1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድነት አዲስ ፕሬዝደንት መምረጡ

ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2007

የኢትዮጵያ ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ጥቅምት 2/2007 ዓ.ም. አቶ በላይ ፈቃዱን በፕሬዝደንትነት መምረጡን አስታውቋል። አቶ በላይ በፕሬዝደንትነት የተመረጡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው ስላጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ መሆኑን የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ስዩም መንገሻ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1DV6W
QUALITÄT! Oppositionspartei in Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር ውህደት ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ የቆየውና አምስት የካቢኔ አባላቱ ከፕሬዝዳንቱ ጋር መስራት አልቻልንም በማለት ከስራ አስፈጻሚነታቸው የለቀቁበት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አዲስ ፕሬዝደንት መምረጡን አስታውቋል። ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር የፓርቲውን መንበረ-ስልጣን ከዶ/ር ዶክተር ነጋሱ ጊዳዳ የተረከቡት ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው በፓርቲው ውስጥና ውጪ በገጠማቸው እክል ከፕሬዝዳንትነታቸው በፈቃዳቸው ራሳቸውን ማግለላቸውን የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ስዩም መንገሻ ይናገራሉ።

ከቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳት ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው ጋር መስራት አንችልም ብለው ራሳቸውን ካገለሉት አምስት የካቢኔ አባላት መካከል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ዳንኤል ተፈራ ይገኙበታል። አቶ ዳንኤል የኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው ውሳኔ ልዩነታቸውን እንደፈታው ይናገራሉ።

Bildergalerie Demonstration Oppositionspartei UDJ in Äthiopien
ምስል DW

ጥቅምት 2/2007 .. በተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ አቶ በላይ ፈቃዱ አቶ ትዕግስቱ አወሉና አቶ ደረጀ ኃይሉ ከተባሉ ሁለት ተፎካካሪዎቻቸው አብላጫ ድምጽ በማምጣት መመረጣቸውን አቶ ስዩም መንገሻ ይናገራሉ። እንደ ዋና ጸሃፊው ከሆነ ካቢኔያቸውን ጥቅምት 9/2007 .. ያሳውቃሉ ተብለው የሚጠበቁት በአንጻራዊ መመዘኛ ወጣቱ ፕሬዝዳንት በፓርቲው ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁበትን ምክንያትና በፓርቲው ውስጥ የሚኖራቸውን ቀጣይ ተሳትፎ በዚህ ዘገባ ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ስዩም መንገሻ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በብሄራዊ ምክር ቤት አባልነታቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች መካከል የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ ስዬ አብርሃ ወደ አሜሪካን ያቀኑ ሲሆን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ ስልጣናቸውን ለኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራው ባስረከቡ ማግስት ራሳቸውን ከፖለቲካ ማግለላቸው አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ