1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንባቢ (ሀ)

ሐሙስ፣ መስከረም 28 1996
https://p.dw.com/p/E0gF

የጀርመንና የሩሲያ መንግሥታት ምክክር፧ በ፪ ቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ የቀጠለ ለመሆኑ ማረጋገጫ ምልክት ነው። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ፧ ዘንድሮም፧ ትናንት፧ የካተሪንቡርግ በተሰኘችው የሩሲያ ከተማ የተጀመረውና ዛሬም የቀጠለው የ ፪ ቀናት ስብሰባ፧ ይበልጥ በኤኮኖሚ ትብብር ላይ ያተኮረ ነው። ሞስኮን ያላስደሰተው የሰብአዊ መብት ነክ ጥያቄም መወሳቱ አልቀረም። ሞስኮ በምትፈልገው ሁኔታ የተካሄደው ነጻና ትክክለኛ መሆኑ ያጠራጠረው የቸችኒያው ምርጫ፧ መራኄ መንግሥት ጌርሃርት ሽሮዖደርና ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ባደረጉት ጭውውት ሳይነሣ እንዳልቀረ ነው የሚነገረው። አንባቢ (ለ) የሩሲያ ኤኮኖሚ፧ የሚያድግ-የሚመነደግበት ሁኔታ፧ እየታየ በመሆኑ፧ የጀርመን የኤኮኖሚ ኀላፊዎች የ ፪ ቱ አገሮች የምጣኔ ሀብት ግንኙነት እጅግ እንዳረካቸው ነው የሚናገሩት። የሩሲያ ኤኮኖሚ፧ ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ እስከ ሰኔ ድረስ፧ በ ፮ ወራት ብቻ፧ ፯ ከመቶ ዕድገት አሳይቷል። የክሬመል መንግሥት፧ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪም ፷ ቢልዮን ዶላር መድረሱ ነው የተገለጠው። በመሆኑም አገሪቱ ያለባትን ዓለም አቀፍ ብድር፧ ከጀርመን የተበደረችውን ጭምር፧ ውሉን አክብራ መልሳ የምትከፍልበት አቅም አላት። የውጭ ባለወረቶችም ሩሲያ ውስጥ፧ በዚሁ፧ 2003 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት እስካሁን ፰ ቢልዮን ዶላር ሥራ ላይ ማዋላቸው ታውቋል። ይህም፧ የአውሮፓው ኅብረት አባል ለመሆን በታጨ በማንኛውም የምሥራቅም ሆነ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገር፧ ያልተሞከረ ነው። ሩሲያ፧ ከነዳጅ ዘይትና ከተፈጥር ጋዝ ሽያጭ በምታገኘው ሰፊ ሀብት ብቻ ሳይሆን፧ በአጠቃላይ የኤኮኖሚ እንቅሥቃሤዋ፧ አስደናቂ ዕድገት ማሳየቷ እየተመሠከረላት ነው። ስለሆነም፧ በዚሁ ዕድገት ማትረፍ የሚሹ፧ የጀርመን ታላላቅና መለስተኛ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች፧ መራኄ-መንግሥት ጌርሃርት ሽሮዖደር ያቀረቡላቸውን ጥሪ በደስታ ተቀብለው አብረዋቸው ተጉዘዋል። የሩሲያ የዕድገት ሂደት፧ ባለወረቶችን እንዲህ ቢያማልልም፧ አሁንም ቢሆን፧ በዓለም ውስጥ፧ በቆዳ ስፋት የአንደኛነቱን ሥፍራ በያዘችው እጅግ ግዙፍ ሀገር፧ የፀጥታው ይዞታ፧ እንዲሁም ሊወገድ ያልቻለው ሙስና እንዳሳሰበ ነው። የሆነው ሆኖ፧ በአውሮፓ በህዝብ ብዛት የመሪነቱን ደረጃ የያዙት የ፪ ቱ አገሮች መንግሥታት፧ በኤኮኖሚውም በፖለቲካውም መርኅ ረገድ ያማረ-የሠመረ ግንኙነት ነው ያላቸው። ከግንኙነታቸው መጠናከር የተነሣም፧ አፍጋኒስታን ውስጥ ፀጥታ በማስከበር ላይ ለሚገኙት የጀርመን ወታደሮች፧ በቅርቡ ሥንቅና ትጥቁ፧ በሩሲያ ምድር በኩል ነው እንዲሸጋገርላቸው የሚደረገው። የኢራቅን የፖለቲካ ይዞታ በተመለከተም፧ ሽሮዖደርና ፑቲን ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው። ፪ ቱም የተባበሩት መንግሥታት፧ በመካከለኛው ምሥራቅ ላቅ ያለ ድርሻ እንዲኖረው ይፈልጋሉ። ፈረንሳይም ብትሆን ይህን አቋም የምትጋራ ሀገር ናት። ጀርመን በይፋ ባትናገረውም፧ ሞስኮ፧ በርሊንና ፓሪስ፧ በዚህ ረገድ የጋራ አቋማቸው እንደፀና ነው የሚገኘው። በተለያዩ ጊዜያት፧ ጀርመንም፧ ሩሲያም፧ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ለማግባባት ያደረጉት ጥረት አልሠመረላቸውም። የካተሪንቡርግ ላይ፧ የሩሲያና የጀርመን መሪዎች፧ ፑቲንና ሽሮዖደር፧ የኢራቁን የፖለቲካ ይዞታ በተመለከተ፧ ከያዙት አቋም ንቅንቅ እንደማይሉ በውይይታቸው ላይ አስገንዝበዋል። በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት፧ ዩ ኤስ አሜሪካ በሚመጡት ሳምንታት የምታቀርበው አዲስ ረቂቅ ውሳኔ እንዲጸድቅላት የምታደርገው ጥረት የሚሠምር መሆኑ እጅግ ነው የሚያጠራጥረው። ሽሮዖደርና ፑቲን፧ በተጨማሪ፧ በ፪ አገሮች መካከል፧ የወጣቶች ልውውጥ ነክ መርኀ-ግብር እንዲጠናከር ተስማምተዋል። ጀርመን፧ የአቶም ጦር መሣሪያ ይጭኑ የነበሩ የሩሲያ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን በማጽዳቱ ረገድ፧ በገንዘብ ትሣተፋለች፧ ሩሲያውያን ሥራ አስኪያጆችንም ታሠለጥናለች። በጀርመንና በሩሲያ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ቅሬታን ያስከትላል ተብሎ አሥግቶ የነበረው ባለፈው እሁድ የተከናወነው የቸችኒያው የፕሬዚዳንት ምርጫ ነው። ሽሮዖደር፧ የአውሮፓውን ኅብረት አቋም በማንጸባረቅ፧ ምርጫው፧ ነጻ፧ ትክክለኛና ዴሞክራቲክ እንዳልነበረ ቢነጋገሩበትም፧ ቡባዔው የጋራ መግለጫ ላይ ሳይጠቀስ ነው የታለፈው። ይህም የሆነው፧ የጀርመንን የኤኮኖሚ ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ሳይሆን እንዳልቀረ የመራኄ-መንግሥት ጌርሃርት ሽሮዖደር አማካሪዎች ጠቁመዋል።