1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አደገኛ ግርዛት በሶማሌላንድ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2008

በባህል እና በሌሎችም ማህበራዊ ምክንያቶች የሴቶች ልጆች የመዋለጃ አካል ትልተላ ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች አንዱ ሶማሌላንድ ነው ። የሶማሊያ ሪፐብሊክ ግዛት በሆነችው በራስ ገዝዋ በሶማሌላንድ ከ90 በመቶ በላይ ሴቶች ይህ አደገኛ ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል ።

https://p.dw.com/p/1JqPL
Symbolbild Genitalverstümmelung bei Frauen in Afrika
ምስል Getty Images/AFP/N. Sobecki

[No title]

ችግሩ አሁን በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በይፋ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል ። በሶማሌላንድ ይህን ጎጂ ልማድ ለማስቀረት የመብት ተሟጋቾች በቡድንም በግልም እየታገሉ ነው ። ።ድርጊቱ ፈጽሞ እንዲቆምም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥሪአቸውን እያስተላለፉ ነው ።የዶቼቬለው አርንት ፔልትነር ያዘጋጀውን ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
የመስኩ ባለሞያዎች የግርዘቱን ዓይነት ሦስተኛ ደረጃ ይሰጡታል ። ከአነስተኛ እና ከመለስተኛው የሴቶች ግርዛት ቀጥሎ ከሴት ልጅ ብልት አብዛኛው ክፍል የሚቆረጥበት እና ትንሽ ቀዳዳ ብቻ በመተው የሚሰፋበትን አደገኛ የግርዛት ዓይነት ።ይህ ጎጂ ባህላዊ ልማድ ከአምስት እስከ 10 ዓመት እድሜ ውስጥ ባሉ ልጃገረዶች ላይ በሶማሌላንድ በስፋት ይፈፀማል ። የ53 ዓመትዋ ወይዘሮ ሃሊማ ሀሰን ይህ ዓይነቱ የመዋለጃ አካል ትልተላ ከተካሄደባቸው የሶማሌላንድ ሴቶች አንዷ ናቸው ። ዛሬም ድረስ የተገረዙበትን ዕለት ያስታውሳሉ ። ሃሊማ ያኔ አያታቸው እንዴት እንደያዝዋቸው ፣ ህመሙ እና ከዚያ በኋላ ለቀናት መራመድ አለመቻላቸውን አሁንም አይረሱትም ፤ግርዛቱ ያስከተለባቸውን የጤና ችግሮችም እንዲሁ ።
«ወጣት ሳለሁ ነበር የተገረዝኩት ። ራቅ ባለ አካባቢ በሚገኝ መንደር ውስጥ ነበር የምኖረው ። ይህ ጎጂ ልማድ እኔን ብቻ ሳይሆን የኔን ትውልድም ነው የጎዳው ። ትምሕርት ቤት ሲዘጋ ፣ ቤተሰቦቼ የጋበዟት አንዲት አዛውንት ሴት ናቸው የገረዙኝ ።በእሾህ ነበር የሰፉኝ ። እሾሁንም እዚያው ተዉት ። እሾሁ ታፋየን እየወጋ ያሰቃየኝ ። ፍፅም ለግምት አስቸጋሪ የሆነ ህመም ነበር ።»
በልጅነታቸው እንዲህ ዓይነቱ ግርዛት ተፈጽሞባቸው የተሰፉት ወይዘሮ ሃሊማ የሠርጋቸው እለት ስፌቱ መላቀቅ ነበረበት ።ከሠርጉ በኋላ ደግሞ እንደገና ተሰፋ ። ይህ ሁሉ የሚፈፀመው በምላጫ እና በእሾህ ነው ። ዛሬ ወይዘሮ ሃሊማ በርሳቸው የደረሰ በሌሎች እንዳይደርስ ፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ማናቸውንም የብልት ትልተላ በእጅጉ ይቃወማሉ ። ፣ በምህጻሩ ናጋድ ከተባለው ሶማሌላንድ ከሚገኝ የሴቶች መብት ተከራካሪ ድርጅት ጋር ይሰራሉ ።ከሶማሌላንድ ርዕሰ ከተማ ሃርጌሳ የአንድ ሰዓት የመኪና መንገድ በሚርቀው በትንሽትዋ መንደር ጋቢልየ በገራዥነት የሚታወቁት ወይዘሮ ካሚላ ኑራ ይገኛሉ ። ሃሊማ ሀሰን እኚህን የ50 ዓመት ሴት ለማግኘት ወደዚያ ሄደው ነበር ። ሴትየዋ የሚገርዙት በይፋ ነው ። በጁቢቲ የማይፈቀደው ይህ ጎጂ ልማድ በሶማሌላንድ አልተከለከለም ። ወይዘሮ ካሚላ እንደሚሉት የርሳቸው ሥራ እንዲገረዝ የመጣላቸውን ልጅ ወላጆች በሚፈልጉበት መንገድ መግረዝ ነው ።
« የግርዘቱ ዓይነት ይለያያል ። ቤተሰብ ከፈለገ ከሴቶቹ ብልት የሚቆረጥበት ና ከዚያም በእሾህ የሚሰፋበትን የግርዘት ዓይነት እፈጽማለሁ ።ቤተሰብ ከባድ ያልሆነውን አንደኛ ደረጃ የሚሰጠውን ዓይነት ግርዛት ይሁን ካለ ደግሞ ርሱንም አደርጋለሁ ። ለዚህም ይህን ኢህል ገንዘብ ስጡኝ አልልም እነርሱ የአቅማቸውን ያህል ይሰጡኛል ። »
ገራዥዋ ካሚላ ኑራ አልተማሩም ። ሌሎች ሲገርዙ እያዩ ነው መግረዝ የጀመሩት ። የሚገርዙት በምላጭ ሲሆን የሚሰፉት ደግሞ በእሾህ ነው ።ሴቶቹ የሚገረዙትም ከቤተሰብ አባላት በአንዱ ተይዘው ነው ።ካሚላ ለገረዙበት ከ5 እስከ 20 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ያገኛሉ ። ሃሚላ ሃሰን ደግመው ደጋግመው ሴትየዋ በሌላ ሥራ እንዲተዳደሩ ለማድረግ ሞክረዋል ። ሴቶችን ለስቃይ እና ለጤና እክል የሚዳርገውን ይህን ሥራቸውን እንዲያቆሙ ገንዘብ ሳይቀር ሰጥተዋቸው ነበር ። ግን ያሰቡት አልተሳካም ። ካሚላ አዎን ይህ ተደርጎልኛል ፤ግን ባለቤቴ በህይወት ስለሌለ ቤተሰቤን የማስተዳድረው ፣ በመግረዝ ከማገኘው ገንዘብ ነው ይላሉ ። ኤድና አደን ዓለም ዓቀፍ እውቅና የተነፈገችው የሶማሌላንድ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የቀድሞ የሶማሌላንድፕሬዝዳንት ሞሀመድ ኢብራሂም ባለቤት ናቸው ። በሶማሌላንድ የሚካሄድ በሴቶች የመዋለጃ አካልላይ የሚፈፀም ትልተላን ለማስቀረት እየታገሉ ነው ። በዚህ ሥራ ከተሰማሩ 40 ዓመታት አልፏል ።በስማቸው ሆስፒታል ሠርተዋል ። ሆስፒታሉ ውስጥ ወይዘሮ ኤድና አዋላጆችን ያሰለጥናሉ ።አዋላጆች መሬት ላይ እንደሚገኝ ወታደር ነው የሚቆጠሩት ።ከዚህ ሆስፒታል የሚመረቁት እነዚህ አዋላጆች ትምሕርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በመላ ሃገሪቱ እርዳታ የሚሰጡ ሲሆን ህብረተሰቡን ስለ ሴቶች ግርዛት ጉዳትም ያስተምራሉ ። በርሳቸው አስተያየትሴቶች ልጆችን መግረዝ መብታቸውን ይጻረራል ።
«ጤናማ ህጻናት እንዲደሙ ማድረግ ባህልን አይጻረርም ፤ ይልቁንም የህጻኑን መብት እንጂ »
ናጋድን የመሳሰለው ድርጅት እና ኤድና አደን በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት አሁን ችግሩ ይፋ ውይይት እየተካሄደበት ነው ።የሴቶች መብት ተሟጋቾቹ ይህ ጎጂ ልማድ ፈጽሞ እንዲወገድ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ቀጥለዋል ።

Somaliland Genitalverstümmelung Edna Adan Aktivistin
ወይዘሮ ኤድና አደንምስል DW/A. Peltner
Somaliland Genitalverstümmelung Halima Hassan Aktivistin
ወይዘሮ ሃሊማ ሀሰንምስል DW/A. Peltner

አrንት ፔልትነር

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ