1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንካራ : በሁለት የቦምብ ጥቃቶች ቢያንስ 86 ተገደሉ

ቅዳሜ፣ መስከረም 29 2008

ተጨማሪ 186 ሰዎች ለቆሰሉበት ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም የአገሪቱ መንግስት የአሸባሪዎች እጅ ሳይኖርበት አይቀርም ብሏል። ቱርክ ሶስት የሐዘን ቀናት አውጃለች።

https://p.dw.com/p/1GmCA
Türkei Anschlag in Ankara - Moment der Explosion
ምስል Reuters/M. Tombalak/dokuz8HABER

በቱርክ ዋና ከተማ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች ቢያንስ 86 ሰዎች ተገደሉ። ሌሎች 186 ሰዎች የመቁሰል አደጋ የገጠማቸው ሲሆን 28ቱ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታውቀዋል።

ከአንካራ የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ በሚካሄድ የሰላማዊ ሰልፍ ላይ ያነጣጠሩት የቦምብ ጥቃቶች በአሸባሪዎች የተፈጸመ መሆኑን የቱርክ መንግስት አስታውቋል። የቱርክ መንግስት ባለስልጣናት በአጥፍቶ ጠፊዎች ሳይፈጸም አይቀርም ይበሉ እንጂ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ የለም። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሪቸፕ ጣይብ ኤርዶጋን «በአንድነታችንና በአገራችን ሰላም ላይ» ያነጣጠረ ያሉትን ጥቃት ኮንነዋል።

የሰላማዊ ሰልፉ በቱርክ መንግስትና የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ግጭቶች ለማውገዝ የታለመ እንደነበር ተጠቁሟል።
የቱርክን መረጋጋት አጥብቀው የሚፈልጉት የአውሮጳ ህብረት፤ፈረንሳይ እና ሩሲያ ጥቃቱን አውግዘዋል። በአንካራ ታሪክ የከፋ የተባለው የዛሬው የቦምብ ጥቃት አገሪቱ በሚቀጥለው ወር ምርጫ ለማካሄድ በተዘጋጀችበት ወቅት የተፈጸመ ነው። ቱርክ በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል የሶስት ቀናት ሐዘን ማወጇን አስታውቃለች።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ