1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጌላ ሜርክል በጀርመን የውኅደት ቀን ምስጋና አቀረቡ

ዓርብ፣ መስከረም 23 2007

መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በጀርመን 25ኛ የውኅደት ቀን ዛሬ ሐኖቨር ከተማ ለተሰበሰቡ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ታዳሚያን ንግግር አደረጉ። መራሒተ-መንግሥቷ ጀርመንን በምሥራቅ እና ምዕራብ ጎራ ከፍሎ የነበረው የበርሊን ግንብ የዛሬ 25 ዓመት እንዲደረመስ አስተዋፅኦ ያደረጉ የምስራቅ ጀርመን ሰልፈኞችን ጀግንነት እና ጥረት በንግግራቸው አወድሰዋል።

https://p.dw.com/p/1DPb5
የጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ንግግር ሲያደርጉ
የጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ንግግር ሲያደርጉምስል picture-alliance/dpa/P. Steffen
በያኔው የምሥራቅ ጀርመን በተለምዶው DDR በሚባለው የጀርመን ክፍል የነበሩ ጀርመናውያን ያካሄዱት ሠላማዊ አብዮት እና የፌዴራል ጀርመን ፖለቲከኞች ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባይታከልበት ኖሮ የግንቡ መደርመስ የማይታሰብ ነበር ብለዋል። መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል፥
«ያለ እነዚህ ዜጎች ጀግንነት እና እነሱን ማሳመን የቻለው የለውጥ ግፊት ውጪ እጎአ ህዳር 9 ቀን 1989 ጀርመንን ለያይቶ የነበረው ግንብ አይደረመስም ነበር።
የጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል እና ሌሎች የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናት
የጀርመን መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል እና ሌሎች የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናትምስል picture-alliance/dpa/O. Spata
ያለእነሱ እንቅስቃሴም እጎአ መጋቢት 9 ቀን 1990 የተካሄደው ነፃ ሕዝባዊ ምርጫ፣ ብሎም የጥቅምት 3፣ 1990 ውኅደትም ባልታሰበ ነበር። ያንን መቼም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም።»
መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል1.500 እንግዶች በተገኙበት የሐኖቨሩ ንግግራቸው ወቅት ጀርመን ውስጥ በሚገኙ ተገን ጠያቂዎች እና ስደተኞች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት «አስፀያፊ» ነው ብለዋል። ጀርመን ውስጥ የአይሁዶች ንብረት አሁንም ድረስ በፖሊስ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑ፣ ሰዎች በፀረ-ሴማዊ አቀንቃኞች ዛቻ ማስተናገዳቸው ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
በሐኖቨሩ ንግግር ወቅት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮኣሒም ጋውክ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታዋቂ ፖለቲከኞች እና የማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል። ሜርክል በንግግራቸው ወቅት ሩስያ ክሬሚያ የተሰኘውን ግዛት መጠቅለሏን፣ እንዲሁም እስላማዊ መንግስት የተባለው ቡድን በሶሪያ እና በኢራቅ ያሰፈነውን ስጋት በተመለከተም አውስተዋል።
ተክሌ የኋላ
ማንተጋፍቶት ስለሺ