1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮጳን ያሰጋው የስደተኞች ብዛት

ሰኞ፣ የካቲት 30 2007

ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት የአውሮጳን ድንበር የተሻገሩ ስደተኞች ቁጥር ከሐቻምናው በሶስት እጥፍ ጨምሯል ተባለ። ከዓመት ዓመት እየጨመረ ለመጣው የስደተኞች ቁጥር ሶርያ እና ሊቢያን በመሳሰሉ ሃገራት የሚታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1EnnV
Flüchtlinge in Melilla Polizei Grenzzschutz Grenzzaun Helikopter 06/2014
ምስል Reuters/Jesus Blasco de Avellaneda

ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በሶስት እጥፍ መጨመሩን አህጉራዊው ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት (Frontex) አስታወቀ። በማዕከላዊ የሜድትራኒያን ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ አውሮጳ የሚጓዙ ስደተኞች መነሻቸው ከሶርያ እና ሊቢያ መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ኢዛቤላ ኩፐር ተናግረዋል።
«በ2013 ከ100,000 የማይበልጡ ስደተኞች የአውሮጳ ህብረትን ድንበር አቋርጠዋል። በ2014 ግን የስደተኞቹ ቁጥር 280,000 ደርሷል። ጭማሪው አስደንጋጭ ነው። በዚህም በማዕከላዊ ሜድትራኒያን አካባቢ የሚገኙ ሃገራት በተለይም ጣልያን ከፍተኛ ተጽዕኖ ደርሶባቸዋል።»
በጎርጎርሳውያኑ 2014 ዓ.ም. 170,00 ስደተኞች ወደ ቱርክ ድንበር መድረሳቸውንና ከእነዚህ ውስጥ የሶርያ እና ኤርትራ ዜጎች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ኢዛቤላ ኩፐር ተናግረዋል። የአውሮጳ ሃገራት የነፍስ አድን ሰራተኞች ባለፉት ወራት ከሰሜን አፍሪቃ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ወደ አውሮጳ ለመግባት የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ህይወታቸውን ሲያጡ አልታደጉም የሚል ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት በሲሲሊ አካባቢ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በመስጠሟ 10 ሰዎች መሞታቸውን የጣልያን ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ለስደተኞቹ ቁጥር መጨመር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የሚታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ የአውሮጳ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት ቃል አቀባይ ኢዛቤላ ኩፐር ተናግረዋል።
«የሶርያ ጦርነት፣ የኤርትራ ጨቋኝ መንግስት እንዲሁም በኢራቅ፤አፍጋኒስታን፤ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ደቡብ ሱዳን ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ወደ አውሮጳ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። የሊቢያ ወቅታዊ ሁኔታ ለስደተኞቹ ቁጥር መጨመር የራሱ አስተዋጽዖ አበርክቷል።በሃገሪቱ የህግ የበላይነት መጥፋት፤የመንግስታዊ ተቋማት አለመኖር ወይም የህግ አካላት መፈራረስ እና የአገሪቱ አለመረጋጋት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በነጻነት እንዲሰሩ አድርጓቸዋል።እነዚህ ህገ-ወጦች ለባህር በማይመጥኑ ትናንሽ የአሳ ማስገሪያ ጀልባዎች በመቶ የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመጫን በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ትርፍ እያጋበሱ ነው »
በፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ላይ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የታመሰችው ሶርያ እና በአሜሪካን ጦር ማዕከላዊ መንግስቷ የፈረሰባት ኢራቅ ዛሬ የሞት እና ስደት ምድር ሆነዋል። ሊቢያ እንዲህ በቅርብ ጠንካራ መንግስት የሚኖራት፤ በኤርትራም ፖለቲካዊ ሁኔታው የሚቀየር አይመስልም። በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ወደ አውሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ገና ካሁኑ ጭማሪ ማሳየቱን የተናገሩት ኢዛቤላ ኩፐር የህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችም ተጨማሪ ፈተና መሆናቸውን ይናገራሉ።
«ባለፈው አመት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በደቡባዊ ቱርክ ከስራ ውጪ በሆኑ አሮጌ የጭነት መርከቦች ስደተኞችን ወደ ቱርክ ማሻገር ጀምረዋል።ይህ አዲስ እና አሳሳቢ ሁነት ነው።በምስራቃዊ የሜዲትራኒያን በኩል ያለው የስደተኞች ሁኔታም እየጨመረ ነው። በምዕራባዊ ባልካን የስደት መስመር በተለይ ከሰርቢያ እና ሃንጋሪ ድንበር የሚነሳውም አሳሳቢ ነው።አብዛኞቹ ከኮሶቮ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሰርቢያ ወደ ሃንጋሪ ይጓዛሉ።»
ኢዛቤላ ኩፐር የድንበር ቁጥጥር መፍትሄ አለመሆኑን ተናግረዋል። የስደተኞቹን ሃገራት ማረጋጋት፤ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

Flüchtlingsaufnahmelager der Caritas in Palermo, Italien
ምስል DW/B. Riegert
Schlauchboot Mittelmeer-Flüchtlinge Italien Symbolbild
ምስል picture alliance/ROPI


እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ