1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያን ስደተኞችና ኦሊምፒክ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20 2008

ከተለያዩ አፍሪቃውያት ሀገራት የተውጣጡ ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በኬንያ ስልጠና በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ዓላማቸውም፣ በዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባንዴራ ስር አንድ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቡድንን ወክለው እጎአ ነሀሴ አምስት፣ 2016 ዓም በብራዚል የሪዮ ደ ጃንየሮ ከተማ በሚደረጉት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተወዳዳሪነት ለመሳተፍ ነው።

https://p.dw.com/p/1Iefr
Brasilien, Olympische Spiele 2016 Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

[No title]

ቁጥራቸው ከአስር የሚበልጡ አፍሪቃውያን ወንዶች እና ሴቶች አትሌቶች ኬንያ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ በ2,400 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው የንጎንግ ተራራ የሩጫ ልምምዱን ተያይዘውታል። ጭቃማ በሆነው መሬት ላይ መሮጡን አትሌቶቹ እክል አድርገው አያዩትም።

አትሌቶቹ የኮንጎ፣ የሶማልያ እና የደቡብ ሱዳን ተወላጆች ናቸው፤ ይሁንና፣ የዜግነቱ ጥያቄ ለነርሱ አንዳችም ሚና አይጫወትም። ምክንያቱም፣ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ስደተኞች መሆናቸው ነው፤ በሪዮ ደ ጃንየሮ፣ ብራዚል በሚካሄዱት የኦሊምፒክ ግጥሚያዎች መሳተፍ ዋነኛው ዓላማቸውም መሆኑን ሶማልያዊው መሀመድ ዳውድ አቡበከር ይናገራል።
« ለሪዮ እንደማልፍ እርግጠኛ ነኝ። ለ5,000 እና ለ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድር ስልጠና ሳደርግ ይኸው አንድ ዓመት ገደማ ሆኖኛል። ርቀቱን የምጨርስበት ሰዓትም ሁሌ በመሻሻል ላይ ነው። »
መሀመድ ከሶማልያ ጦርነትን ሸሽቶ ወደ ኬንያ በመሰደድ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖር ነበር፣ በዚያ የመሀመድ ዳውድን የሩጫ ችሎታ ያየችው በሴቶች የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን የያዘችው ኬንያዊትዋ አትሌት ቴግላ ሎሩፕ መሀመድን ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያዋ በመውሰድ፣ የምታሰለጥናቸውን ሌሎች የስደተኞች ቡድን እንዲቀላቀል በማድረግ ስልጠናዋን እንደቀጠለች በመግለጽ፣ ይኸው ርምጃዋ ድጋፍ እንዳገኘላት አስታውቃለች።
« ከዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ቶማስ ባኽ ጋር ተገናኘን፣ እሳቸውም በሪዮ አንድ ስደተኞችን የሚወክል ቡድን የሚሳተፍበትን ሀሳብ አመጡ። እና በዚሁ አነጋገራቸው ስደተኞቹን የማሰልጠን ጥረቴን እንደሚደግፉልኝ ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ። »
አሳዛኝ የስደት ሕይወት የመራችው የ23 ዓመቱ ሮዝ ናትሂከ በ800 ሜትር ሩጫ ለመወዳደር ተስፋ አድርጋለች።
« የሱዳን ጦርነትን በመሸሽ ወደካኩማ መጠለያ ጣቢያ መጥተናል። በካኩማ ስኖር ይኸው ከአስር ዓመት በላይ ሆኖኛል። »
ወላጆችዋ እርግጥ ወደ ሱዳን ተመልሰዋል፣ ሮዝ ግን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ትምህርቷን መከታተል ስለቻለች በዚያው ቀርታለች። ከዚያን ጊዜ ወዲህም ወላጆችዋን አይታ አታውቅም። በሕይወት ካሉ የፊታችን ነሀሴ በሪዮ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሲጀመሩ ሊያዩዋት ይችሉ ይሆናል ብላ ሮዝ ተስፋ አድርጋለች።
ቴግላ ከምታሰለጥናቸው ስደተኞች መካከል አንድ ወይም ሁለቱ ለሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያልፋሉ ብላ ታስባለች።

Afika Kenia Iten Runners
ምስል DW

ቪም ዶርንቡሽ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ