1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ፓስፖርት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 13 2008

ኪጋሊ ሩዋንዳ ውስጥ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተጠናቀቀው በ27 ተኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ አፍሪቃውያን በክፍለ ዓለሙ ያለቪዛ መዘዋወር የሚያስችላቸው ፓስፖርት ይፋ ተደርጓል ። ዓላማው በክፍለዓለሙ የዜጎችን እንቅስቃሴ ማቃለል እና እና የርስ በርስ የንግድ ግንኙነትን ማበረታታት መሆኑ ተገልጿል ።

https://p.dw.com/p/1JSli
Ruanda Idriss Deby und Paul Kagame stellen neuen Reisepass vor
ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/P. Siwei

[No title]

በአፍሪቃ የጋራ ፓስፖርት ይፋ የተደረገው የክፍለ ዓለሙ ዜጎች ያለ ቪዛ በነፃ መዘዋወር እንዲችሉ ሃሳብ በቀረበ በ25 ዓመቱ ነው ። በአፍሪቃ ህብረት ባለሥልጣናት እምነት ፓስፖርቱ ሥራ ላይ መዋል ሲጀምር አፍሪቃ የህዝቦቿን ልዩ ስጦታ ክህሎት እና የሠራተኛ ኃይል ያለ ዝውውር ገደብ መጠቀም የምትችልበት እድል ይፈጠራል ። ስለ ፓስፖርቱ አጠቃቀምም ሆነ አሰጣጥ በአሁን ደረጃ በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የለም ። ፓስፖርቱ ግን ሁለት ዓይነት ሲሆን አንደኛው ለአፍሪቃ ህብረት ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች እንዲሁም በንግድ ምክንያት አዘውትረው ወደ ተለያዩ ሃገራት ለሚጓዙ ሰዎች የሚሰጥ ፣ሁለተኛው ደግሞ እያንዳንዱ አባል ሃገር ለማናቸውም ዜጎቹ የሚሰጠው መሆኑ ተገልጿል። በአሁኑ ጊዜ ከ55 ቱ የአፍሪቃ ሃገራት 13ቱ ብቻ ናቸው አፍሪቃውያንን ያለቪዛ የሚያስገቡ ፣ወይም ወደ ተጓዙበት አገር ሲደርሱ ቪዛ የሚሰጡ ። ይህም በአፍሪቃውያን መካከል ለሚካሄደው የርስ በርስ ንግድ ደንቃራ ሆኗል ። አዲሱ ፓስፖርት ይህን መሠረታዊ ችግር ያቃልላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ። አቶ አበበ አይንቴ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ እንደሚሉት የፓስፖርቱ ሥራ ላይ መዋል ከንግዱ በተጨማሪ አፍሪቃውያን በሌሎችም ዘርፎች ይበልጥ እንዲቀራረቡ እድል ይፈጥራል ።ፓስፖርቱ በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ይፋ ሲደረግ ተሰናባቿ የአፍሪቃ ህብረት ፕሬዝዳንት ንኮሳዛና ድላማኒ ዙማ እርምጃውን አወድሰዋል ፤በዜጎቿ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የበለፀገች እና ርስ በርስ የተገናኘት አፍሪቃን ወደ መፍጠር ግብ የሚወስድ እና ክፍለ ዓለሙም በዓለም የሚገባውን ቦታ እንዲይዝ የሚያደርግ ሲሉ ። ይሁንና የአፍሪቃ አገሮች በርካታ የውስጥ ችግሮቻቸውን ሳይፈቱ ወደ ጋራ ፓስፖርት አጠቃቀም መሸጋገራቸው ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው ። ፓስፖርቱ የሚሰጥበት መንገድ እና ሥራ ላይ ከዋለ በኋላም ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የሚፈራው መዘዝ እያነጋገረ ነው ። ስለ ፓስፖርቱ አስተያየታቸውን የሰጡ አፍሪቃውያን እርምጃው ስደትን ሊያበረታታ ፣ የጸጥታ ችግሮችን ሊያባብስ እንዲሁም ሌሎችም የተዘበራረቁ ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሏቸው ። አቶ አበበ አይንቴ ደግሞ እነዚህን ስጋቶች ለመከላከል ሃገሮች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ወሳኝ ናቸው ይላሉ ።የወቅቱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀ መንበር የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖና እና የ27 ተኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አስተናጋጅ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ፓስፖርቱ ከአፍሪቃ ህብረት የተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ መሪዎች ናቸው ። እነርሱ የወሰዱት ፓስፖርት ለአፍሪቃ ህብረት ባለሥልጣናት እና ለመንግሥታት መሪዎች የሚሰጥ ፓስፖርት ነው ።ከጊዜ በኋላም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ይሰጣል ተብሏል ። ለዲፕሎማቶች ይሰጣል የተባለው ፓስፖርት በእንግሊዘኛ በፈረንሳይኛ በአረብኛ በፖርቱጋልኛ እና በስዋህሊ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው። በመላው አፍሪቃ ያለቪዛ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ይህንኑ ፓስፖርት እስክ ጎርጎሮሳዊው 2020 ለተራው አፍሪቃዊ የመስጠት እቅድ ተይዟል ።

Ruanda AU-Gipfel in Kigali
ምስል Getty Images/AFP/C. Ndegeya
Ruanda AU-Gipfel in Kigali
ምስል Getty Images/AFP/C. Ndegeya

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ