1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትንበያ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2009

ኢትዮጵያ  የተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ  ዝቅተኛ የገቢ መጠን አላቸዉ ብሎ ካስቀመጣቸዉ 48 የዓለም ሃገሮች አንዷ ናት።በተቋሙ የዘንድሮ የትንበያ ሪፓርት ከ2021 እስከ 2024 ድረስ ባሉት ዓመታት  16 ሀገሮች ከዝቅተኛ ወደ መካካለኛ ገቢ ይሸጋገራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።  ኢትዮጵያ ግን  በዝርዝሩ ዉስጥ አልተካተተችም።

https://p.dw.com/p/2UxRB
Afrika Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ትንበያ

የኢትዮጰያ ሁለተኛዉ የእድገትና  የትራንስፎርሜሽን  እቅድ በጎርጎሮሳዊ የዘመን ቀመር 2025 ሀገሪቱ ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ሃገሮች ተርታ እንደምትሽጋገር  ያስረዳል። በእቅዱ መሰረትም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት እንደተመዘገበ መንግስት ሲገልጽ ቆይቷል ። የዓለም ባንክን የመሳሰሉ  አበዳሪ  ድርጅቶችም  ተገኘ የተባለዉን  እድገት ይስማሙበታል ከሰሞኑ የወጣዉ  የተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ  የትንበያ ዘገባ ግን  ከዚህ የተለየ ነዉ።
ኢትዮጵያ  በተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ  ዝቅተኛ የገቢ መጠን አላቸዉ ብሎ ካስቀመጣቸዉ 48 የዓለም ሃገሮች አንዷ ናት።  እነዚህ  ሀገሮች በተባበሩት  መንግስታት የልማት ፓሊሲ ኮሚቴና በገለልተኛ  የባለሙያዎች  ቡድን  በየሦስት ዓመቱ ሀገራቱ  ያሉበት የኢኮኖሚ ደረጃ ተጠንቶ ክለሳ ይደረግበታል። በጥናቱ መሰረትም ሀገሮቹ ካሉበት ዝቅተኛ የገቢ መጠን ወደ መካከለኛ የሚያደርጉትን ሽግግር በተመለከተ  ተቋሙ ትንበያዉን  ያስቀምጣል። የተባበሩት መንግስታት  የንግድና ይልማት ጉባኤ በምህጻሩ «ዩ ኤን ሲ ቲ ኤ ዲ » ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ  ቀጠና ሃላፊ በዶክተር  ጆይ ካቲኔካዋ ይፋ በተደረገዉ የዘንድሮዉ የትንበያ  ሪፓርት እንደተመለከተዉ ኢትዮጵያን ሳይጨመር  16 ሃገራት ከዝቅተኛ የገቢ መጠን ወደ መካከለኛ ይሸጋገራሉ።  የነፍስ ወከፍ የገቢ መጠን ፤ የሰዉ ሃብት ልማትንና  የኢኮኖሚ ተጋላጭነትን ተቋሙ መስፈርት  አድርጎ  ምዘና ያካሄደ ሲሆን በእነዚህ መስፈረቶች ተመዝነዉ በጎርጎሮሳዊ የዘመን ቀመር ከ 2017 እስከ 2024  ባሉት  ዓመታት ወደ መካከለኛ ገቢ ይሸጋገራሉ ተብሎ  ከተተነበየላቸዉ  ሃገራት ዉስጥ  ኢትዮጵያ  በሪፓርቱ  አልተካተተችም። ዩኤስ አሜሪካ በሚገኘዉ የዊሲከንሲን ዩኒቨርሲ የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዳንኤል ተፈራ ሀገሪቱ በሪፓርቱ ያልተካተተችበትን ምክንያት እንዲህ ያብራራሉ።
ተቋሙ በትንበያ ሪፓርቱ  እንድስቀመጠዉ   ከ16 ቱ ሃገራት መካከል ከአፍሪካ  አንጎላና ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ እንዲሁም ደቡብ  ፓስፊካዊቷ  ሃገር  ቫናቱ በጎርጎሮሳዊዉ ዘመን ቀመር  እስከ 2021 ካላደጉ ሃገራት ተረታ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ሃገራት ተርታ ይገባሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ጎረቤት ጅቡቲን ጨምሮ  ቀሪዎቹ  ያላደጉ 13  የዓለም ሃገራትም ከ 2021 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ተመሳሳይ ሽግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።የተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ ዳጎስ ባለዉ የትንበያ ሪፓርቱ ይፋ እንዳደረገዉ ሃገሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ለመሸጋገር በሦስት  ዓመታት በአማካኝ 1035 ዶላር ዓመታዊ  የነብስ ወከፍ  ገቢ  ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መስፈርት ኢትዮጵያ ስትመዘን ከ800 ዶላር በታች በሆነ  ዓመታዊ  የነፍስ ወከፍ ገቢ ከማያሟሉት ሀገሮች ዉስጥ ተቋሙ መድቧታል። የዓለም ባንክ ባለፉት ዓመታትና ከተቁሙ የትንበያ ሪፓርት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ አዉጥቶት በነበርዉ  ሪፓርት ግን  ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ያለች ሀገር እንደሆነች ገልጾ ነበር። ትንበያዎቹ  ለምን ተለያዩ? ዶክተር ዳንኤል ተፈራ ይናገራሉ።በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠዉ የተቋሙ መስፈርት የሰዉ ኃብት መጠንን የሚመለከት ሲሆን የተመጣጠነ አመገባብ ፣ጤና በተለይም የህጻናት ሞት ቁጥር፣ በትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ወይም የተማሪዎች ጥምርታ እንዲሁም የተማረዉ ህዝብ ብዛት ጠቋሚ ይሆናሉ ተብለዉ ተቀምጠዋል። በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠዉ የሀገሮች መመዘኛ መስፈርት ደግሞ የኢኮኖሚ ተጋላጭነት ነዉ። በዚህ መስፈርት የተፈጥሮ አደጋ መለትም በአደጋዉ ወቅት በግብርናዉ ዘርፍ የተረጋጋ ምርታማነት መኖርና ለአደጋ ተጋላጭ የሆነዉ ህዝብ ቁጥር፣ የእቃዎችና የአገልግሎቶች የተረጋጋ ኤክስፖርት ማለትም ከንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ አሉታዊ ክስተቶች በመለኪያነት ተቀምጠዋል። የተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ ሪፓርት  ከላይ በተጠቀሱት መመዘኛዎች መሰረት ኢትዮጵያ በመጭወቹ አስር ዓመታት ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ የገቢ መጠን ከሚሸጋገሩ ሀገራት ተርታ በትንበያዉ የለችም። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ መፍትሄ ይጠቁማሉ።የባህር በር አለመኖር ለኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት ተደርጎ በተቋሙ ትንበያ ተወስዷል።የባህር በር የሌላቸዉ ሀገሮች አነስተኛ የኢኮኖሚ ነጻነትና የዉጭ ንግድ ዉሱንነት ተግዳሮቶች ቢኖሩትም ይህንን ተቋቁመዉ ኢኮኖሚያቸዉን ያሻሽላሉ ተብለዉ እንደ ቦትስዋና ያሉ ሀገሮች በተቋሙ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።በተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ በዝቅተኛ ደረጃ ያደጉ ተብለዉ ከተቀመጡት 48 የዓለም ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 33ቱ የአፍሪካ ሀገሮች ናቸዉ።የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በተለይ ስንመለከት ደግሞ ከኬንያ በስተቀር ሁሉም  የቀጠናዉ ሀገራት በዚሁ ደረጃ ዉስጥ የተካተቱ ናቸዉ። ለመሆኑ ኬንያ ምን የተለየ የኢኮኖሚ ተሞክሮ ቢኖራት ነዉ? የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ ዶክተር ዳንኤል ይገልጻሉ።እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ መንግስትም ይሁን የዓለም ባንክ እንዲሁም የተባብሩት መንግግስታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባኤ ያላቸዉ ትንበያ ምንም ይሁን ምን የህዝቡን ኑሮ በተጨባጭ ለማሻሻልና በሀገር ዉስጥ ጉልበትና ሀብት የተመሰረተ ስራ ከተሰራ ጥሩ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል። የተባበሩት መንግስታት የንግድና የልማት ጉባኤ በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ያሉ ሀገሮችን ወደ መካከለኛ የሚያሸጋግረዉ የመመዘኛ መስፈርት  45 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ከ5 የማይበልጡ ሀገራት ብቻ ካላደጉ ሀገራት ተርታ መዉጣት ችለዋል።

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien
ምስል DW
Äthiopien Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa
Äthiopien Bonga Kaffee Äthiopien 9
ምስል DW/J. Jeffrey

ፀሐይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ