1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮፓና ያለግብር የሚሸሸው ሃብት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 12 2001

ግብር ሳይከፈልበት በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ ለባለሃብቶች ያመቹ ባንኮች በያመቱ የሚፈሰው ገንዘብ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ነው። ለመንግሥት ግብር የመክፈል ግዴታቸውን በመወጣት ፈንታ ገንዘባቸውን ወደ ውጭ ለሚያሸሹ ኩባንያዎችና ግለሰቦች እነዚህ ባንኮች ልዩ ማራኪነት አላቸው።

https://p.dw.com/p/FerG
ፔር ሽታይንብሩክ
ፔር ሽታይንብሩክምስል AP

ምንም ወይም ቢበዛ ጥቂት ግብር ቢጠይቁ ነው፤ የባንክ ሚስጥርንም አሳልፈው አይሰጡም። በመሆኑም ቀዳዳውን ለመድፈን አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚደረገው ጥሪ በወቅቱ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ መልሶ ሲጠናከር ኦ.ኢ.ሢ.ዲ. በሚል አሕጽሮት የሚጠራው የኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ድርጅትም አየል ባለ ሁኔታ ቀዳዳውን ለመድፈን ተነሳስቷል።

ጊዜው ማለቂያው መቼ እንደሆነ በማይታወቅ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ የብዙሃኑ ፍጆተኛ የገንዘብ አቅምና ሁኔታ የተዳከመበት ነው። ይህም ሆኖ ግብር ሳይከፈልበት በስውር የባለሃብቶች-ገነት ወደሚባሉ የውጭ ሃገራት ባንኮች መፍሰስ የቀጠለው ገንዘብ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። መንግሥታት በዚህ ሁኔታ በያመቱ የሚያጡት የግብር ገቢ እንግዲህ መዓት ነው። ቢሰበሰብ ብዙ ማሕበራዊ ችግርን ሊያቃልል በቻለ ነበር።

በዚህ በአውሮፓ የፊናንሱን ስርዓት ከውድቀት ለመሰወር ባለፉት ሣምንታት መንግሥታት በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ አፍሰዋል። የባንኮች ቁጥጥርን ለማጠናከር፣ የፊናንሱን ገበዮች የገንዘብ ፍሰት በአግባብ ለመዘወር፤ በአጠቃላይ የፊናንሱን ስርዓት በአዲስ ለውጥ አስተማማኝ ለማድረግ ብዙ ዕርምጃና ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚሁ ተያይዞ የባለሃብቶችን ገንዘብ በስውር እየሳቡ የሚያስገቡትን አገሮች መውጫ ቀዳዳ ማሳጣቱም ከመቼውም ይልቅ ዛሬ አስፈላጊነቱ ታይቷል። የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ በጉዳዩ የጠራው ስብሰባ ትናንት ፓሪስ ላይ ተካሂዶ ነበር።

ግልጽ አሠራርን ለማራመድ የሚጥረው ድርጅት ትራንስፓረንሢያ ኢንተርናሺናል ግብር ለማይከፍሉ ባለሃብቶች-ገነት የሚሏቸው ባንኮች የሚገኙባቸው አገሮች በዓለም ላይ ከሃምሣ እስከ ሰባ ይደርሳሉ። የኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ድርጅቱ በዋነኝነት ባወጣው ብላክ-ሊስት ዝርዝር፤ በአውሮፓ የሚገኙት ሞናኮ፣ ሊሽተንሽታይንና አንዶራ ሰፍረዋል። ሆኖም ቢያንስ ሉክሰምቡርግን፣ አውስቲያንና በተለይም ስዊዝን የመሳለሉት የባንኩ ንግድ ተጠቃሚዎች በስበባው ላይ’ አለመገኘታቸው የትብብር ችግር መኖሩን የሚያመለክት ሲሆን ቅሬታን መፍጠሩም አልቀረም። በኦ.ኢ.ሢዲ. አማካይነት ከፈረንሣይ ጋር ስብሰባውን የጠራችው የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ በተለይም የስዊዝን ጎጂ ሚና ከፍ አድርገው ነው ያስቀመጡት።

“ስዊዝ የጀርመን ግብር ከፋዮች በአገር ግዴታቸውን በመወጣት ፈንታ ገንዘባቸው ወደርሷ እንዲያሻግሩ ሁኔታዎችን ታመቻቻለች። እና ከዚህ የተነሣ በተጠያቂነቱ ዝርዝር ውስጥ መስፈር ያለባት አገር ናት። ስዊዝ ከኛ ጋር ለመተባበር ዝግጁ የምትሆነው የግብር ማጭበርበር ወንጀል ሲኖር ብቻ ነው። ግን ለዚህ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል። ስዊዝ ደግሞ ይህን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደልም። ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው።”

ስዊዝን ካነሣን አይቀር የስዊዝ ባንኮች ስውር ሚና ከማንኛውም የላቀ ነው። ግብር ሳይከፍሉ ገንዘባቸውን በገፍ ወደዚያው ከሚያሸሹት ዓለምአቀፍ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ሌላ አገሪቱ የታዳጊ ሃገራት አምባገነኖችና በሙስና የተዘፈቁ ገዢዎችም የሕዝብን ገንዘብ እየዘረፉ የሚያከማቹባት አስተማማኝ አገር ናት። ማን ምን ያህል ገንዘብ አለው፤ ከየት አመጣው የባንኮቹና የተገልጋዮቻቸው ሚስጥር ነው። በአገሪቱ ባንኮች የተከማቸው ግዙፍ ንብረት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ለመናገርም አይቻልም።

የኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ድርጅቱ ኦ.ኢ.ሢ.ዲ. በመጪው ዓመት መጀመሪያ የግብር ሽሽትና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ማጥራት ድርጊት የሚያበረታቱ አገሮች ዝርዝሩን ከጊዜው በተጣጣመ መልክ ለማውጣት ያስባል። ከጥቁሩ ሰነድ ባሻገር ግብር ማጭበርበርንና ሙስናን በመታገሉ ተግባር የሚተባበሩ አገሮችን አረንጓዴ የተሰኘ ዝርዝር ለማቅረው ነው የሚያቅደው። ፔር ሽታይንብሩክ በበኩላቸው እንዳስገነዘቡት ገንዘቡ በሚፈስባችው አገሮች ላይ የሚደረገው የአውሮፓ መንግሥታት ግፊት ይበልጥ መጠናከር ይኖርበታል። እነዚሁ ሲያካሂዱት በቆየው አስተማማኝ ያልሆነ ንግድ የወቅቱ የፊናንስ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ ድርሻ አላቸው ባይ ናቸው።

“እኛጋ ብዙ ሕዝብ በፊናንሱ ቀውስ፥ ለዘርፉ ባለሥልጣናት ከሚከፈለው ከፍተኛ ደሞዝና መደጎሚያ ካሣ፤ እንዲሁም በዘርፉ በተናጠል ከሚታየው የግብር ማጭበርበርና ሙስና የተነሣ በማሕበራዊና በኤኮኖሚ ስርዓታችን ላይ ቀስ በቀስ ዓመኔታውን እያጣ በመሄድ ላይ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ባለሥልጣናት በዓለምአቀፍ ደረጃ ጭምር መላ ባታሊዮናቸውን ማንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። የግብር ማጭበርበሩንና ማሾለኩን ለመታገል እንድንችል”

በትራንስፓረንሢይ ኢንተርናሺናል ግምት ከጀርመን ብቻ እንኳ ያለ ግብር ባለሃብቶችን ወደሚያስተናግዱት አገሮች የሚፈሰው ገንዘብ በያመቱ 600 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። አገሪቱ በዚሁ ወደ ሃያ ሚሊያርድ የሚደርስ ግብር ያመልጣታል ማለት ነው። በዓለምአቀፍ ደረጃ እንበል ባሃማስን በመሳሰሉት ደሴቶች ተከማችቶ የሚገኘው ገንዘብ ደግሞ በግምት ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ የሚነግዱት የገንዘብ ድርጅቶች በያዙት ሕገ-ወጥ አሠራር ሊቀጥሉ አይገባም። በመሆኑም ቁጥጥሩን ማጠናከሩና ፍቱን ማድረጉ አጣዳፊ ተግባር ነው። የእስካሁኑ ዕርምጃ በቂ አልነበረም።