1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የላይቤሪያ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 28 2004

አወዛጋቢው የላይቤሪያ ምርጫ ጥላ ባጠላበት ሁኔታ ዛሬ ሲካሄድ ዋለ። ቅድመ ምርጫው ለሀገሪቱ ሴት ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ያደላ ነው በሚል ዋነኛ ተፎካካሪው ዊንስተን ተብማን ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ተዘግቧል። ትናንት በዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ በተቀሰቀ ግጭት ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/RvNX
የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰንምስል dpa - Report

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ላይቤሪያ ዛሬ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ዋለ። ከማለዳው ጀምሮ የወጡት መራጮች ቁጥር ባለፈው ወር ለመጀመሪያው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከወጡት አንፃር አነስተኛ እና ዘገምተኛ መሆኑ ተዘግቧል። በተለይ ዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጭምር ጥበቃ እየተደረገላት ነው ምርጫው የተከናወነው። ለዚያ ደግሞ ምክንያቱ ትናንት በሀገሪቱ በተከሰተ ብጥብጥ ቢያንስ የአራት ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ነበር። የትናንትናው ግጭት የተቀሰቀሰው ዋነኛ የምርጫ ተፎካካሪው ዊንስተን ተብማን ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ከወጡ በኋላ እንደነበረም ተዘግቧል። ተብማን ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ዛሬ በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ በዚህ መልኩ ነበር ቀደም ሲል የገለፁት፥ «ላይቤሪያውያን ማክሰኞ ከቤታቸው እንዳይወጡ ጥሪ ማቅረቤ በዚህ የምርጫ ሂደት ፕሬዚዳንቷ አደጋ ላይ የጣሉትን ዲሞክራሲያችን እና ሰላማችንን ለማስጠበቅ ነው» ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በመላ ላይቤሪያ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኤለን ጆንሰን ዋነኛ ተፎካካሪያቸውን ማሸነፋቸው ይታወቃል። የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪቃዊት መሪ ሆነው ከ5 ዓመታት በፊት በላይቤሪያ የተመረጡት ኤለን ጆንሰን ባለፈው ወር ምርጫ 44 ከመቶ ድጋፍ ነበር ያስመዘገቡት። ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ዊንስተን ተብማን ደግሞ 33 በመቶ የመራጮች ድጋፍ ማግኘታቸው ይታወቃል። ተብማን ከቀድሞው እውቁ የኤስ ሚላን እግር ኳስ ተጫዋች እና የዘንድሮ ምርጫ ተወዳዳሪ ጆርጅ ዊሃ ጋር በመጣመር ነው 33 በመቶውን ድጋፍ ያገኙት። ሆኖም በጆርጅ ዊሀና በዊንስተን ተብማን ለምርጫ የተጣመረው Congress for Democratic Change ፓርቲ ራሱን ከሁለተኛው ዙር ምርጫ ማግለሉን አስታውቋል። የሐገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ በተቃዋሚዎች የተጠራውን ለምርጫ አትውጡ ተቃውሞ በዚህ መልኩ ነበር የተቃወሙት፥ «ማንኛውም ፖለቲከኛ ሀገራችንን በእገታ እንዲይዝ አትፍቀዱለት። ሚስተር ተብማን በምርጫው አልሳተፍም በማለት በተሳሳተ መንገድ የሚያደርጉትን ጥሪ አትቀበሉ። እያደረጉ ያሉት ምርጫው ወደመጨረሻው ውጤት እንዳይጓዝ ማስተጓጎል ነው። ያን ማድረጋቸው ደግሞ ስለፈሩ ነው!» ባለፈው ወር በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ያገኙት ድምፅም ሆነ ዋነኛ ተፎካካሪው ያስመዘገቡት ድምፅ ለፕሬዚዳንትነት የሚያበቃ አልነበረም። ለዚያም ነው ሁለተኛ ዙሩ ምርጫ ዛሬ የተከናወነው። ዋነኛ ተቀናቃኙ ተብማን የመጀመሪያው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል ማለታቸው በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል። ቁጥራቸው ከ4000 በላይ የሆኑ የዓለም አቀፍ እና የሀገር በቀል የምርጫ ታዛቢዎች የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ መታዘባቸው ይታወቃል። በላይቤሪያው ሁለተኛው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲያካሂዱ የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች ከጥቂት ደቂቃ በፊት ተዘግተው ምርጫው መጠናቀቁም ታውቋል።

Liberia Wahlen in Monrovia Winston Tubman
ዋነኛ የምርጫ ተፎካካሪው ዊንስተን ተብማንምስል DW

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ