1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃዉያ ከቡድን 20 ምን ይጠብቃሉ?

ሐሙስ፣ ሰኔ 22 2009

በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው ሀገራት መሪዎች በሀምሌ መጀመሪያ ላይ ጀርመን በምታስተናግደው የቡድን 20 ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሀምቡርግ ይመጣሉ። በጉባዔው አፍሪቃ ትልቅ ሚናን እንደምትጫወት ተገልጿል። አፍሪቃዉያንስ ከቡድን 20 ጉባኤ ምን ይጠብቃሉ?

https://p.dw.com/p/2fdJN
Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

G20-Gipfel: Was erwartet Afrika?/ONLINE - MP3-Stereo

 

የናይጀርያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂዮፍሬ ኦንያማ «ቡድን 20» የሚለዉን ቃል ሲሰሙ ከአንደበታቸዉ የሚወጣዉ ሙገሳና ጥሩ ቃላት ነዉ። ኦንያማ ጀርመን የ « ቡድን 20» ሊቀመንበር  በሆነችበት ጊዜ  ሁኔታዉ ሁሉ በጣም ጥሩ ነበር፤ የጀርመንና የናይጀርያ የወዳጅነት ግንኙነትም እጅግ ጥሩ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

«ጀርመን የቡድን 20 ጉባዔን በፕሬዚደንትነት መምራቷ ለኛ አዎንታዊ ነዉ። ምክንያቱም ከጀርመን ጋር እጅግ ጥሩ ግንኙነት አለን። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና ፕሬዚደንት ቡሃሪም የጠነከረ ወዳጅነት አላቸዉ። የቡድን 20 አባል ሃገር የመሆን ፍላጎትም አለን። » 

Deutschland G20 Afrika Treffen Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ስለዚህም  የናይጀርያዊዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦንያማ፤ ጀርመን ፤ ናይጀርያ የቡድን 20 አባል ሃገር እንድትሆን እንድትረዳት ጠይቀዋል። ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፤ « ቡድን 20 ጠቃሚ አካል ነዉ። ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች በሚወሰዱበት ጊዜ ከነዚህ ዋና ከሚባሉ አባል ሃገራት ጋር ባንድነት መቀመጡ ለናይጀሪያ ትልቅ ትርጉም አለው።   »

በወቅቱ የቡድን 20 ጉባዔ ላይ ደቡብ አፍሪቃ ብቸኛዋ ተሳታፊ አፍሪቃዊት ሃገር ስትሆን፤ ከፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ ለጥቆ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር አልፋ ኮንዴ እንዲሁም «ለአፍሪቃ ልማት አዲስ ወዳጅነት» በምህፃሩ  የ«NEPAD» ን ወክለዉ የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በጉባዔዉ ላይ ይገኛሉ።

ጀርመን በቡድን 20 ፕሬዚደንትነት ወቅቷ  ያደረገችዉ ጥረት በብዙዎች የአፍሪቃ ፖለቲከኞች በጣም ይወደሳል። በሰኔ ወር አጋማሽ  በርሊን ላይ በተካሄደዉ የአፍሪቃ ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩት የአፍሪቃ ሃገራት ፕሬዚዳንቶች የጀርመንዋ  መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ጥረት አድንቀዋል። በዚሁ ስብሰባ ላይ የጊኒዉ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ስብሰባዉን «የሜርክል እቅድ ለአፍሪቃ » ሲሉ ነበር የሰየሙት። ይሁንና በስብሰባዉ ይህን መሠል ጥሩ ቃል ይሰማ እንጂ አፍሪቃዉያኑ ከዚህ በስተጀርባ የሚጠብቁት ነገር እንዳለ የታወቀ ነዉ። ቡድን 20 የግል መዋለ ንዋይ አፍሳሾችን ወደ አፍሪቃ ለማንቀሳቀስ ቃል ገብቶአል። የዚህ ፕሮግራም ዋናዉ ጉዳይም  በአፍሪቃ ሃገራት በቡድን 20 እንዲሁም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል የመዋለ ንዋይ አፍሳሾች ትብብር ነዉ። የአፍሪቃ መንግሥታት በበኩላቸዉ ይህን እቅድ ለአፍሪቃ የበለጠ የሥራ እድሎችን እና ኃብትን ያመጣል ብለዉ ተስፋ ያደርጋሉ።

የኤኮኖሚ ጉዳይ ተወካዮችም ይህን የቡድን 20 እቅድ ትክክለኝነት ይናገራሉ። ጆሃንስበርግ  በሚገኝ የንግድ ማዕከል ዳይሬክተር ዶና ኔመር እንደሚሉት ይህን የግል መዋለ ንዋይ አፍሳሾችን እንቅስቃሴ በብዙ ሠዎች ዘንድ ተሰሚነት ይኖረዋል። «የአፍሪቃ የርዳታ ፕሮግራም ለአፍሪቃ ልማት እድገት ቁልፍ ይሆናል ብለን አንገምትም፤ ብለዋል። » በታንዛንያ የሚገኝ አንድ የዶይቼ ቬለ የኪስዋሂሊ ቋንቋ ፊስቡክ ተከታታይ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰጥቶአል።

« ጠንካራ ቴክኖሎጂ እና ኤኮኖሚ ያላቸዉ አጋር አገራት የአፍሪቃን ኤኮኖሚ ሊረዱ ይችላሉ»  ሌላዉ አስተያየት ሰጭ በበኩሉ፤

Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

« አፍሪቃን በተመለከተ የአፍሪቃና የጀርመን ፖለቲከኞች ትኩረት የተሞላዉ ፍላጎትን ካሳዩ ፤ በኤኮኖሚና አካባቢዊ ጉዳዮች ላይ  አዎንታዊ ለዉጥን ሊያመጡ ይችላሉ»   ሲል አስተያየቱን አስቀምጦአል። የኒጀር የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ማና ሳኒ አዳሙ ይህን ጉዳይ በጥርጣሬ ነዉ የሚመለከቱት። ቡድን 20  የአፍሪቃን እድገት ለማራመድ የሚያደርገው ጥረት ጥሩ ይመስላል።  በተካሄዱት ጉባዔዎች ላይ ሌሎች ሃገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች  አፍሪቃን እንዴት መርዳት እንደሚቻል በተደጋጋሚ ሃሳብ አቅርበዋል።  ጥያቄዉ ግን፣ ይላሉ አዳሙ፣ የአፍሪቃ ሃገራት ፍላጎታቸዉን እንዴት አቀናጅተው ባንድነት ማቅረብ ይችላሉ የሚለዉ ነዉ።

« ጀርመን ለአፍሪቃ ልማት ይበጃል በሚል የወጠነችውን  እቅድ ያዘጋጀችው ከአምስት የአፍሪቃ  ሃገራት ማለትም ሴኔጋል ኮትዴቮዋር፤ ቱኒዝያ ሩዋንዳ እና ሞሮኮ ጋር ከተነጋገረች በኋላ ነው። ደቡብ አፍሪቃ በርግጥ የቡድን 20 አባል ሃገር ናት። እዚህ ላይ ጥያቄዉ የአፍሪቃ ሃገራት ፍላጎታቸዉን በትክክል ማቅረብ ይችላሉ የሚለዉ ነዉ።  ችግሩ እስካሁን በተደጋጋሚ ለአፍሪቃ ልማት የተለያየ ሀሳብ መቅረቡ ነው። አፍሪቃውያኑ በርግጥ የሚፈልጉትን በትክክል ማሳወቅ አለባቸው። አፍሪቃውያኑ የልማት እቅድ አልያም  ማርሻል ፕላን ብለዉ የሚጠሩትን ንድፈ ሃሳብ ለቡድን 20 ጉባዔ ቢያቀርቡ በጣም የተሻለ ይሆን ነበር» 

Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

የንግድ ግንኙነቱ ለዉጥ እንዲደረግበት ዉጥረት ማሳደር ይገባቸዉ ነበር። በዚህም የወቅቱ  የቡድን 20 አፍሪቃ እንቅስቃሴ በአፍሪቃ ትልቅ የኤኮኖሚ ዉጤት ያመጣል ብሎ አይጠበቅም። አንዳንድ  አፍሪቃዉያን የዶይቼ ቬለ የፊስቡክ ተከታታዮች አስተያየቶች ከዚህ ዘለል ያሉ ናቸዉ። ከቤኒን የዶይቼ ቬለ የፈረንሳይ ቋንቋ ክፍል ተከታታይ አዚሃኑ ማዉናዮ ባስቀመጠዉ አስተያየት፤ «ምዕራባዉያን ሃገራት የራሳቸዉን ጥቅም እያሳደደዱ ለአፍሪቃ ሃገራት እድልና ልማትን እየፈለግን ነዉ ሲሉ የሚናገሩትን ነገር ቢያቆሙ ጥሩ ነዉ » ብለዋል። ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ፓቴንት ፓዉል ንጎዮ የተባለዉ የዶይቼ ቬለ ሌላዉ የፈረንሳይ ቋንቋ ተከታታይ በበኩሉ «ስለ አፍሪቃ ልማት መናገር የሚችሉት አፍሪቃዉያን ብቻ ናቸዉ።»  ሲል አስተያየቱን አስቀምጦአል።  ይህ ማለት  ምራባዉያኑ ሃገራት አፍሪቃዉያኑ እራሳቸዉ በቀደዱት መንገድ እንዲራመዱ ሊለቁዋቸዉ ይገባል ነዉ።

አንዳንዶች ተስፋ የሚያደርጉት ቡድን  20 አባል ሃገራት አስቸኳይ ጥያቄዎችን ችላ እንዳይሉ ነዉ። ሌላዉ የዶይቼ ቬለ የፈረንሳይ ቋንቋ ክፍል ተከታታይ ባስቀመጠዉ አስተያየቱ « የቡድን 20 ጉባዔ ተሳታፊዎችን የምንጠይቀዉ በአፍሪቃ ትክክለኛ ዴሞክራሲን ለማስፋፋት እንዲረዱ ነዉ ። ያለ ዴሞክራሲ ትክክለኛ ልማት የለም። 

አዜብ ታደሰ / ዳንየል ፔልስ

አርያም ተክሌ