1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ማጉፉሊ

ዓርብ፣ ጥቅምት 19 2008

ታንዛኒያ ከትናንት ጀምሮ አዲሱን ፕሬዝደንቷን አዉቃለች። ሀገሪቱን ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ የመራዉ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በገጠመዉ የተሟሟቀ ፉክክር ተጣምረዉ የተፎካከሩትን የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ማሸነፉ ተሳክቶለታል።

https://p.dw.com/p/1GxMJ
Tansania Präsidentschaftswahlen Kandidatur John Pombe Magufuli mit Amtsinhaber Jakaya Kikwete
ምስል picture-alliance/AP Photo/K. Said

[No title]

አዲሱ ፕሬዝደንት ጆን ፖምቤ ማጉፉኒ ከምርጫ ኮሚሽኑ የዘንድሮዉን ፕሬዝደንታዊ ፉክክር ማሸነፋቸዉን የሚገልፅ የምስርክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ማጉፉኒ በምን ይታወቃሉ ?

የ55ዓመቱ ዶ/ር ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ በታንዛኒያ ፖለቲካ እንግዳ አይደሉም። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1977ዓ,ም አንስቶ የአብዮታዊዉ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ CCM አባል ናቸዉ። የኬሚስትሪ መምህሩ በ1995 ለመጀመሪያ ጊዜ ለምክር ቤት አባልነት ተመርጠዉ፤ የግንባታ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትርነት ስልጣን ያዙ። ከአምስት ዓመት በኋላ የግንባታ ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ተሹመዉ ለአምስት ዓመታት ያህል ከሠሩ በኋላ የመሬት፤ የቤቶች ግንባታ እና የከተማ ልማት ሚኒስትር ሆኑ። ከዚያም ለሁለት ዓመታት በእንስሳና ዓሣ ሚኒስትርነት እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም ምርጫ ድረስ የቆዩት ማጉፉሊ ወደግንባታ ሚኒስትርነት ተመልሰዉ በዘንድሮዉ ምርጫ ወፕሬዝደንትነቱ ስልጣን እስኪወጡ ታንዛኒያን አገልግለዋል። ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ ባደረጉት ንግግርም ለታንዛኒያ ፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ጉዳይ እንግዳ እንዳልሆኑ እንዲህ ነበር የገለፁት፤

Tansania Flagge
ምስል Imago

«ለፕሬዝደንታዊ እጩነት እንድቀርብ የጠየኩት ለሙከራ ብቻ አይደለም። የምወዳደረዉ ለታንዛኒያ መሥራትና ታንዛኒያዉያንን ለማገልገል ስለምፈልግ ነዉ። የዚህችን ሀገር ታሪክ አዉቃለሁ፤ ከየት እንደመጣን፤ አሁን የት እንዳለን፤ እንዲሁም ወደየት እያመራን እንደሆነም አዉቃለሁ።»

በደጋፊዎቻቸዉም ሆነ በተቃዋሚዎቻቸዉ ማጉፉሊ በኪስዋሂሊ «ጄምቤ» ማለትም የሥራ ፈረስ በመባል ይታወቃሉ። «ቡልዶዘር» የሚለዉ ቅፅልም በሕዝብ ዘንድ መታወቃያቸዉ ነዉ። ሥራዎች በጥንቃቄ ካልተሠሩ አይረኩም፤ የጀመሩት ሥራ ከዳር ሳይደርስም አይደክሙም ይሏቸዋል። በጃፓን መንግሥት ድጋፍ ሊከናወን የነበረ የአዲስ መንገድ ግንባታ የጥራት ደረጃዉን አያሟላም ብለዉ አግደዋል። የአካባቢዉን የጥራት ደረጃ አልጠበቁም ያሏቸዉን የመንግሥት ሕንፃዎችም ማፈራረሳቸዉ ይነገራል። በእሳቸዉ አመራር የተከናወነ አንድ የመንገድ ሥራ ተጠናቆ ሲመረቅም ከተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር ዉዳሴን አላጡም። የተቃዋሚዉ ቻዴማ ፓርቲ መሪ ፍሪማን ምቦዌ የየትኛዉም ፓርቲ አባል ይሁን ዋናዉ ለታንዛኒያ የሚረባ ሥራ ከሠራ ይወደሳል ይላሉ ፤

Tansania Wahlen Karikatur von Said Michael
ምስል Said Michael

«በእኔ አመለካከት ልማት የየትኛዉንም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አይከተልም። ከየትኛዉም ፓርቲ ለታንዛኒያ አዎንታዊ ልማት ከመጣ የእኛን እዉቅና እና አድናቆት ያገኛል።»

በሌላ በኩል አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች ማጉፉሊ ዘመነ ስልጣናቸዉን የራሳቸዉን ሃሳብ ሰዎች ላይ በመጫን ሊፈጁት ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸዉ። ደጋፊዎቻቸዉ ደግሞ የለም ሰዉየዉ ከቃላት በላይ ሙስናን ከሥሩ የሚነቅሉ፤ የደነዘዘዉን ኤኮኖሚ የሚያነቃቁ፤ ሠርተዉ ማሳየት የሚችሉ ናቸዉ ሲሉ ይከራከራሉ። ራሳቸዉ ማጉፉሊም በምርጫ ቅስቀሳቸዉ ወቅት ወደዝቅተኛዉ የኅብረተሰብ ክፍል አኗኗር እንደሚመለከቱና፤ ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት የሚከፋፈልበትን፤ የእርሻዉ ዘርፍ የሚስፋፋበትን፤ የአነስተኛ ነጋዴዎች ችግር የሚፈታበትን፤ ከዚህም አልፈዉ የሰነፍ ባለስልጣናትን ቢሮ የሚያጸዱበትን መንገድ እንደሚፈጥሩ ቃል ገብተዋል። በተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም ከድህነት ባልወጣችዉ ታንዛኒያ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ጉዳያቸዉን ለማስፈጸም ጉቦ መስጠታቸዉ የአደባባይ ምሥጢር ነዉ። የሕዝቡን ችግር ከሥር መሠረቱ እንደሚያዉቁ የሚናገሩት አዲሱ ፕሬዝደንት ማጉፉሊ፤ እሳቸዉ እንደመሲህ ከዚህ ሁሉ ሊታደጉት እንደመጡም ደጋግመዉ ተናግረዋል።

Tansania Wahlen John Magufuli
ምስል Reuters

«እዉነቱን ለመናገር ሥራ ፈጥረዉ፤ ለመንግሥት ግብር በመክፈት፤ እና በአካባቢዉ ለሚገኙ ኗሪዎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ እስከሆነ ድረስ ባለወረቶች በርከት ብለዉ እንዲመጡልን እልሻለን፤ በዚያም ላይ ከማዕድን ቁፋሮዉ ለመንግሥት ገቢ ማስገኘት ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተሰጡን ሀብቶች ናቸዉ።»

ማጉፉሊ በጠንካራ ሠራተኝነታቸዉ የመታወቃቸዉን ያህል እሳቸዉ ብዙዎች በችኮላ አሳለፏቸዉ በሚሏቸዉ አንዳንድ ዉሳኔዎችም መንግሥታቸዉ ዋጋ እንዳስከፈለ ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ ትላልቅ የዉጭ ሀገር ዓሣ አስጋሪ ጀልባዎች በሕገወጥ ዓሣ ማስገር ተግባር ላይ ተይዘዋል በሚል ባቀረቡት ክስ፤ ፍርድ ቤት ሕጋዊ መሆናቸዉን ወስኖ የታንዛኒያ መንግሥት 2,8 ቢሊየን የታንዛኒያ ሽልንግ ለባለቤቶቹ እንዲከፍል አብቅተዋል። ማጉፉኒ ሀገራቸዉ እና ከዉጭ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። በሙያቸዉም በርካታ መጽሐፍትን እና የመጽሔት መጣጥፎችንም ጽፈዋል።

ሴሳንጋ ኢዲ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ