1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንትና ተግዳሮቶቻው

ሐሙስ፣ ኅዳር 23 2008

አዲሱ የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ሮህ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬ ከፊታቸው ብዙ ተግዳሮቶች ይጠብቋቸዋል። ከእነዚህ መካከል በቀድሞው መሪ በብሌዝ ኮምፓኦሬ ዘመን የተፈፀሙ ወንጀሎችን መመርመር ይገኙበታል። ይህም ደግሞ የቀድሞው መንግስት ባለሥልጣን የነበሩት ካቦሬ በቀላሉ የሚወጡት ተግባር አይሆንም።

https://p.dw.com/p/1HGu3
Burkina Faso Wahl in Ouagadougou Präsdentschaftskandidat Roch Marc Kabore
ምስል Reuters/J. Penney

ባለፈው እሁድ የተካሄደው የቡርኮና ፋሶ ምርጫ ውጤት የተደባለቀ ስሜት ትቶ ነው ያለፈው። በአንድ በኩል ከ55 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡርኪና ፋሶ ህዝብ ውጤቱ አስቀድሞ ላልታወቅበት ምርጫ በትዕግስት ተሰልፎ ድምጹን ሲሰጥ ማየት እሰየው የሚያሰኝ ነበር። በሌላ በኩል ሮህ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬ በአሁኑ ምርጫ ማሸነፋቸው ብዙ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም። በርግጥም በቀድሞው መሪ በኮምፓኦሬ ዘመን ለዓመታት ያገለገሉት ፖለቲከኛው ካቦሬ እጅግ አስደማሚ ውጤት አግኝተው ለድል መብቃታቸው እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው። የምርጫው ውጤት እዉነት አስቀድሞ የታወቀ አልነበረምን?። በቡርኪናፋሶ የፖለቲካ ሂደት ውስጥስ የቀድሞው መሪ የኮምፓኦሬ ተፅእኖ ምን ያህል ሥር የሰደደ ይሆን? ካቦሬ ከቀድሞው መንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሙሉ ማቋረጣቸውን ከመናገር አይቦዘኑም፤ ይህ በርግጥ እውነት ይሆን? በዚህ መካከል የቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ሚናስ ምን ይሆን? ኮምፓኦሬ፣ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶችዋ መሪዎች ጋር እየተዋዋለች ከለላ ትሰጣቸዋለች የምትባለው የፈረንሳይ ጥቅም አስከባሪ እንደነበሩ ነው የሚነገረው። እነዚህና የመሳሰሉት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከካቦሬ ድል በኋላ እየተነሱ ነው። ለጥያቄዎቹ በሙሉ አሁን መልስ ማግኘት ይከብዳል። አዲሱ ፕሬዝዳንት ግን ሃገሪቱን ለማሳደግ ህዝቡ በአንድ ላይ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
«በሀገሪቱ እርቅ ሰላም ለማውረድ ሃቅንና ፍትህን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት አለብን። መጀመሪያ ይህን ለማድረግ ከበቃን በህብረት ወደፊት መመልከት እንችላለን። መስማማት ካልቻልን፣ ርስ በርስ የምንዋጋ ከሆነ የሀገራችን ልማት እውን አይሆንም።»
ካቦሬ ለረዥም ጊዜ የኮምፓኦሬ አጋር ተደርገው ነበር የሚታዩት። በኮምፓኦሬ ዘመነ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርና በኋላም ለ10 ዓመታት የፓርላማው ፕሬዝዳንት ነበሩ። «የዲሞክራሲና የእድገት ምክር ቤት የተሰኘው» የኮምፓኦሬ ፓርቲ ፕሬዝዳንትም ሆነው አገልግለዋል። ብሌዝ ኮምፓኦሬና ካቦሬ ሆድና ጀርባ የሆኑት ኮምፓኦሬ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ከተነሱ በኋላ ነው። ካምፓኦሬ የስልጣን ዘመናቸውን አራዝማለሁ ማለታቸውን ካቦሬ አልደገፉም። አንዳንዶች እንደሚሉት የኮምፓኦሬን ውሳኔ የካቦሬ ህሊና አልተቀበለውም። ሌሎች እንዳሉት ደግሞ ኮምፓኦሬ ሲወርዱ ካባሬ እንዲተኩ ሁለቱ ተስማምተው ስለነበር ኮምፓኦሬ ያን ትተው እንደገና እወዳደራለሁ ማለታቸው ካባሬን ስላበሳጫቸው ነው ይላሉ። እውነታው ምን እንደሆነ ግን ለማወቅ ያዳግታል። ኮምፓኦሬ ቡርኪናፋሶን ለ27 ዓመታት መርተዋል። ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ነበር በህዝባዊ አመፅ ከሥልጣን የተወገዱት። አልተሳካላቸውም እንጂ በወቅቱ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በማሻሻል የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ፈልገው ነበር። አዲሱ ፕሬዝዳንት ካቦሬ ያለፈውን ትተው በወደፊቱ ላይ ለማተኮር ነው የሚፈልጉት። ከቡርኪናፋሶ ህዝብ ሁለት ሶስተኛው እድሜው ከ18 ዓመት በታች ነው። በርካታ ወጣቶች ሥራ አጥ ናቸው። ወጣት ሥራ አጥነት ከሀገሪቱ ፈታኝ ችግሮች አንዱ ነው። ህዙቡ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ከሚጠብቃቸው ተግባራት ውስጥ ይህን ችግር ማቃለል ይገኝበታል።
«አዲሱ ፕሬዝዳንት ለወጣቱ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፣ ትምህርት ቤቶችንና መንገዶችን ቀናና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይገነባሉ ብለን እንጠብቃለን። ሆኖም ነገሮችን በትክክለኛ መንገድ ካልካሄዱና እንደ ቀድሞው መሪ የሚያስተዳድሩ ከሆነ እንደገና ተመልሰን ወደ ጎዳና መውጣታችን አይቀርም።»
እኚህ የቡርኪናፋሶ ዜጋ እንዳሉት ሁሉ የመብት ተሟጋቾችም ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ ቃል የገቡትን ተግባራዊ ካላደረጉ እንደ ኮምፓኦሬ ከስልጣን መወገዳቸው እንደማይቀር እያስጠነቀቁ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2014 እና 2015 ከተካሄዱት ህዝባዊ አመፅ እና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ እርቀ-ሰላም ማውረድና ፍትህን ማስፈን ካቦሬ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በፓርላማ ፕሬዝዳንትነት እና በፓርቲ መሪነት የሠሩት ካቦሬ ይህ ተግባራዊ እንዳይሆን መሰናክል ሊሆኑ ምርምራዎችንም ሊያደናቅፉ የመቻላቻቸው ስጋት አለ።

Burkina Faso Präsidentschaftswahl - Gewinner Roch Kaboré
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo
Burkina Faso Präsidentschaftswahl - Gewinner Roch Kaboré
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Renaut

ዲርከ ከፐ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ