1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ማግሥት የታሰሩት የአቶ በቀለ ገርባ ክስ አሁንም እየታየ ነው

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2009

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ገርባ በድጋሚ ከታሰሩ አንድ ዓመት እና ጥቂት ቀናት ተቆጠሩ። የኦሮሞ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ማግሥት በሽብር ተጠርጥረው ከዓመት በላይ የታሰሩት አቶ በቀለ የፍርድ ሒደት አሁንም አልተጠናቀቀም።

https://p.dw.com/p/2V125
Äthiopien Politiker Bekele Gerba
ምስል Addis Standard Magazine

MMT-Bekele Gerba-One Year in Prison - MP3-Stereo

ከስድስት ዓመታት በፊት በተካሔደው ምርጫ መድረክን ወክለው ለሙግት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ብቅ ያሉት አቶ በቀለ ገርባ ሕገ-መንግስቱን ጠቅሰው አንድ ጥያቄ ጠየቁ። የመሬት ባለቤትነት እና አጠቃቀም ላይ አተኩረው ንግግራቸውን ያደረጉት አቶ በቀለ «በእውነት መሬት የሕዝብ ነው? የመንግስት ነው?» ሲሉ ጠየቁ። አቶ በቀለ ራሳቸው ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ሰጡ። «በእኛ ግምት መሬት ዛሬ የማንም አይደለም። መሬት የገዢው ፓርቲ ባለስልጣኖች የግል ንብረት ነው። እንደፈለጉ የሚሸጡት የሚለውጡት ጓደኛ የሚያፈሩበት በዘመድ አዝማድ የሚያከፋፍሉት፤ ለፓርቲ አባላት መመልመያ የሚጠቀሙበት ማባበያ ነው-መሬት።» ሲሉ ተናገሩ። የተሰጣቸው ጊዜ እስኪጠናቀቅ መሬት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚጫወተውን ልውጥ ሚና ተነተኑ።

ይኸን የሚያስታውሰው የፖለቲካ አቀንቃኙ ግርማ ጉተማ ንግግራቸው በደጋፊዎቻቸው ልብ ውስጥ እንዲታተሙ አድርጓቸዋል ሲል ይናገራል። ግርማ «ምርጫ 2010 ላይ (በጎርጎሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር) ያደረገው እና በቴሌቭዥን የተላለፈ መልዕክት በእኔ እምነት አሁንም ድረስ መንግስት ጥርስ ያስነከሰበት ይመስለኛል።» ሲል ያክላል።  

 ምርጫው እንደ አመጣጡ ተሰናበተ። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ይሁን የአቶ በቀለ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደቀድሞው አልሆነም። ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ  ግንባር /ኢሕአዴግ/ ከአንድ ወንበር በቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ጠቅሎ ወሰደ። ነሐሴ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ደግሞ አቶ በቀለ ገርባ ታሰሩ። ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚዎች ጋር በተገናኙ ማግሥት የታሰሩት አቶ በቀለ ከሁለት ዓመት በኋላ የስምንት ዓመት እስራት ተበየነባቸው። 

የእስር ጊዜያቸውን ያለ አመክሮ አጠናቀው የተፈቱት አቶ በቀለ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናትን የሞገቱበት የመሬት ጉዳይ እሳት ሆኖ ጠበቃቸው። በእስር ላይ ሳሉ አዲስ አበባን ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች ጋር ለማቀናጀት የቀረበውን እቅድ በመቃወም የታሰሩ ወጣቶችን ተገናኝተዋል። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተጉዘው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ በቀለ ተቃውሞ እና የፖለቲካ ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያዋጣል ሲሉ ወትውተዋል።  ከእስር በተፈቱ ማግሥት ያነጋገረቻቸው የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ዋና አርታዒ ጸዳለ ለማ «ስለ አመፅ አልባ ትግል የሚናገሩበት ሁኔታ፤ይሆናል የሚሉበት መንገድ፤ የሚገልፁበት አኳኋን በሙሉ እዛ አገር (ኢትዮጵያ) እኛ ከለመድንው እና የፖለቲካ ሰዎች ካሳዩን ወይም እያሳዩን ካለው አቋም እጅግ የተለየ ስለሆነ ለየት ያደርጋቸዋል።» ስትል ትናገራለች። ጸዳለ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያላቸው ቁርጠኝነት «እንዲሕ አይነት የፖለቲካ አቋም ይዞ ፖለቲካው ውስጥ የመሳተፍ እድል ይኖራል ወይ?» የሚል ጥያቄ ያጭራል ስትልም አክላለች። 

«የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ውስጥ አቶ በቀለ እንደ ምልክት ሆኖ ወጥቷል።» የሚለው ግርማ ጉተማ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘታቸውን እና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ መልዕክት ማስተላለፍ መቻላቸውንም ይገልጣል። «ሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ በደንብ ብንሰራበት ለውጥ ያመጣል። » ብለው ይናገሩ እንደነበር የሚያስታውሰው ግርማ ወደ አስተምህሮቱ ያዘነበሉት አቶ በቀለ የጥቁር አሜሪካውያን የነፃነት ታጋይ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን «ሕልም አለኝ» የተሰኘ መፅሐፍ ወደ ኦሮሚኛ መተርጎማቸውን ያወሳል። 

Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

አቶ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰሱበት ችሎት "በህይወት ዘመኔ ኢ-ፍትሃዊ አድሎን ፤ ዘረኝነትን እና ጭቆናን ተፀይፌ ተቃውሜያለሁ ። በራሴ ምርጫ ሳይሆን በፈጣሪ ፍቃድ የተፈጠርኩበትን የኦሮሞን ህዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ተከብረውለት፣ በእኩል ዓይን እንዲታይ ባደረኩት ሰላማዊ ትግል ምክንያት መስዕዋትነት መክፈል መቻሌ ለኔ ክብር ነው።» በማለት ያደረጉት ንግግር የማሕበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተወደደ ሆኖ ነበር።

የአቶ በቀለ ገርባ «እስር ቤት መግባት መውጣት የእኛን አገር የፍትኅ ውድቀት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።» የምትለው የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ዋና አርታዒ ጸዳለ ለማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉድለት መፍጠሩንም ታክላለች። «የእሳቸው መታሰር ለፖለቲካው የነፈገው ትልቁ ነገር በሰላማዊ መልክ በመነጋገር ጥሩ መፍትሔ ያላቸው ሰዎች እድል አግኝተው ፖለቲካውን የማቃናት እድል የነፈገ ነው።» እንደ ጸዳለ አገላለፅ በአቶ በቀለ ገርባ መታሰር ፓርቲያቸው እና የሚወክሉት ኦሮሞ ሕዝብ ጉዳት ቢደርስባቸውም «ትልቁ ጉዳት በጠቅላላ የፖለቲካ ግንባታ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው።» ብላለች። የኦሮሞ ተቃውሞ በተቀቀሰ ማግሥት የታሰሩት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ግለሰቦች በአወዛጋቢው የጸረ-ሽብር ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ይገኛል። 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ