1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና በሥነ-ቴክኒክ፧ ባህርዬ-ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእት፧

ሐሙስ፣ ሰኔ 17 1996

በቡርኪና ፋሶ መዲና በዋጋዱጉ፧ የዩ ኤስ አሜሪካ ድርጅቶች ያዘጋጁት፧ በሥነ- ቴክኒክ፧ የተፈጥሮ ባህርዬ ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእትን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ዓላማ ነክ ጉባዔ፧ ትናንት፧ ተደምድሟል። ከ ፲፭ የአፍሪቃ አገሮች የተውጣጡ ሚንስ ትሮች፧ በጉባዔው የተሳተፉ ሲሆን፧ አሜሪካውያኑ፧ ባህርዬ ውርሳቸው የተለወጠ በቆሎ፧ ስንዴና ጥጥ፧ ለአፍሪቃ በረከት ናቸው ይላሉ።

https://p.dw.com/p/E0fY

አሜሪካውያን፧ ሌላው ወገን በፍጹም አልፈልገውም ቢልም፧ ለዓለም የሚበጅ ነው በማለት፧ የሚሲዮናዊነት ተልእኮ በመሰለ መልኩ ተቀባይነት እንዲያገኝላቸው ይጥራሉ። እንደነርሱ አባባል፧ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም፧ ባህርዬ-ውርሳቸው በተለወጠ አዝርእት ቢጠቀም፧ ምርቱን በ ፬ እጥፍ ማሳደግና ረሃብን ድል ማድረግ ይችላል። ይኸው፧ ዋግ እንደማይመታው የሚነገርለት የእህል ዘር፧ የሚገዛው፧ ባህርዬ-ውርሳቸው የተለወጠ እዝርእት ልዩ የባለቤትነት ፈቃድ ካለው ሞንሳንቶ ከተሰኘው የዩ ኤስ አሜሪካ ኩባንያ ነው። የተጠቀሰውን ዓይነት የእህል ዘር የአፍሪቃ አገሮች ሁሉ የሚጓጉለት አይደለም። ከጥጥ ዓይነት፧ የተፈጥሮ ባህርዩ በሥነ ቴክኒክ እንዲለወጥ የተደረገው በአህጽሮት BT (ቱዑሪንጊያ-ባሲለስ) የተሰኘው፧ የአፍሪቃን ችግር ይቀርፋል ነው የሚባለው። ባህርዬ-ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእት፧ ጠቀሜታ አላቸው በማለት፧ የዩ ኤስ አሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደ. ቡሽም እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ ያሰሙት።
O-tone(We see the benefits of bio-tech every day.........)
«ሥነ- ህይወት፧ በሥነ-ቴክኒክ ለውጥ የታየበትን ውጤት በየእለቱ፧ በምግብ ዋጋ፧ መሬት እንክብካቤ በሚደርግለት አሠራርም ሆነ ልምድ የምናየው ነው። ስለሆነም፧ ዐቢይ ጠቀሜታ የሚያስገኘው ቴክኖሎጂ፧ ይበልጥ እጅግ ተፈላጊ ወደ ሆነባቸው አፍሪቃና ሌሎችም አህጉር መዳረስ ይኖርበታል።
ብዙዎች የአውሮፓ መንግሥታት፧ ባህርዬ ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእት እንዳይገባ ገበያ ዘግተዋል፧ ይኸው የአውሮፓውያኑ እርምጃም፧ የአፍሪቃ አገሮች በሥነ-ህይወትና ሥነ ቴክኒክ አጠቃቀም ላይ እንዳያተኩሩ፧ እንቅፋት ሆኗል። በዓለም ዙሪያ፧ ረሃብን ድል ለማድረግ፧ ጠቃሚ የሆነው፧ ባህርዬ ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእትን የማዛመቱን እርምጃ መደገፍ ይኖርብናል« ብለዋል።
የአሜሪካው የግብርና ኩባንያ፧ ሞንሳንቶ፧ በተጠቀሰው ቴክኖሎጂ ላይ በማትኮር አፍሪቃ ውስጥ እግር ለመትከል የቻለ ብቸኛው ድርጅት ነው። ኩባንያው ቡርኪና ፋሶ ውስጥ፧ የተፈጥሮ ባህርዩ የተለወጠውን ጥጥ በመትከል ላይ የሚገኝ ሲሆን፧ የቡርኪና ፋሶ የግብርና ሚንስትር ሳሊፍ ዲያሎ፧ አገራቸው በዚህ ዘዴ ፬ እጥፍ ማምረት ትችላለች በማለት የአሜሪካውያኑን ግፊት ጠቃሚ አድርገው ተቀብለውታል። በአጎራባች ሀገር ቤኒን ደግሞ የመንግሥት አመለካከት ፍጹም የተለየ ነው። የግብርና ሚንስትሩ Didier Hubert Madafime በበኩላቸው፧
O-ton(”Die großen Firmen wie Monsanto.............)
«ሞንሳንቶንና ኮኝንታን የመሳሰሉ፧ ክፍለ-ዓለማችንን ለማጥለቅለቅ የተነሳሱ፧ አንዳንዴ
የቤተ-ሙከራ ጭራቆች የምላቸው ናቸው። በተለይ፧ ሩዝንና በቆሎን በተመለከተ፧ ከአደገኛ ነጻ የሚየደርገው አስተማማኝ ምርምር አልተካሄደም። በመሆኑም የቤኒን መንግሥት፧ ከ ፭ ዓመት በፊት፧ በተጠቀሰው የአዝርእትን ምርት ከፍ ለማድረግ ይበጃል በሚባልለት የምርምር ዓይነት ላለማትኮር ወስኗል« ብለዋል።
የቤኒን መንግሥት፧ ባህርዬ-ውርሳቸው የተለወጠ አዝርእት፧ በጤንነት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት ጠንቅ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ገበሬዎች፧ የሌሎች ጥገኞች የመሆናቸው አደጋም አለበት ነው የሚለው። ሞንሳንቶ፧ በአፍሪቃ እንዳሰበው አልተሳካለትም።አሜሪካውያኑ፧ ለዚህ ሁሉ ዋና እንቅፋት፧ የተፈጥሮ ባህርያቸው የተለወጠ ጥጥ፧ ጥራጥሬም ሆነ ፍራፍሬ፧ እንዳይገባ በማከላከላቸው ነው። ከደቡብ አፍሪቃ በስተቀር፧ ሌሎቹ የአፍሪቃ መንግሥታት፧ ለምርምሩ እንኳ በሩን ጥርቅም አድርገው መዝጋታቸውን ነው አሜሪካውያኑ በቅሬታ የሚናገሩት። እዚህ ላይ በተለይ፧ ዛምቢያ፧ ባለፈው ዓመት፧ እርዳታ ቢሆንም እንኳ፧ የተፈጥሮ ባህርዩ የተለወጠ በቆሎም ሆነ ስንዴ ፍጹም አልቀበልም በማለት፧ ከዩ አኤስ አሜሪካ ጋር እንካ ስላንትያ ገጥማ እንደነበረ አይዘነጋም።