1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ

ሐሙስ፣ ሰኔ 4 2001

አፍሪቃውያን መሪዎች የኤኮኖሚው ቀውስ በአህጉሩ ላይ ያስከተለውን መዘዝ የማስወገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን አሳሰቡ።

https://p.dw.com/p/I7VS
ምስል AP

ለኤኮኖሚያዊ እና የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትላቸው ችግሮች እንዲሁም፡ ለምግብ ዋስትና ቀውስ መፍትሄ ማፈላለግና የህዝቦቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎት በመጀመሪያ ደረጃ ማሟላት ያለባቸውም አፍሪቃውያን መሪዎች መሆናቸውን አናን አክለው አሳስበዋል። አናን ይህንን ጥሪ ያሰሙት በደቡብ አፍሪቃ ኬፕ ታውን ከተማ በተከፈተውና እስከ ነገ በሚቆየው በአፍሪቃ ላይ ባተኮረው አስራ ዘጠነኛው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ላይ ነበር።

በአፍሪቃ የኤኮኖሚው ዕድገትን በተመለከተ በወቅቱ አበረታቺ ዜና ባይሰማም፡ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ አለመሆኑን የተመድ ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን አስረድተዋል። አፍሪቃ፡ ምንም እንኳን በወቅቱ በድህነት የሚኖረው ህዝብዋ በአስራ ስድስት ከመቶ ቢጨምርምና ኤኮኖሚያዊ ዕድገትዋም ከስድስት ወደ አንድ ከመቶ ቢቀንስም፡ ወደፊት ምግብና የኃይል ምንጭን በንግድ ወደ ውጭ የምትልክና ዓለም አቀፉን ንግድ የምታሳድግ አህጉር የመሆን ተስፋ እንዳላት አመልክተዋል። በአሁኑ ጊዜ እንደሚታወቀው በአፍሪቃ ሊታረስ ከሚችለው መሬት መካከል አምስት ከመቶ ብቻ ለግብርናው ዘርፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው። በመሆኑም፡ አፍሪቃውያኑ መሪዎቹ የየሀገሮቻቸውን ግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻሉ አሰራር ትኩረት እንዲሰጡም እአአ በ 2007 ዓም የበለጸጉት ሀገሮች የልማት ርዳታ ለመስጠት የገቡትን ቃል መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የአፍሪቃ የልማት ሂደት ተመልካቹ ቡድን ያወጣው ዘገባ አስገንዝቦዋል። ይሁንና፡ አፍሪቃውያኑ መንግስታት መሪዎች በዓለም ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የተከሰተው የኤኮኖሚ ቀውስ አሁን በአህጉሩ ላይ እያስከተለ ያለውን መዘዝ የመቀነስ ዋነኛ ኃላፊነት መሸከማቸውን የቀድሞው ኮፊ አናን አስገንዝበዋል።

« መሪዎቹ ሊያደርጉዋቸው የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ። እንደሚታወቀው፡ የተወሰነ የተፈጥሮ ሀብት አለን፤ እና ይህንን በትክክል ልናስተዳድረው ይገባል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአህጉሩ የአነስተኛ የኤኮኖሚ መርሆች ተሻሻለዋል፤ በነዚሁ ዓመታትም ውስጥ ከአምስት ነጥብ አምስት ከመቶ የበለጠ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት አስገኝተዋል። ይሁን እንጂ፡ በወቅቱ ይህ ዕድገት የሚቀንስበት ስጋት ላይ ነው የምንገኘው። የዓለም ባንክ ዕድገቱ በሁለት ከመቶ ገደማ እንደሚቀንስ ከወዲሁ ጠቁሞዋል። ዕድገቱ ዝቅ እንደማይል ግን ተስፋ አደርጋለሁ። ይሁንና፡ አፍሪቃውያኑ መሪዎች ለዚሁ ጥረታቸው የተጓዳኞቻቸው ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። »

የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ኦ ኢ ሲ ዲ ባለፉት ዓመታት አፍሪቃን አስመልክቶ ባወጣቸው ዘገባዎቹ በአውሮጳና በእስያ አንጻር አፍሪቃ በዓለም አቀፍ የፊናንስ ክንውን ውስጥ ያን ያህል ያልተዋሀደች እንደመሆንዋ መጠን የኤኮኖሚው ቀውስ መጀመሪያ ላይ አፍሪቃን ያን ያህል አይጎዳም የሚል ተስፋ አሰምቶ ነበር። ይሁንና፣ የድርጅቱ ኤኮኖሚ ጠቢብ ዮሀንስ ዩቲንግ ገሀዱን ከዚህ ለየት ያለ ሆኖ ነው ያገኙት።

« የሚያሳዝነው ገሀዱ ይህን አይመስልም። ዘገባው በዋነኛነት ያነሳው ጉዳይ እንደጠቆመው፡ በአህጉሩ ለአንድ ግማሽ አሰርተ ዓመት ከታየው ጠንካራና ከአምስት ከመቶ በላይ ከሆነ የኤኮኖሚ ዕድገት በኋላ ለ 2009 ዓም የሚጠበቀው ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ብሩህ አይደለም። »

በተለይ ጥሬ አላባን ወደውጭ የሚልኩ አፍሪቃውያት ሀገሮች የኤኮኖሚው ቀውስ በነዚሁ ጥሬ አላባ ዋጋ ላይ ባስከተለው ቅናሽ አብዝተው ተጎድተዋል። ለምሳሌ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ በካታንጋ ክፍለ ሀገር አካባቢ ውስጥ ከስድሳ ከመቶ የሚበልጠው የመዳብና ኮባልት ማዕድኖች በመዘጋታቸው ከ300,000 የሚበልጡ ሰዎች ካለ ስራ ቀርተዋል። በደቡብ አፍሪቃም የፕላቲንየም ዋጋ በአርባ ከመቶ በመቀነሱ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ስራ አጥ ሆነዋል። በዚህ የተነሳ፡ አፍሪቃውያት ሀገሮች የኤኮኖሚ አለመረጋጋትን እና ወቅት እየጠበቀ የሚታይ ኤኮኖሚያዊ ዝግመትን ለመከላከል ይችሉ ዘንድ በአንድ ማዕድንን በመሰለ የኤኮኖሚ ዘርፍ ላይ ብቻ ጥገኛ ከሆኑበትን አሰራር በመላቀቅ፡ ለግብርናውም ትኩረት እንዲሰጡ ከፍተኛ የዓለም ፖለቲከኞችና ባለሀብቶች በተሳተፉበት የኬፕ ጉባዔ ላይ ሀሳብ ቀርቦዋል።

አርያም ተክሌ/ሸዋዬ ለገሠ