1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና ወጣቱ ሥራ አጥ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2005

አፍሪቃ ዛሬ የበለጸገው ዓለም በፊናንስና የኤኮኖሚ ችግር ተወጥሮ ባለበት ሰዓት በርከት ባሉ ምዕራባውያን የምጣኔ-ሐብት ጠበብት መጨዋ፤ በመንቃት፤ በመነሣት ላይ ያለችው ግዙፍ እየተባለች ነው የምትጠራው።

https://p.dw.com/p/16doP

አፍሪቃ ዛሬ የበለጸገው ዓለም በፊናንስና የኤኮኖሚ ችግር ተወጥሮ ባለበት ሰዓት በርከት ባሉ ምዕራባውያን የምጣኔ-ሐብት ጠበብት መጨዋ፤ በመንቃት፤ በመነሣት ላይ ያለችው ግዙፍ እየተባለች ነው የምትጠራው። የአፍሪቃ ክፍል-ዓለም፤ በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው ክፍል ለአሠርተ-ዓመታት የድህነት፣ የረሃብ፣ የእርስበርስ ጦርነት፣ የስደትና የመከራ መለያ ገጽታ ሆኖ ነው የኖረው። ነገር ግን ካለፈው አሠርተ-ዓመት ወዲህ በርከት ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት የሚታየው ያልተቋረጠ የልማት ዕርምጃ ምንም እንኳ ድህነትን ለማሸነፍ ባይበቃም በልማትና በኤኮኖሚ ጠበብት ዘንድ የተሥፋ ምንጭ መሆኑ አልቀረም።

ምዕራባውያን ባለሙያዎች የሚናገሩት ክፍለ-ዓለሚቱ የሚደነቅ የኤኮኖሚ ዕድገት እያሳየች፣ መካከለኛው የሕብረተሰብ መደብ እየሰፋና የሥራ መስኮችም እየተፈጠሩ በመሄድ ላይ እንደሚገኙ ነው። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል በብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች የሚታየው እስከ 30 በመቶና ከዚያም በላይ የሚዘልቅ የወጣት ሥራ አጦች ብዛት የልማቱን ዘላቂ ሆኖ መቀጠል አሳሳቢ አድርጎታል። ኦኢሲዲ በሚል አህጽሮት የሚጠራው የአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በቅርቡ ፓሪስ ላይ አካሂዶት በነበረ ከ 500 የሚበልጡ ፖለቲከኞች፣ የኤኮኖሚና የሣይንስ ጠበብት የተሳተፉበት ጉባዔ በአፍሪቃ የምጣኔ-ሐብት ይዞታ ላይ ሲያተኩር የወጣት አፍሪቃውያንን የወደፊት ዕድል ነበር ዓቢይ ማተኮሪያ ያደረገው።

በዓለምአቀፉ የአፍሪቃ መድረክ እንደተገለጸው የአውሮፓ ኤኮኖሚ እየመነመነ ወይም ባለበት የሚቀጥል ሲሆን የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በአንጻሩ በዚህ በያዝነው ዓመት በ 4,4 ከመቶ እንደሚያድግ ነው የተተነበየው። የኤኮኖሚው ዕድገት የአውሮፓ የዕዳ ቀውስ ሳይገታው በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ወደፊት መራመዱን እንደሚቀጥልም ይጠበቃል። የኤኮኖሚው ትብብርና ልማት ድርጅት ኢኢሲዲ ባቀረበው የአፍሪቃ ዘገባው እንዳመለከተው በሌላ በኩል ይሁንና ብዙሃኑ የአፍሪቃ ሕዝብ ያለፉት ዓመታት የኤኮኖሚ ዕድገት ፍሬ ተቋዳሽ ለመሆን አልበቃም።

ድህነትንና ረሃብን መታገሉ ተጎታች እንደሆነ ሲቀጥል ድርጅቱ ይህን ከፍተኛ አደጋ አድርጎ ነው የሚመለከተው። በትምሕርት፣ ጤና ጥበቃና በመዋቅራዊ ልማት ረገድ ያለው ጉድለት ከአካባቢ አየር መለወጥ ጋር ተያይዞ ለዕድገት ጸር መሆኑ ይታመናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአፍሪቃ ሃገራት ለልማታቸው ቀጣይነት አጣዳፊ የሆነውን አጣዳፊ ችግር የወጣቶችን ሥራ አጥነት ለመቀነስ የተፏጠነ መፍትሄ ማግኘታቸው ግድ ነው። አፍሪቃ በዓለም ላይ በወጣት ሕዝቧ ድርሻ ቀደምቷ ስትሆን በ 15 እና በ 24 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚገኙት ነዋሪዎቿ 200 ሚሊዮን ገደማ ይጠጋሉ።

ገና ከአሁኑ ደግሞ በርከት ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት 15 በመቶው ስርቶ ለማደር የሚሻ ወጣት እንኳ ቋሚ ገቢ የሚያገኝበት የሥራ ግንኙነት የለውም። እርግጥ መንግሥት ወይም በሚገባ ያልተስፋፋው ኢንዱስትሪ በቂ አዳዲስ የሥራ መስኮችን ሊከፍቱ የሚችሉ አይደሉም። ለዚህ አማራጭ መገኘቱ ግድ ነው። ኢትዮጵያም በሕዝብ ቁጥር ቀደምት ከሆኑት የአፍሪቃ ሃገራት አንዷ ስትሆን የወጣቱ ሥራ አጥ ብዛትም የዚያኑ ያህል ግዙፍ መሆኑ አያጠያያቅም። ቢያንስ ቢያንስ ከሃያ በመቶ የሚበልጠው የአገሪቱ ወጣት መተዳደሪያ ሥራ እንደሌለው ርቆ ሳይኬድ አደባባዩ ይናገራል። በወጣቱ ሥራ አጥነት ችግር፣ ድህነትና መፍትሄ ላይ በኢትዮጵያ የተወካዮች ም/ቤት ብቸኛውን የተቃዋሚ ወገን እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉን አነጋግሬያለሁ። ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ