1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢዉ የቱርክ ያለመከሰስ መብት ማሻሻያ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 2008

የቱርክ ምክር ቤት አባላትን ዱላ ያማዘዘዉ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እስከ መጭዉ አርብ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ያለመከሰስ መብትን የሚደነግገዉን የሕገ መንግሥት አንቀፅ ለማሻሻል የሃገሪቱ ምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ ቢከራከሩም እስካሁን ዉሳኔ ላይ አልደረሱም።

https://p.dw.com/p/1IpHs
Türkei Schlägerei im türkischen Parlament
ምስል Reuters/Stringer

የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ኩርዶችን በሚደግፈዉ የ «HDP » ፓርቲ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። ምክር ቤቱ ዉሳኔ ላይ ደርሶ የሕግ ማሻሻያዉ ከተደረገ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት እንደሚነሳ ነዉ የተመለከተዉ።

የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብትን በሚደነግገዉ የቱርክ ሕገ-መንግስት አንቀፅን ለመለወጥ የምክር ቤቱ አባላት የሚያደርጉት ክርክር ዛሬ ከቀትር በኃላም ቀጥሎአል። ማሻሻያዉ እስከፊታችን አርብ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ዉሳኔዉ ከፀደቀ ለወደፊቱ የፓርላማ አባላት ያለመከሰስ መብትን ለማንሳት ቀላል ይሆናል። ይህ የታቀደዉ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ የሚያነጣጥረዉ በተለይ ኩርዶችን በሚደግፈዉ የ «HDP » ፓርቲ ላይ መሆኑ ነዉ የተመለከተዉ። ምክንያቱ ደግሞ ከ 59 የ «HDP » ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች 50 ዉ ላይ ያለመከሰስ መብታቸዉ እንደሚነሳ ነዉ ማመልከቻ የቀረበዉ። ብዙዎቹ የ HDP » ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች የሽብርተኛዉን የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ «PKK»ን ትደግፋላችሁ በሚል መንግስት ይወነጅላቸዋል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የ«HDP » ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች የረጅም ዓመት የእስራት ብይን ያሰጋቸዋል። «HDP » ፓርቲ በበኩሉ እንዲህ አይነቱ ዉንጀላ ፓርቲዉ ላይ የመንኮታኮት እጣ ፈንታ ደቅኖበታል ሲል ስጋት ገብቶታል።

Symbolbild Türkei Ankara Parlament
ምስል picture-alliance/dpa/Str

ኮርዶች በብዛት በሚኖሩበት ደቡባዊ ቱርክ ታንኮች ሲሽከረከሩ፤ መንገዶች በፍርስራሽና አመድ ተሞልተዉ ይታያል። የቱርክ መንግሥት እንደሚለዉ ከሆነ አሸባሪዉን የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ (PKK) መዋጋት ያስፈልጋል። ወይም ደግሞ ከኩርዶች ጋር ወገንተኛ የሆነዉ የቱርክ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ « HDP» እንደሚለዉ የመንግሥት ጦር ከገዛ ሕዝቡ ጋር የጀመረዉ ጦርነት ነዉ። « HDP» የተሰኘዉ የቱርክ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር ሴላሃቲን ዴሚርታስ ፤

« በስድስት ጄኔራሎች የሚታዘዙ 10.000 ወታደሮች አንድ አካባቢን ሲወሩ፤ ሕዝብ ሊከላከል ይነሳል። መንግሥት ቤት ለቤት እየገባ ሲፈትሽና ሲያስስ ሕዝብ ላይ ጦርነት አዉጇል ማለት ነዉ። ርግጥ ነዉ ከዚህ በኃላ ሕዝቡም ለመከላከል ይነሳል። »

እንደ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራቺብ ታይብ ኤርዶዋን ከሆነ የ« HDP» ፓርቲ ሊቀመንበር ለእንደዚህ አይነቱ ንግግራቸዉ እስር ቤት በተወረወሩ ነበር። « ሂዮማን ራይትስ ዎች» የመሳሰሉት የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን የቱርክ መንግስት ጠንካራ ክርኑን እየተጠቀመ ነዉ። በሚያካሂደዉ ወታደራዊ ዘመቻ ለሲቪል ማኅበረሰብ ጥንቃቄን አያደርግም በማለት ይወነጅሉታል። ግን እንዲህ አይነቶቹ ወቀሳዎች ፕሬዚዳንት ኡርዶኻን ላይ ነጥረዉ ብቻ ነዉ የሚመለሱት፤

Türkei Ankara Präsident Recep Tayyip Erdogan
ምስል Getty Images/AFP/A. Altan

የ«HDP » ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች ያለመከሰስ መብታቸዉን በመጠቀም ክልክል የሆኑ ነገሮችን ይፈፅማሉ ሲሉ ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ለተደጋጋሚ ጊዜ ወቀሳ ሲያሰሙ ተደምጠዋል።

«የፓርላማ ተወካዮቹ ያለመከሰስ መብታቸዉን ከለላ በማድረግ አሸባሪ ቡድንን ይደግፋሉ።»

ኤርዶዋን ከአንድ ወር በፊት እንዲህ ብለዉ ተሳድበዉም ነበር።

«ምክር ቤቱ ይህን ያመከሰስ መብት ጥሰትን በትግስት ማየት አይችልም። ምክር ቤቱና የሃገሪቱ የፍትህ ስርዓት ከአንድ አሸባሪ ድርጅት አባል እኩል በሚንቀሳቀሱ የምክር ቤት ተወካዮች ላይ ርምጃ መዉሰድ ይኖርባቸዋል።

ቱርክን የሚያስተዳድረዉ የፍትሕ እና የልማት ፓርቲ በቱርክኛ አፅሮቱ «AKP» የሕገ-መንግሥት ለዉጥ በማድረግ የፓርላማ ተወካዮች ያለመከሰስ መብታቸዉን በቀላሉ ለማንሳት እንዲችል መንገድ እያስተካከለ ነዉ። ሕጉን በሚመለከት ፓርላማ ዉስጥ በተደረጉት ዉይይቶች ላይ ለሦስት ጊዜ ዱላና ቦክስ ያሰናዘረ ከፍተኛ ብጥብጥ ተካሂዶአል። ሕገ-መንግሥቱን ለመቀየር የሚያስችል አብላጫ ድምፅ አስተማማኝ እየሆነም መጥቶአል። የፊታችን አርብ የቱርክ ምክር ቤት በአለመከሰስ ሕጉ ላይ የለዉጥ ዉሳኔዉን ያፀድቃ ተብሎ ይጠበቃል።

ቶማስ ብሮማን / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ