤ያለንበት ዘመን የተሻለ ለማድረግ መስራት አለብን የሚል አንድምታ ያላቸዉም አሉ።ያጠፋም ቢኖር ምህረትና ይቅርታ ቦታ ሊያገኙ እንደሚገባ ያስባል።ዉሃና እሳት በአንድ ላይ ተቀላቅሎ በሚታይበትና« በፍፁም አልሸጠዉም»በሚለዉ ስዕሉ አማካኝነት ይሄዉ ሀሳብ በአዉደ ርዕዩ  በተምሳሌትነት ቀርቧል። ሰዓሊዉ  ስለ ሀገሩ ያለዉን ህልም ፣ተስፋና ስጋትም በስራወቹ ያንጸባርቃል።   
«እና ይሄኛዉ ነገር የሚሰማዉ ፤ዳርዳር ያለዉ፤ ምናልባት አዲስ አበባ ኮንሰርት ሊኖር ይችላል።ግን አዲስ አበባ ዉስጥ ሀዘኑ የለም ማለት አይደለም።የአዲስ አበባ ህዝብ በብዛት የክፍለሀገር ሰዉ ነዉ።አዲስ አበባ ተወልደን ያደግነዉ በጣም ትንሽ ነን።ስለዚህ መርዶ ይመጣል ።ዳር ዳር ለሞተዉ ወጣት መርዶ ከተማ ዉስጥ አለ።እና ጎርፉ ይደርሳል ማለት ነዉ።ላይ የዘነበዉ ጎርፉ እዚህ አለ ይነካናል።ሠላም የሚመስለዉ ነገር ዉስጥ ዉስጡ በጣም የሚያስፈራ ይሆናል።እኔ እፈራለሁ ።በጣም እፈራለሁ።ስለ ኢትዮጵያ ሳስብ ስለ ሀገሬ ሳስብ እፈራለሁ።እንዳልፈራ የሚያደርገኝ እንዲህ አንዳንዴ የምሰራቸዉ ስዕሎች ያድኑኛል።የምፅፋቸዉ ግጥሞች ያድኑኛል።ለራሴ እድንባቸዋለሁ።ተስፋ ለመዝራት ያህል።»
የብላቴን ጌታ ኅሩይ የሥነ-የጥበብ ማዕከል ዳይሬክተር፤ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ የቸርነትን የጥበብ ስራወች በቅርብ ከሚያዉቁት  ዉስጥ አንዱ ነዉ።ሰዓሊዉ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ብዙወቻችን ዉስጥ ዉስጡን የምንብሰለሰልባቸዉን ርዕሰ ጉዳዮች በግልጽ አስቀምጧል ሲል ያብራራል።

Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat
Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat
Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat
Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat

«አብዮት እንደበረከት በሚል ስያሜ የሰጣቸዉ ስዕሎቹ አሁን ባለችዋ ኢትዮጵያ አሁን እየሆነባለዉ ፖለቲካዊ ሁነት ዉስጥ የራሱን ምልከታ የራሱን ግንዛቤ ያሳየበት ነዉ። ርዕሱ አብዮት ሲባል ብዙ ጊዜ መርገምትን አብዮኅ ሲባል ጥፋትን  ዉድመትን የሚያመለክት ሆኖ ይታያል። ሆኖም አብዮት በስርዓት ከተያዘ  ይዞት ሊመጣ የሚችል በረከት አለዉ ብሎ ያምናል።ለዚህም ነዉ አሁን ስዕሎቹ ላይ ከላይ ዕሳት ይታያል ጥፋት ይታያል።የሚንቦገቦግ ከተማን የሚበላ ዕሳት ይታያል ከስር ደግሞ የለመለመ ነገር እናያለን።የሚሞቁ ቀለማትን ድንጋጤ የሚያጭሩ ቀለማትን ተጠቅሟል፤ በእነዚህ ቀለማት ዉስጥ ደግሞ  ልብ ያላልነዉ ዙሪያ ዙሪያዉን በየ መገናኛ ብዙሃኑ የሚገለጸዉ እንዲያዉ ባልሆነ ባልደረሰ ሀገሪቱን ቁልቁል ይዟት ባልወረደ የሚያስብሉ ሀሳቦች ላይ ተሽከርክሮ ነዉ ስዕሎቹን ያሳላቸዉ። እነዚህ ሃሳቦች ደግሞ በግጥሞቹ ዉስጥም በተለይ ፅዋዉ ሲሞላ  በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት ብቻዉን አንድ የግጥም ኮንሰርት በሀርመኒ ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር ፅዋዉ ሲሞላ በሚል  ርዕስ ያቀረበዉ ግጥም ነበር።ራሱ በቃ አለ ዉስጥ ዉስጣችንን እየታመስን ፣እያቃሰትን  የምንብሰከሰክባቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ  አጠንጥኗል።እና ይሄ የግጥሞቹ መንፈስ በአንዳንድ ስዕሎቹ ላይም የተንጸባረቀ ሆኖ ይሰማኛል። »

ሰዓሊዉ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከሚዳስሱት ስራወቹ ባሻገር የሀገሪቱን ያለፈ ታሪክና ባለዉለታወችን የሚዘክሩ እንዲሁም  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን  የሚያሳዩ ስዕሎችንም ለዕይታ አቅርቧል።ከእነዚህም መካከል «የተከፈለበት»ና  «ተራኪዉ »በሚል ርዕስ በሀገሪቱ በተካሄዱ ጦርነቶች ለሉዓላዊነት የተከፈለዉን መስዋዕትነት ለማሳየት በአንድ የወታደር ጫማ ተምሳሌትነት የቀረበ ስዕልም ይገኝበታል። 
«የተከፈለበት ስለሀገር አንድነት የተከፈለ ዋጋ አለ።ብዙ ጊዜ ስንማርም ሆነ በእድሜዬ ያየሁት ሀገር የሚባለዉ ነገር ዋጋ ሲከፈልበት እን አይቻለሁ።ከቤተሰቤም አይቻለሁ።ለኢትዮጵያ አንድነት የታገለ ቤተሰብ አለኝ ።በቅርብ በእኛ እድሜ ደግሞ ስለ ሉዓላዊነት ተብሎ ፣ሀገር ተደፈረች  ተብሎ ፣ባድመ ተብሎ ወጣቱ ሄዶ ሲሞት አስታዉሳለሁበኔ እድሜ ይሄ የተከፈለበት ነዉ።ይሄ ስለሀገር ሀገር የተከፈለ ዋጋ ነዉ። በምንም ስብከት ይሂድ ሀገርህ ተደፈረች ተብሎ ነዉ የሞተዉ። እና ይህንን መርሳት የለብንም ።ባድመ ሄዶ የሞተዉ የወላይታ ወጣት ስለ ባድመ አያገባኝም አላለም። ብሄሩም አልተጠየቀም ።ሀገሬ ናት ኢትዮጵያ ናት ብሎ ነዉ ሄዶ የሞተዉ። ኦሮሞዉ ሄዶ ሲሞት  ባድመ የትግራይ ክልል ነዉ ።አያገባኝም አላለም ። ዛሬ ከሱማሌ ክልል የሚወጣበት ምክንያት አይገባኝም።»
«እንጀራ» በሚለዉ የስዕል ስራዉም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰወች ከህይወት ጋር የሚያደርጉትን ትግል ቃኝቶበታል።

Äthiopien Künstler Chernet W/Gebreal Sisay
ምስል Privat

«እንጀራ ያዉ አካባቢያችን ያሉ ነገሮች ናቸዉ።ገንዳ አለ።ገንዳ ላይ የሚርመሰመሱ ሰወች ይኖራሉ።አይጠፉምና አንዳንዱ እዚያዉ ላይ ያነሳል።አንዳንዱ ያ ቆሻሻ መኖሩ ገንዳዉ መኖሩ እንጀራዉ ነዉ።ኢቢስ ላይ አንድ የጽዳት ሰራተኛ ቀርቦ« ቆሻሻ እኮ ብር ነዉ አለ።»እና እንጀራዉ ነዉ ለዚህ ልጅ።«እኔ በረንዳ አዳሪ ነበርኩ ቆሻሻ  ማጽዳት ከጀመርኩ ጀምሮ ነዉ  ልጆች ወልጀ ቤት ተከራይቼ የምኖረዉ አለ።» እንጃራ ነዉ ማለት ነዉ። እኛ የምናየዉ ዝም ብሎ ገንዳ አይደለም።ዝም ብሎ ቆሻሻ አይደለም ለሆኑ ሰወች እንጃራ ነዉ።ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቆሞ መሄጃቸዉ ነዉ። እና እሱን ነዉ
ቸርነት ከስዕል ስራወቹ በተጨማሪ «ኤፍራጥስ»በሚል ርዕስ የግጥም መድብል ለህትመት አብቅቷል። «ዲና» የተሰኘ የግጥም ስብስብም በቪሲዲ  አሳትሟል።በቅርቡም «ፅዋዉ ሞልቷል»በሚል ተጨማሪ የግጥም ስራወችን እየሰራ መሆኑንም አጫዉቶናል። በስዕሎቹም ይሁን በግጥም ስራወቹ  የሀገር አንድነትና ፍቅር ደጋግሞ የሚያነሳቸዉ ጭብጦቹ ናቸዉ።ጥላቻ ትርፉ መለያየት ነዉ ብሎ ያምናል።«ተነጣጥሎ ከመቆም ይልቅ  እንዋደድ፣ እንፋቀር፣ እንተባበር »ቸርነት ደጋግሞ የሚያነሳዉ ሀሳብ ነዉ።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ