1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የፕሮፌሰሩ ንግግር

ዓርብ፣ ጥር 19 2009

የፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ንግግር በርካቶችን አወዛግቧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊነት 3 ተወዳዳሪ ውስጥ ገብተዋል። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ለበዓለ ፋሲካ እንደሚያወጣ ይፋ አድርጓል። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሩት የሆሊውድ ግስጋሴ።

https://p.dw.com/p/2WToz
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

አወዛጋቢው የፕሮፌሰሩ ንግግር ፥ ዶ/ር ቴድሮስ 

ድንገተኛ ክስተት አይደለም። በየጊዜው ወሰድ መለስ ያደርገዋል። ሄዶ ሲመለስ ታዲያ በርካቶችን በስሜት እየነዳ ማንሳፈፉ አይቀርም። እንደ ቦይ ውኃ አይነት ነገር። በአንድ ወገን ቁጣን እያስደፈቀ የሚያምሰገስግ፤ ደግሞ በሌላ ወገን በኩራት የሚያንጎማልል፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የምሁራን ትንታኔ። ፋታ ወስዶ ዳግም ያጠዛጥዝ ይዟል።  የዓለም ጤና ድርጅት የመጨረሻዎቹ ሦስት ተወዳዳሪዎቹን ይፋ አድርጓል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም አንዱ መሆናቸው፦ ደጋፊም ነቃፊንም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዳግም አስነስቷል። የኢትዮጵያዊው ዶክተር ልጅ በትወናው ዓለም የሆሊውዱ ኦስካር ዕጩ ኾናለች። 

የኢትዮጵያ አንድነት እና የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ጽንፍ በያዘ መልኩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ሲፋጩ መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ከሰሞኑ፦ ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ «ማነው ኢትዮጵያዊ?» በሚል ርእስ በኢሳት ቴሌቪዝን ቀርበው የሰጡት የታሪክ ትንታኔ የሁለቱ ቡድን ንትርክን ዳግም አንሮታል። ቃለ ምልልሱ ወደ ሦስት ሰአት ግድም የፈጀ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ከኋላ ተነስቶም እስካለንበት ዘመን ድረስ ይቃኛል።

ከቃለመጠይቁ የተቀነጨበ አጠር ያለ የቪዲዮ ምስልን ብዙዎች በፌስቡክ እና ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተቀባብለውታል። የኦሮሞ ብሔር አቀንቃኞች ፕሮፌሰሩ አንድ የተወሰነ ማኅበረሰብን ዘልፈዋል ሲሉም ቅሬታ እና ቁጣቸውን አንጸባርቀዋል። ሌሎች በበኩላቸው የለም ፕሮፌሰሩ የነበረውን ታሪክ እውነት በመነገራቸው ሊመሰገኑ ይገባል እንጂ ሊወቀሱ አይገባም ብለዋል። 

Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

የፕሮፌሰሩ ረዥም ቃለ-ምልልስን በመንተራስ በአንድነት እና በብሔርተኝነት አቀንቃኞች መካከል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰነዘሩ ቃላት ብዙዎችን አስተዛዝበዋል። ዱላ ቀረሹ እንኪያ ሰላንታ በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያየ ቋንቋ እና ባሕል ያላቸውን ማኅበረሰቦች መስተጋብር እና ግንኙነት የሚሸረሽር ነው ሲሉም የተቹ አሉ። 
በእርግጥም መሰል እሰጥ አገባ የኢትዮጵያ ታሪክ ትንታኔ በተሰጠ ቁጥር ብቅ እያለ የአንድ ሰሞን ግርታ ከመሆን አያልፍም ሲሉም የሰሞኑን ንትርክ ያጣጣሉ አልታጡም። ለዚህ ማስረጃቸው ደግሞ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ርእሰ-ጉዳዮች በተለያዩ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ተነስተው የዛ ሰሞን ብዥታ ሆነው ጠፍተዋል የሚል ነው። 

ከዚህ ቀደም ከተከሰቱ እሰጥ አገባዎች መካከልም የቅርብ ጊዜዎቹን ለማስታወስ ያህል፦ የፕሮፌሰር  ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍን ማንሳት ይቻላል። ፕሮፌሰሩ የአማራ እና የኦሮሞ ማኅበረሰብ የዘር ግንዳቸው አንድ እንደሆነ፤ በኢትዮጵያ ነባር ህዝቦች እንደሆኑ፤ መጤም እንዳልሆኑ መጥቀሳቸውን ያደነቁ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ውግዘት ያሰሙም ነበሩ።  አንዳንዶች መጽሐፉን በማኅበረሰቦች መካከል ቅራኔ እንዲነሳ የሚለፉ ግለሰቦችን ሴራ ማርከሻ ምርጥ ሥራ ሲሉ አድናቆት ሰጥተው ነበር። ሌሎች ደግሞ መቀራረብን ለመፍጠር «የተፈበረከ ተረት ተረት» ሲሉም ተችተዋል። በጊዜው ጉዳዩ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ኾኖ አልፏል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ «የኦሮሞ ቻርተር» በሚል በውጭ ሀገር በሚኖሩ የብሔር አቀንቃኞች ሲነሳ፤ በዚያው ሰሞን የአንድነት አቀንቃኞች «የኢትዮጵያ ቻርተር» በሚል ስብሰባ ያደርጉ ነበር። የዚያን ሰሞንም ልክ እንደ አሁኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎቹ እስኪበቃቸው ተጠዛጥዘዋል። ያም ያንድ ሰሞን የቦይ ውሃ መስሎ አልፏል። 
በዚህ መሀል ከሁለቱም ወገን ውጪ ሆነው ነገሮቹን ግራ በመጋባት የሚመለከቱ ወገኖች፦ የሚለኮሱ የንትርክ እሳቶች ላይ ነዳጅ ላለማርከፍከፍ ቁጥብ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተስተውለዋል። የራሳቸውን ግላዊ ዝና እና ስም ለማግነን ግራ ቀኙን የሚቧጥጡት መበራከታቸው አስደማሚ ነው ያሉም አሉ። ዝምታም የመረጡ አልታጡም።

Karte Äthiopien englisch

እንዲህ ወደ ኋላ እና ወደፊት እየተናጠ የሚመላለሰው ንትርክ የሰሞኑ የፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ቃለ ምልልስ እንደተሰማ እንደገና አገርሽቷል። በተለይ በፌስቡክ ታዋቂ ጸሐፍትን ጽንፍ አስይዞ በሚያስተዛዝብ መልኩ አሟግቷል። ከግራ ከቀኝ ማስረጃዎችን እያጣቀሱም አንዱ ሌላኛውን ከስህተቱ እንዲታረም ለማድረግም የጣሩ ተስተውለዋል። 
የሀገር ውስጥ ልሂቃን እና የውጭ ሀገር አሳሾች ምንጮች እየተቀነጣጠቡ እዚህም እዚያም ሲሰነቀሩ ተስተውለዋል። ጸሐፍቱ ባልኖሩበት ዘመን የኋልዮሽ ሽምጥ እየጋለቡ መጠዛጠዛቸው ማብቂያ ያለው አይመስልም። ከንትርክ ውይይትን፤ ከመጓተት መቀራረብን፤ እንደ ቦይ ከመስፍሰስ ተሰባስቦ መነጋገር ላይ ቢያጤኑበት የተሻለ እንደሆነ የሚወተውቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ስጋትን ከወዲሁ መለስ ብሎ ማጤኑ አይከፋም። ነገ በሚቀደደው ቦይ ላለመፍሰስ ምን ማረጋገጫ አለና።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ኃላፊነት ከተወዳደሩ ዕጩዎች መካከል የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ውስጥ መካተታቸው ረቡዕ እለት ከጄኔቫ እንደተገለጠ ድጋፍም ተቃውሞም ተስተጋብቷል። ደጋፊዎቻቸው በዶክተሩ መመረጥ ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል። መመረጣቸው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃም ኩራት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዶክተር ቴድሮስ መመረጥን የሚቃወሙም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሁንም ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። ዶክተሩ መመረጥ የለባቸውም ሲሉም በትዊተር እና በሌሎች መገናኛዎች ዘመቻቸውን ቀጥለዋል። 

ዜጎችን ከሚበድል፣ ከሚያስር፣ ከሚያንገላታ እና ከሚገድል ቡድን ጋር አብረዋልና ከፍተኛው ዓለም አቀፋዊ አመራር አይገባቸውም ሲሉ ተቃውመዋል።  የለም ዶክተር ቴድሮስ ያለቦታቸው የሚገኙ ሰው ናቸው ሊጸጸቱ ግን ይገባል ሲልም አስተያየት የሰጠ አለ። 

USA Academy Awards Oscarstatuen
ምስል Getty Images/C. Polk

  ጠጠር ካለው የፖለቲካ ርእሰ ጉዳይ ወጣ ብለን የጥበቡ ዘርፍንም በመጠኑ እንቃኝ። ከኢትዮጵያዊ አባት እና አየርላንዳዊ እናት የተወለደችው ተዋናዪት ሩት ነጋ ለኦስካር ሽልማት በምርጥ ሴት ተዋናይት ዘርፍ እጩ መሆኗ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በቀናነት የታየ ርእስ ነበር። በተዋናዪቷ መታጨትም በርካቶች ደሰታቸውን አንጸባርቀዋል። ብዙዎች መልካም ዕድል ተመኝተውላታል። ሩት በተለያዩ ታዋቂ መጽሄቶች ላይም ስሟ በተደጋጋሚ ተነስቷል። 

ኒውዮርክ የሚታተመው ቩልቸር ዳት ካም (Vulture.com)የተሰኘው መጽሄት በኢንተርኔት ባወጣው ሐተታ ምርጥ ሴት ተዋናዪት በሚለው ርእስ ስር ስለ ሩት ነጋ ጽፏል። ሩት «ላቪንግ» በተሰኘው ፊልም ብዙም ንግግር በሌለበት ትወናዋ ጎላ ጎላ ባሉት አባባይ አይኖቿ ተመልካቹን ገዳይ ናት ብሏል። ከፍተኛ ተነባቢነት ካላቸው መጽሄቶች መካከል (The hollywood reporter) የተሰኘው መጽሄት ከኢትዮጵያዊ ዶክተር አባት የተወለደችው ሩት ነጋ ከዐሥር ዓመት በፊት የነበራትን ጥረት አውስቷል። ሩት ሆሊውድ ለመድረስ ይህን ያህል ጊዜ የፈጀባት ለዚያ ብዙም ግድ ስለሌላት እንደነበር ገልጣለች። የኦስካር እጩ ተዋናዪት ለመሆን ግን በቅታለች። ሌላው ጥበባዊ የሆነው መነጋገሪያ አጀንዳ አርቲስት ቴዲ አፍሮ አዲስ የሙዚቃ አልበም ለበዓለ-ፋሲካ ለማድረስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን መግለጹ ነበር። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው ወዲያው ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ