1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አከራካሪው የዩጋንዳ የጤና ባለሞያዎች የሥራ ጉዞ

ዓርብ፣ የካቲት 27 2007

የኡጋንዳ መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጤና ባለሞያዎችን ወደ ካረብያዋ ሃገር ትሬኔዳድና ቶቤጎ ሊልክ ማቀዱ እያወዛገበ ነው ። የጤና ባለሞያዎች እጥረት ካለባት ከኡጋንዳ እነዚህ ሙያተኞች ወደ ሌላ ሃገር ይሄዳሉ መባሉን መንግሥትን እያስተቸው ነው ። መንግሥት ግን ኡጋንዳ በዚህ ታተርፋለች እንጂ እትጎዳም ይላል ።

https://p.dw.com/p/1EmMD
ምስል AFP/Getty Images/I. Kasamani

መንግሥት በበኩሉ የጤና ባለሞያዎቹ ወደ ትሬኔዳድና ቶቤጎ በመሄዳቸው ኡጋንዳ ብዙ ታተርፋለች እንጂ እትጎዳም ሲል ይከራከራል ።

የኡጋንዳ መንግሥት ከ200 በላይ የሚሆኑ የኡጋንዳ ሐኪሞችና ነርሶችን በመጪዎቹ ወራት ውስጥ ወደ ትሬኔዳድና ቶቤጎ ለመላክ የሚያስችል የጋራ ስምምነት ላይ ደርሷል ። የዩጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለው የስምምነቱ ዓላማ የትሬኔዳድና ቶቤጎን የጤና አስተዳደር ስርዓት ማጠናከር ነው ። ከትሬዳንድ ና ቶቤጎ በኩል የቀረበውን ይህን ጥያቄም መንግሥት በደስታ እንደተቀበለው የዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፍሬድ ኦፖሎት ተናግረዋል ።

«የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አንዳንድ የጤና ሠራተኞችን ወደ ውጭ ለመላክ እንዲስማማ የቀረበለትን ጥያቄ በደስታ ተቀብለናል ። የሃገሪቱን አቅምና ብቃት ሳይገመግሙ አይቀሩም ። እናም 200 300 የጤና ባለሞያዎች ከሃገሪቱ ቢሄዱ በጎደለው መሙላት የሚችሉ ሌሎች አሉ ማለት ነው »

Uganda Krankenhaus Symbolbild
ምስል AFP/Getty Images/M. Sibiloni

ወደ ትሬኔዳድና ቶቤጎ የሚሄዱትን ሀኪሞችና ነርሶችም የዩጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርና የትሬኔዳድና ቶቤጎ መንግሥት ተወካይ ናቸው የሚመርጡት ።ቃል አቀባይ ኦፖሎት እንደሚሉት ካሬብያዊትዋ ሃገር ትሬኔዳድና ቶቤጎና ዩጋንዳ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ የሆኑበት የረዥም ጊዜ ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት ናቸው ።በተለይ ግንኑነታቸው ይበልጥ የተጠናከረው በዩጋንዳ ነዳጅ ዘይት ከተገኘ በኋላ ነው ። ትሬኔዳድና ቶቤጎ በነዳጅ ዘይት ዘርፍ የተሰማሩ የዩጋንዳን ባለሞያዎች በማሰልጠን ረድታለች ። ምንም እንኳን ትሬኔዳድና ቶቤጎ የዩጋንዳ ባለውለታ ብትሆንም በርካታ የጤና ባለሞያዎች ወደ ዚያች ሃገር መላካቸው ግን አግባብ አይደለም ይላሉ የኡጋንዳው የመንግሥት ፖሊሲ ጥናት ተቋም በምህፃሩ IPPR ሃላፊ ጀስቲንያን ካቴራ ።

«በኛ አመለካከት ለትሬኔዳዳውያን ጥቅም ሲባል ከዩጋንዳ የጤና ባለሞያዎችን መውሰድ አሳማኝ ምክንያት የሌለውና ህገ ወጥም ነው ። በሃገራችን አሁንም እጅግ ግዙፍ የሆኑ የህክምናና የጤና ችግሮች አሉብን ። »

ተቋሙ አሁን ዩጋንዳ የጤና ባለሞያዎችዋን ለመላክ ያወጣችውን እቅድ በአፍሪቃ ትልቅ ችግር ከፈጠረው የምሁራን ኩብለላ ወይም ፍልሰት ጋር የሚስተካከል አድርጎ ነው የሚያየው ።ይህን በመቃወምም መንግሥትን እስከመክሰስ ደርሷል ።ካቴራ እንደሚሉት ትሬኔዳድና ቶቤጎ ከምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሃገር ከኡጋንዳ በ10 እጥፍ የሚበልጡ ሐኪሞች አሏት ። የዩጋንዳ ሆስፒታሎች ግን በበሽተኞች እንደተጣበቡ ነው የሚሉት ካቴራ በሃገሪቱ ለ25 ሺህ ሰዎች አንድ ሐኪም ብቻ እንደሚደርስ ነው የሚያብራሩት ። በአዳጊ ሃገራት የጤና አጠባበቅን እንዲሻሻል የሚሰራው ኢንትራ ሄዝ የተባለው ተቋም የዩጋንዳ ተጠሪ እንደሚሉት ከሁለት የዩጋንዳ ህፃናት አንዱ ሁለት ዓመት ሳይሞላው ይሞታል ። ከሃገሪቱ ወላድ ሴቶች 40 በመቶው የሚሆኑት ብቻ ናቸው በህክምና እርዳታ የሚገላገሉት ።በርሳቸው አስተያየት ዋናው ችግር የጤናው ዘርፍ የተመደበለት ገንዘብ አነስተኛ መሆኑና በቂ ባለሞያዎችም አለመኖራቸው ነው ። ባለሞያዎቹ እነዚህን መሰል መከራከሪያዎችን ቢያቀርቡም የመንግሥት ቃል አቀባይ አፖሎት ግን ኡጋንዳ የጤና ሙያቶችን ወደ ውጭ በመላክዋ አትራፊ እንጂ ተጎጂ አይደለችም በሚለው አቋማቸው እንደፀኑ ነው ።

Uganda Kampla Protest gegen Gesundheitssystem
ምስል Getty Images/AFP/K. Isaac

« በትሬኔዳድና ቶቤጎ የሕክምና መሣሪያዎቹና በአጠቃላይ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ከዩጋንዳ በጣም የተሻለ ነው ። እነዚህ ሰዎች ከ3 ዓመት በኋላ ሲመለሱ ዩጋንዳውያን ከሚያገኙት ልምድ ከሚያዳብሩት ክህሎት በእርግጠኝነት ተጠቃሚ ይሆናሉ ። ጥቅሙ እጅግ በርካታ ነው ። »

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ