1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስትራቴጂው ከቀድሞዎቹ ዕቅዶች የተለየ አልያዘም በሚል ተተችቷል

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2009

ባለፈው ግንቦት የኢትዮጵያ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ያረቀቀዉ “የወጣቶች የልማትና የዕድገት ስትራቴጂ” በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተዘግቧል፡፡ የስትራቴጂው አንድ አካል ነው የተባለለት የ10 ቢሊዩን ብር ተንቀሳቃሽ ገንዘብ አተገባበር ደግሞ ከሳምንት በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለውይይት ሊቀርብ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

https://p.dw.com/p/2Uops
Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

አዲሱ የኢትዮጵያ የወጣቶች ስትራቴጂ ምን ይዟል?

የኢትዮጵያ መንግስት የወጣቶች ነገር ክፉኛ ያሳሰበው ይመስላል፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የወጣቶችን ነገር ከአፋቸው አልነጥልም ብለዋል፡፡ ክልሎች ዘንድም ተመሳሳይ ነገር ይስተዋላል፡፡ ከካቢኔ ምስረታ እስከ ምክር ቤት ስብሰባቸው የወጣቶችን ጉዳይ አትኩሮት ሰጥተው እየተከታተሉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ እንደማዋዣ ደግሞ የወጣቶችን የስራ ችግር ለመቅረፍ ከቢሊዮኖች እስከ ሚሊዮኖች ብር በጀት በፌደራልም በክልሎችም መመደባቸውን አሳውቀዋል፡፡ አነጋጋሪው ነገር ቢሊዮኖች ብር የሚፈስስበት የዚህ ዕቅድ ዝርዝር ገና ያልጠራ መሆኑ እና እናት ስትራቴጂውም ገና ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ያልጸደቀ መሆኑ ነው፡፡  

ለፈንዱ መቋቋም መነሻ ነው የተባለለት የ“ኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና የዕድገት ስትራቴጂ” በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው በግንቦት 2008 ዓ.ም ነው፡፡ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይህ ዕቅድ 36 ገጾች ያሉት ሲሆን ስድስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል “የኢትዮጵያ ወጣቶች ነባራዊ ሁኔታ” የሚዳስስ ሲሆን ሁለተኛው የስትራቴጂውን ዓላማ፣ መርሆዎች እና እሴቶች ይዘረዝራል፡፡

የስትራቴጂው ዋና ዋና ጉዳዮች የሚተነተኑበት ሶስተኛው ክፍል ወጣቶች በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ ያተኩራል፡፡ ልዩ ትኩረት የሚሹ ወጣቶች እና የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወጣቶች ጉዳይም ለብቻው ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግስት ከ10 ዓመት በፊት “የወጣቶች የዕድገት ፓኬጅ የተሰኘ ማዕቀፍ” አውጥቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ቢቆይም “የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚል” ዕቅዱን መከለስ እንዳስፈለገው በስትራቴጂው ላይ ተጠቁሟል፡   ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ሂደት ወጣቶች በተደራጀ አኳኋን የመሪነት ሚናቸውን ለማስቻል ወቅቱን የጠበቀ ወጣት ተኮር መረጃዎችን በማካተት ስትራቴጂው መዘጋጀቱንም ያትታል፡፡

Äthiopien Mulatu Teshome ist neuer Präsident
ምስል Elias Asmare/AFP/Getty Images

ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበረው ፓኬጅ የወጣቶችን “ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በሚጠበቀው መጠን” አለመመለሱንም አልካደም፡፡ ይህንን አመለካከት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ መድረኮች ሲያስተጋቡት ቆይተዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ያሰሙት ንግግር ለዚህ እንደ አብነት የሚወሰድ ነው፡፡

“መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሶስተኛ አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚህ ላይ በመመሰረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ታይቷል፡፡”

“ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአፈጸም ብቃት መጓደል እና በስነ ምግባር ጉድለቶች ምክንያት ሲደነቃቀፉ  የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች ራሱን የወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን ህዝባዊ አመጽ ከወጣቶች ቅሬታ ጋር አዛምደውታል፡፡ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድ የሚከታተሉ ባለሙያዎችም መንግስት “አዲስ የወጣቶች ስትራቴጂ ይዤ መጥቻለሁ” ያለበት ምክንያት የወጣቶችን ጥያቄ እና ፍላጎት ከስር መሰረቱ ለመፍታት በመሳብ ሳይሆን የአመጹን ግለት ለማብረድ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ወደም ሲል ቀደም ባሉ የፖለቲካ ቀውሶች ጊዜ የታየ እንደሆነ ምሳሌ ያጣቅሳሉ፡፡ በኒው ዮርክ አዮና ኮሌጅ የሶሺዮሎጂ መምህር የሆኑት ዶክተር ደረሰ ጌታቸው ስትራቴጂው ከዚህ ቀደም ከነበረው እምብዛም የተለየ ነገር እንደሌለው እና ከምርጫ 97 በኋላ እንደታየው ሁሉ ለተቃውሞ ማብረጃነት የዋሉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

“የወጣቶች የልማት ስትራቴጂ የተባለው ውስጥ አዲስ ነገር በብዛት አላገኘሁም፡፡ በ1998 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጣው የ‘ኢትዮጵያ የወጣቶች ብሔራዊ ፖሊሲ’ ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡ ከምርጫ 97 በፊት ኢህአዴግ የወጣቶችን ጉዳይ አተኩሮ የሚመለከተው አልነበረም፡፡ ሀገሪቱ የወጣቶች ፖሊሲም አልነበራትም ፡፡ ወደ ከተማ እና ወደ ወጣት የማተኮር ነገር ከምርጫ 97 ጀምሮ የመጣ ነገር ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ ባሉ ወጣቶች በመንግስት ላይ የደረሰው ተቃውሞ ‘ገጠር እና ገበሬ ላይ ብቻ ነው’ የማተኩረው የሚለው መንግስት ድንገት እንዲባንን አድርጎታል፡፡”

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherin
ምስል Jeroen van Loon

“ከምርጫው በኋላ ነው እንግዲህ የመጀመሪያው የወጣቶች ብሔራዊ ፖሊሲ ተብሎ የተቋቋመው፡፡ ወጣቶችን አነስተኛ እና በጥቃቅን ኢንዱስትሪ ማደራጀት የተጀመረው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፡፡ እኔ ይሄኛውን አዲሱን ወጣቶችን በተመለከተ ተነደፈ የተባለውን ስትራቴጂ የማየው በዚህ ዓመት ውስጥ ለተደረጉ ሁለት የፖለቲካ ንቅናቄዎች በተለይ ለኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ እና በአማራ ክልል ለተነሳው ተቃውሞ የሚደረግ ምላሽ አድርጌ ነው ያየሁት” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ፡፡  

ለስትራቴጂው መረቀቅ ምክንያቱ ምን ይሁን ምን ዋናው ጉዳይ ሰነዱ የኢትዮጵያውያን ወጣቶችን መሰረታዊ ፍላጎት እና ጥያቄ “በትክክል ተገንዝቦ ለእርሱ የሚመጥን መፍትሄ አስቀምጦለታል ወይ?” የሚለው ነው፡፡ እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ደረሰ ምልከታ በሰነዱ ላይ ሁለት ችግሮች ጎላ ብለው ተጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው በወጣቶች ዘንድ ተንሰራፍቷል የተባለው ስራ አጥነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይህን ተከትሎ በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ያለ ተቃውሞ እና ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡

መምህሩ ስራ አጥነት በእርግጥም በሀገሪቱ ትልቅ ችግር እንደሆነ ይቀበላሉ፡፡ ለዚህም አሃዞችን በማሳየነት ያቀርባሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት በዚህ ወር ያወጣው የዓለም የህዝብ ብዛት ዘገባ የኢትዮጵያ ህዝብ 102 ሚሊዮን ገደማ መድረሱን እና ከዚህ ውስጥ 41 በመቶው ከ15 ዓመት በታች ያለ መሆኑን መተንበዩን ይጠቅሳሉ፡፡ ሀገሪቱ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያልጨርሱ ወደፊት ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከተቀላቀሉና ከተመረቁ በኋላ ስራ የሚጠብቁ እልፍ ወጣቶች እንዳሏት ማሳያ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡   

“በመንግስት በራሱ ትንበያ ወደ 20 በመቶ የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ወጣት ከ15 እስከ 29 [ዕድሜ] ያለው ነው ይላል፡፡ በከተማ አካባቢ የስራ አጥነት ቁጥሩ ወደ 17 በመቶ ነው ይላል፡፡ ‘ወጣቱ የኢኮኖሚ ችግር እንዳለበት፣ ድህነት የተንሰራፋ እንደሆነ’ ይሄ ትክክለኛ ግምገማ ይመስለኛል፡፡ ችግሩና ሁልጊዜ የማይጠቀሰው አንደኛ ‘ድህነት እና የወጣቱ ስራ አጥነት እንዲህ የተስፋፋው ለምንድ ነው?’ [የሚለው ነው]፡፡ እርሱ ራሱ የኢህአዴግ የፖለቲካ ውድቀት አይደለም ወይ? የአገዛዝ ውድቀት አይደለም ወይ? የሚለውን መንግስት አያነሳም፡፡” 

“ሁለተኛ ለዚህ ስራ አጥነት መፍትሄ የሚሆነው ነገር በኢህአዴግ ጡት አጥቢነት ወይም ሞግዚትነት የሚደረግ የወጣቶች መደራጀት  ነው ወይ? ለሚለውም መፍትሄ አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ችግሩ እንዴት መጣ የሚለው ላይ ግልጽ እና ተአማኒ ትንተና አይደርግም፡፡ ይሄ ፖሊሲ ችግሩን ለመፍታት ከራሱ ሞግዚትነት በስተቀር ሌላ የማህብረሰብ አካል ወይም ሌላ ተቃዋሚ ወይም ወጣቶች ራሳቸው አቅም አላቸው ብሎ አያምንም” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይተቻሉ፡፡     

ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከግማሽ የማያንሰው በወጣት የእድሜ ክልል እንደሚገኝ በመስከረም ወር ንግግራቸው ያስታወሱት ፕሬዝዳንት ሙላቱም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ተወደደም ተጠላም ወጣት ተኮር መሆኑ የግድ መሆኑ እንደማይቀር ተናግረው ነበር፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ በገጠር የሚገኝ እንደመሆኑ ወጣቱም በዋነኛነት ተከማችቶ የቆየውና ዛሬም የሚገኘው በዚሁ አካባቢ እንደሆነ ገልጸው ሆኖም ይህ መለወጥ መጀመሩን አመልከተዋል፡፡

እንደ ፕሬዝዳንቱ አባባል አብዛኛው የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የለውም፡፡ የገጠሩ ወጣት በኢትዮጵያ ተሰፍፍቷል ባሉት የትምህርት እድል ተጠቃሚ በመሆኑ የወላጆቹን ልማዳዊ የግብርና ስራ ሊቀጥልበት የማይፈልግ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶችም የገጠሩ ወጣት ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች በተለይ ደግሞ ወደገጠር ከተሞች እየጐረፈ መከማቸት መጀመሩንም ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

“ይህ ወጣት ገጠሩን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የለቀቀ ቢሆንም፣ በከተሞቻችን አስተማማኝ የስራና የገቢ ሁኔታ ግን ገና እየተፈጠረለት ነው፡፡ በተከማቸባቸው ከተሞች ሁሉ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው በመሆኑ ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ ነው፡፡ ሁኔታዎች ዘንበል ያሉ ቀን ለከፋ አደጋ እጋለጣለሁ ብሎ በሰቀቀን እና እርግጠኛነት በማጣት ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ ይህን የመሰለው ወጣት በትንንሽ የገጠር ከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ በትልልቅ ከተሞችም ጭምር የሚገኝ በመሆኑ መንግስት ከመቸውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር በተደጋጋሚ መጋለጧ እንደማይቀር መገንዘብ ይገባል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግራቸውን አሰምተው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በህዝብ ከናይጄሪያ ለጥቃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም ከተሜ ቀመስ በሆነ ህዝቧ ግን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳለች ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በሶስት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብር የተሰራ እና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች የሚዳስስ የዚህ ዓመት ጥናት እንደሚያመለክተው በከተማ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከጎርጎሳውያኑ 2005 ጀምሮ በ3.8 በመቶ ብቻ ሲያድግ ቆይቷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት 15 ሚሊዮን የነበረው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪ በ2037 በሶስት እጥፍ ጨምሮ 42 ሚሊዮን ገደማ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ መንግስት ላይ ከፍተኛ የልማት ተግዳሮት እንደሚደቅን የጥናቱ አዘጋጆች ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሙላቱ የጠቆሙት የስራ አጥነት ችግርም አለ፡፡

እንደስራ አጥነት የመሳሳሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሌም መንግስት የሚከተለው አንድ አይነት አካሄድ እንደሆነ ዶክተር ደረሰ ይተቻሉ፡፡ የሶሾዮሎጂ መምህሩ በወጣቶች ስትራቴጂውም ሆነ በሌሎች የሚታየው የመንግስት ድክመት “ለሁሉም ችግር መፍትሄው መንግስት ነው”ብሎ ማመኑ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

“በትምህርት እንዲህ አደርጋለሁ፡፡ በጤና፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲህ አሳትፋችዋለሁ፡፡ እዚህ ድርጅት ውስጥ እጨምራችኋላሁ፡፡ የወጣት ቡድን አቋቁማለሁ፡፡ እና መንግስት ሁልጊዜ ለተነሳ ችግር በሙሉ ቀሚስ ቀዶ ሰፍቶ እዚያ ውስጥ ህዝብ ለማስገባት ነው የሚሞክረው ፡፡ ወጣቶች ማንም ሳያደራጃቸው እኮ መብታቸው ከተጠቀሙ፣ ተምረው ስራ ሚያገኙበት ፍትሃዊ የሆነ ገበያ ከተሰራላቸው ራሳቸው ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ሰነዱን ስታነበው ወጣቶች በምንም ዓይነት የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑ አይመስልህም፡፡ ዝም ብለህ መደርደሪያ ላይ እንደሚቀመት መጽሐፍ ከፍ እና ዝቅ እያደረግህ የምታስቀምጣቸው፣ ስትፈልግ የምታስተምራቸው፣ ስትፈልግ ብድር የምትሰጣቸው እንደው ቁስ ነው የሚመስሉትና ያሳዝናል” ይላሉ፡፡  

ዶክተር ደረሰ ስትራቴጂውን ሲያነቡ እንዳዘኑበት ሁሉ ያስገረማቸው እና ያሳቃቸውም አለ፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ስትራቴጂውን ሲያዘጋጅ ዋቢ አድርጎ ካጠናቸው ሀገራት መካከል ደቡብ ሱዳን ተጠቅሳ ማግኘታቸው አስደንቋቸዋል፡፡ “አሁን የደቡብ ሱዳን የወጣት ፖሊሲ ምን ሰናይ ነገር አበርክቶ ለኢትዮጵያ ምሳሌ ሆኖ ይቀርባል?” ሲሉ በፈገግታ ታጅበው ይጠይቃሉ፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ